በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኩሩዎቹ እና ትሑቶቹ

ኩሩዎቹ እና ትሑቶቹ

ምዕራፍ 39

ኩሩዎቹ እና ትሑቶቹ

ኢየሱስ የአጥማቂው ዮሐንስን መልካምነት ከጠቀሰ በኋላ ትኩረቱን በዙሪያው ወዳሉት ኩሩና ተለዋዋጭ ባህርይ ያላቸው ሰዎች አዞረ። የዚህ ትውልድ ሰዎች አለ:- “በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፣ እነርሱም ባልንጀሮቻቸውን እየጠሩ:- እንቢልታ ነፋንላችሁ ዘፈንም አልዘፈናችሁም፤ ሙሾ አወጣንላችሁ ዋይ ዋይም አላላችሁም ይሉአቸዋል።”

ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር? እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፣ እነርሱም:- ጋኔን አለበት አሉት። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፣ እነርሱም:- እነሆ፣ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ይሉታል።”

ሰዎቹን ማርካት አስቸጋሪ ነበር። ምንም ነገር አያስደስታቸውም ነበር። ዮሐንስ “የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም” ከሚለው የመልአኩ መግለጫ ጋር በሚስማማ መንገድ ናዝራዊ ሆኖ የራሱን ጥቅም በመሠዋት ምቾት የለሽ ሕይወት አሳልፏል። ሰዎቹ ግን ጋኔን አለበት አሉት። በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ ራሱን ሳይጨቁን የሌሎቹን ሰዎች ዓይነት ኑሮ በመኖሩ መረኑን ለቋል ብለው ከሰውታል።

ሰዎቹን ማስደሰት ምንኛ አስቸጋሪ ነበር! ጓደኞቻቸው እንቢልታ ሲነፉላቸው በዘፈን ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኞች እንዳልሆኑ ወይም ሙሾ ሲያወጡላቸው ዋይ ዋይ ለማለት አሻፈረኝ እንዳሉ ልጆች ናቸው። ሆኖም ኢየሱስ “ጥበብም በልጆችዋ [“በሥራዋ፣” NW] ጸደቀች” ብሏል። አዎን፣ ማስረጃዎቹ ማለትም በተግባር የተፈጸሙት ነገሮች በዮሐንስ ላይም ሆነ በኢየሱስ ላይ የቀረቡት ክሶች ሐሰት መሆናቸውን በግልጽ ያሳያሉ።

በመቀጠል ኢየሱስ አብዛኞቹን ተአምራት የፈጸመባቸውን ሦስት ከተሞች ማለትም ኮራዚንን፣ ቤተ ሳይዳንና ቅፍርናሆምን በስም በመጥቀስ ነቀፋቸው። ኢየሱስ ተአምራቱን የፊንቄ ከተሞች በሆኑት በጢሮስና በሲዶና ፈጽሞ ቢሆን ኖሮ ማቅ ለብሰውና አመድ ነስንሰው ንስሐ ይገቡ እንደነበረ ተናገረ። ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት እንደ መኖሪያውና የእንቅስቃሴው ማዕከል አድርጎ ይጠቀምባት የነበረችውን ቅፍርናሆምን በማውገዝ “በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም አገር ይቀልላታል” አለ።

ቀጥሎም ኢየሱስ ሰማያዊ አባቱን በሕዝብ ፊት አወደሰ። እንዲህ ለማድረግ የተገፋፋው አምላክ ውድ የሆኑትን መንፈሳዊ እውነቶች ከጥበበኞችና ከምሁራን ሰውሮ ለዝቅተኛ ሰዎች ወይም በምሳሌያዊ አነጋገር ለሕፃናት በመግለጹ ነበር።

በመጨረሻ ኢየሱስ የሚከተለውን ማራኪ ጥሪ አቀረበ:- “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።”

ኢየሱስ ዕረፍት የሚሰጠው እንዴት ነው? የሃይማኖት መሪዎቹ የሰንበት ቀንን በሚመለከት አውጥተዋቸው የነበሩትን የእገዳ ደንቦች ጨምሮ በሰዎቹ ላይ ከጫኗቸው ባሪያ የሚያደርጉ ወጎች ነፃ በማውጣት ነው። በተጨማሪም የፖለቲካ ባለ ሥልጣናት አገዛዝ ሊወጡት የማይችሉት ከባድ ሸክም የሆነባቸው ሰዎችና በሠሯቸው ኃጢአቶች ሕሊናቸው ቆስሎ በጣም የተጨነቁ ሰዎች እፎይታ የሚያገኙበትን መንገድ ያሳያቸዋል። እንዲህ ዓይነቶቹ ሕሊናቸው የተጎዳ ሰዎች ኃጢአታቸው እንዴት ይቅር ሊባልላቸው እንደሚችልና ከአምላክ ጋር እንዴት ውድ ዝምድና ሊመሠርቱ እንደሚችሉ ይገልጽላቸዋል።

ኢየሱስ ያቀረበው ልዝብ ቀንበር ራስን ሙሉ በሙሉ ለአምላክ መወሰንና ርኅሩኁንና መሐሪውን ሰማያዊ አባታችንን ማገልገል መቻልን የሚጠይቅ ነው። ኢየሱስ ወደ እሱ ለሚመጡት ሰዎች ያቀረበው ቀላል ሸክም ደግሞ አምላክ ለሕይወት ያወጣቸውን ብቃቶች ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙትን ትእዛዛቱን ማክበር የሚጠይቅ ነው። እነዚህን ትእዛዛት ማክበር ደግሞ ከባድ አይደለም። ማቴዎስ 11:​16-30፤ ሉቃስ 1:​15፤ 7:​31-35፤ 1 ዮሐንስ 5:​3

▪ በኢየሱስ ዘመን የነበረው ኩሩና ተለዋዋጭ ትውልድ እንደ ልጆች የነበረው እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ ሰማያዊ አባቱን ለማወደስ የተገፋፋው ለምንድን ነው?

▪ ሰዎች ከባድ ሸክም የተጫናቸው በምን መንገዶች ነው? ኢየሱስ የሚሰጠው ዕፎይታስ ምንድን ነው?