በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቶስ በድል ወደ ኢየሩሳሌም ገባ

ክርስቶስ በድል ወደ ኢየሩሳሌም ገባ

ምዕራፍ 102

ክርስቶስ በድል ወደ ኢየሩሳሌም ገባ

በሚቀጥለው ቀን ማለትም ኒሳን 9 እሁድ ዕለት ጠዋት ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ ቢታንያን ለቆ ወጣና በደብረ ዘይት ተራራ አድርጎ ወደ ኢየሩሳሌም አቀና። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ወደምትገኘው ወደ ቤተ ፋጌ አቅራቢያ ደረሱ። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ አላቸው:-

“በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፣ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ማንም አንዳች ቢላችሁ:- ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል።”

ምንም እንኳ መጀመሪያ ላይ ደቀ መዛሙርቱ እነዚህ መመሪያዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አፈጻጸም ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ያልተረዱ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ተገንዝበውታል። ነቢዩ ዘካርያስ አምላክ ተስፋ የሰጠበት ንጉሥ በአህያ ላይ፣ አዎን፣ “በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ” ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚገባ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። በተመሳሳይም ንጉሥ ሰሎሞን ለንግሥና ወደሚቀባበት ቦታ የሄደው በአህያ ልጅ ላይ ተቀምጦ ነው።

ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቤተ ፋጌ ገብተው ውርንጭላይቱንና እናቷን ሲወስዱ በዚያ ቆመው ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ ‘ምን ማድረጋችሁ ነው?’ አሏቸው። ሆኖም እንስሶቹን የሚወስዱት ለጌታ እንደሆነ ሲነግሯቸው እንዲወስዱለት ፈቀዱላቸው። ደቀ መዛሙርቱ ከላይ የሚደርቡትን ልብስ አውልቀው በአህያዋና በውርንጭላዋ ላይ አነጠፉት፤ ኢየሱስ ግን በውርንጭላዋ ላይ ተቀመጠ።

ኢየሱስ በውርንጭላዋ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ የሕዝቡ ቁጥር ጨመረ። አብዛኞቹ ሰዎች ከላይ የደረቡትን ልብስ አውልቀው በመንገዱ ላይ ሲዘረጉ ሌሎቹ ደግሞ የዛፍ ዝንጣፊዎችን ቆርጠው መንገዱ ላይ አነጠፉ። “በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው” በማለት ጮኹ። “በሰማይ ሰላም በአርያምም ክብር” አሉ!

በሕዝቡ መካከል የነበሩ አንዳንድ ፈሪሳውያን በእነዚህ ዕወጃዎች ተበሳጭተው “መምህር ሆይ፣ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው” በማለት ለኢየሱስ አቤቱታ አቀረቡ። ሆኖም ኢየሱስ “እላችኋለሁ፣ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ” ሲል መለሰላቸው።

ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየቀረበ ሲሄድ ከተማይቱን አየና እንዲህ ሲል አለቀሰላት:- “ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል።” ኢየሱስ እንደሚከተለው ሲል በተናገረው ትንቢት መሠረት ኢየሩሳሌም ሆን ብላ ለመታዘዝ አሻፈረኝ በማለቷ መቀጣት ነበረባት:-

“ጠላቶችሽም [በጄኔራል ቲቶ የሚመሩት ሮማውያን] ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፣ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም።” ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገረው ይህ የኢየሩሳሌም ጥፋት ከ37 ዓመታት በኋላ በ70 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ፍጻሜውን አግኝቷል።

በሕዝቡ መካከል ያሉት ብዙዎቹ ሰዎች ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ሲያስነሳው ተመልክተዋል። አሁን እነዚህ ሰዎች ስለዚህ ተአምር ለሌሎች መናገራቸውን ቀጠሉ። ስለዚህ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ከተማው በሁከት ተሞላ። ሰዎቹ “ይህ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁ። ሕዝቡም “ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ። ፈሪሳውያን እየተከናወነ ያለውን ነገር ተመልክተው ምንም ነገር ማድረግ እንዳልቻሉ ስለተሰማቸው “ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል” በማለት በምሬት ተናገሩ።

ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ብዙ ጊዜ እንደሚያደርገው ሁሉ አሁንም በቤተ መቅደሱ ለማስተማር ሄደ። እዚያም ዓይነ ስውሮችና አንካሶች ወደ እሱ መጡና ፈወሳቸው! የካህናት አለቆቹና ጻፎቹ ኢየሱስ እየፈጸማቸው የነበሩትን አስደናቂ ነገሮች ሲመለከቱና በቤተ መቅደሱ የነበሩት ልጆች “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ” እያሉ ሲጮኹ በሰሙ ጊዜ ተቆጡ። “እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን?” በማለት ተቃወሙ።

ኢየሱስ “እሰማለሁ” ሲል መለሰ። “ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን?” አላቸው።

ኢየሱስ ማስተማሩን ቀጠለ፤ ከዚያም ዞር ብሎ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ ተመለከተ። ብዙም ሳይቆይ ቀኑ መሸ። ስለዚህ ከአሥራ ሁለቱ ጋር ሆኖ ከዚያ ወጣና እንደገና ሦስት ኪሎ ሜትር ገደማ ተጉዞ ወደ ቢታንያ ተመለሰ። እሁድ ሌሊት በዚያ አደረ፤ ያደረውም በወዳጁ በአልዓዛር ቤት ሳይሆን አይቀርም። ማቴዎስ 21:​1-11, 14-17፤ ማርቆስ 11:​1-11፤ ሉቃስ 19:​29-44፤ ዮሐንስ 12:​12-19፤ ዘካርያስ 9:​9

▪ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ንጉሥ ሆኖ የገባው መቼና በምን ዓይነት ሁኔታ ነበር?

▪ ሕዝቡ ኢየሱስን ማወደሳቸው ምን ያህል አስፈላጊ ነበር?

▪ ኢየሱስ ኢየሩሳሌምን ሲያይ ምን ተሰማው? ምን ትንቢትስ ተናገረ?

▪ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ሲሄድ ምን ነገር ተከናወነ?