በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርክር ተነሣ

ክርክር ተነሣ

ምዕራፍ 115

ክርክር ተነሣ

ገና አመሻሹ ላይ ኢየሱስ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ የትሕትና አገልግሎትን በተመለከተ ግሩም ትምህርት ሰጥቶ ነበር። ከዚያ በኋላ እየተቃረበ ላለው ሞቱ የመታሰቢያ በዓል አቋቋመ። አሁን በተለይ ከጥቂት ጊዜ በፊት ከተፈጸመው ሁኔታ አንጻር በጣም አስገራሚ የሆነ አንድ ነገር ተከሰተ። ሐዋርያቱ ከመካከላቸው ታላቅ ስለሚሆነው ሰው የጦፈ ክርክር ማድረግ ጀመሩ! ይህ ቀደም ሲል ተካሄዶ የነበረው ክርክር ቀጣይ ክፍል ሳይሆን አይቀርም።

ኢየሱስ በተራራው ላይ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከተለወጠ በኋላ ሐዋርያቱ በመካከላቸው ታላቅ ስለሚሆነው ሰው ተከራክረው እንደነበረ አስታውስ። ከዚህም በተጨማሪ ያዕቆብና ዮሐንስ በመንግሥቱ ከፍ ያለ ቦታ እንዲሰጣቸው በመጠየቃቸው በሐዋርያቱ መካከል ሌላ ጭቅጭቅ ተነስቶ ነበር። አሁን ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር በሚያሳልፈው በዚህ የመጨረሻ ሌሊት እንደገና ሲጣሉ ሲያይ ምንኛ አዝኖ ይሆን! ኢየሱስ ምን እርምጃ ወሰደ?

ኢየሱስ ሐዋርያቱን ባሳዩት ጠባይ አልተቆጣቸውም፤ ከዚህ ይልቅ አሁንም እንደገና በትዕግሥት እንዲህ ሲል አሳማኝ የሆነ ሐሳብ አቀረበላቸው:- “የአሕዛብ ነገሥታት ይገዙአቸዋል፣ በላያቸውም የሚሠለጥኑት ቸርነት አድራጊዎች ይባላሉ። እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ . . . በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው? የተቀመጠው አይደለምን?” ከዚያም የራሱን ምሳሌ እንዲያስቡ በማድረግ “እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ” አላቸው።

ምንም እንኳ ሐዋርያቱ አለፍጽምና የነበረባቸው ቢሆንም በፈተናዎቹ ሁሉ ከኢየሱስ ጋር ተጣብቀው ቆይተዋል። ስለዚህ እንዲህ አለ:- “አባቴ ከእኔ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን እንደገባ ሁሉ እኔም ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ።” (NW) ይህ በኢየሱስና በታማኝ ተከታዮቹ መካከል የተደረገ የግል ቃል ኪዳን ከእሱ ጋር የንጉሣዊ ሥልጣኑ ተካፋዮች እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ወደዚህ የመንግሥት ቃል ኪዳን የሚገቡት ሰዎች ቁጥር 144,000 ብቻ ይሆናል።

ሐዋርያቱ ምንም እንኳ ይህን የመሰለ ከክርስቶስ ጋር በመንግሥታዊ አገዛዝ የመካፈል ግሩም ተስፋ የቀረበላቸው ቢሆንም በዚህ ወቅት በመንፈሳዊ ደካሞች ነበሩ። ኢየሱስ “በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ” አላቸው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ጴጥሮስን ስለ እሱ እንደጸለየ ከገለጸለት በኋላ “አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና” ሲል አጥብቆ አሳሰበው።

“ልጆች ሆይ፣” አለ ኢየሱስ፤ “ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድም:- እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አይቻላችሁም እንዳልኋቸው፣ አሁን ለእናንተ ደግሞ እላችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፣ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።”

ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ ወዴት ትሄዳለህ?” ሲል ጠየቀው።

“ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፣” ሲል ኢየሱስ መለሰለት፤ “ነገር ግን በኋላ ትከተለኛለህ” አለው።

“ጌታ ሆይ፣ አሁን ልከተልህ አለመቻሌ ስለ ምንድር ነው?” ሲል ጴጥሮስ ጠየቀ። “ነፍሴን ስንኳ ስለ አንተ እሰጣለሁ” አለው።

“ነፍስህን ስለ እኔ ትሰጣለህን?” ሲል ኢየሱስ ጠየቀው። “እውነት እልሃለሁ፣ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው።

“ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፣ ከቶ አልክድህም” በማለት ጴጥሮስ ተቃውሞውን ገለጸ። ሌሎቹ ሐዋርያትም ተመሳሳይ የሆነ ነገር ሲናገሩ ጴጥሮስ “ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም” በማለት ተኩራራ።

ኢየሱስ ሐዋርያቱን በገሊላ እየዞሩ እንዲሰብኩ ያለ ኮሮጆና ያለ ከረጢት ልኳቸው እንደነበረ በመጥቀስ “አንዳች ጐደለባችሁን?” ሲል ጠየቃቸው።

“አንዳች እንኳ” ሲሉ መለሱ።

“አሁን ግን ኮረጆ ያለው ከእርሱ ጋር ይውሰድ፣ ከረጢትም ያለው እንዲሁ” አላቸው፤ “የሌለውም ልብሱን ሽጦ ሰይፍ ይግዛ። እላችኋለሁና፣ ይህ:- ከዓመፀኞች ጋር ተቈጠረ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ሊፈጸም ግድ ነው፤ አዎን፣ ስለ እኔ የሚሆነው አሁን ይፈጸማልና።”

ኢየሱስ ከክፉ አድራጊዎች ወይም ከዓመፀኞች ጋር የሚሰቀልበትን ጊዜ መጥቀሱ ነበር። በተጨማሪም ከዚያ በኋላ ተከታዮቹ ከባድ ስደት እንደሚደርስባቸው ማመልከቱ ነበር። እነርሱም “ጌታ ሆይ፣ እነሆ፣ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ” አሉት።

እርሱም “ይበቃል” አላቸው። ወደፊት እንደምንመለከተው ሰይፎቹን መያዛቸው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢየሱስ ሌላ በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት እንዲሰጣቸው አጋጣሚ ይፈጥርለታል። ማቴዎስ 26:​31-35፤ ማርቆስ 14:​27-31፤ ሉቃስ 22:​24-38፤ ዮሐንስ 13:​31-38፤ ራእይ 14:​1-3

▪ የሐዋርያቱ ክርክር በጣም የሚያስገርመው ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ ለክርክሩ እልባት የሰጠው እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን ዓላማው ምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ ምን አዲስ ትእዛዝ ሰጠ? ትእዛዙስ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

▪ ጴጥሮስ ከሚገባው በላይ በራሱ እንደተማመነ ያሳየው እንዴት ነው? ኢየሱስስ ምን አለው?

▪ ኢየሱስ ኮሮጆና ከረጢት ስለ መያዝ የሰጠው መመሪያ ቀደም ሲል ስለ እነዚህ ነገሮች ከሰጠው መመሪያ የተለየ የሆነው ለምንድን ነው?