በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወሳኝ የሆነው ቀን ሲጀምር

ወሳኝ የሆነው ቀን ሲጀምር

ምዕራፍ 105

ወሳኝ የሆነው ቀን ሲጀምር

ኢየሱስ ሰኞ ምሽት ኢየሩሳሌምን ከለቀቀ በኋላ በደብረ ዘይት ተራራ ምሥራቃዊ ዐቀበት ወደምትገኘው ወደ ቢታንያ ተመለሰ። በኢየሩሳሌም ካከናወነው የመጨረሻ አገልግሎት ሁለቱ ቀኖች ተገባደዋል። ኢየሱስ አሁንም ሌሊቱን ያሳለፈው በወዳጁ በአልዓዛር ቤት እንደሆነ አያጠራጥርም። ዓርብ ዕለት ከኢያሪኮ ከመጣ ጊዜ ጀምሮ በቢታንያ ሲያድር ይህ አራተኛ ጊዜው ነው።

አሁን ኒሳን 11 ማክሰኞ ጠዋት ማለዳ ላይ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እንደገና መጓዝ ጀመሩ። ይህ ቀን በኢየሱስ አገልግሎት ውስጥ ወሳኝ ነገሮች የተከናወኑበትና እስካሁን ካሳለፋቸው ጊዜያት ሁሉ በበለጠ በሥራ የተጠመደበት ዕለት ነበር። ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ለመጨረሻ ጊዜ የሄደበት ዕለት ነበር። ፍርድ ፊት ቀርቦ ከመገደሉ በፊት የመጨረሻውን ሕዝባዊ አገልግሎት ያከናወነውም በዚህ ቀን ነው።

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ አሁንም በደብረ ዘይት ተራራ ላይ አድርገው ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዙ። ከቢታንያ ተነሥተው እየተጓዙ ሳለ መንገድ ላይ ጴጥሮስ በፊተኛው ቀን ጠዋት ኢየሱስ የረገማትን ዛፍ ተመለከተ። “መምህር ሆይ፣ እነሆ፣ የረገምሃት በለስ ደርቃለች” አለው።

ኢየሱስ ዛፏን ያደረቃት ለምን ነበር? ኢየሱስ እንዲህ ብሎ በተናገረ ጊዜ ምክንያቱን ገልጿል:- “እውነት እላችኋለሁ፣ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩም፣ በበለሲቱ እንደ ሆነባት ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ [ቆመውበት የነበረውን የደብረ ዘይት ተራራ] እንኳ:- ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት ይሆናል፤ አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ።”

ስለዚህ ኢየሱስ ዛፏ እንድትደርቅ በማድረግ በአምላክ ማመን እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ሠርቶ ማሳያ አቀረበላቸው። “የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፣ ይሆንላችሁማል” ሲል ገለጸ። በተለይ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከሚያጋጥሟቸው አስፈሪ ፈተናዎች አንጻር ሲታይ ይህ ሊማሩት የሚገባ እንዴት ያለ ጠቃሚ ትምህርት ነበር! ሆኖም የበለስ ዛፏ መድረቅ ከእምነት ጋር የሚያያዝበት ሌላም ሁኔታ ነበር።

የእስራኤል ሕዝብ ልክ እንደ በለስ ዛፏ አታላይ የሆነ መልክ ነበረው። ምንም እንኳ ሕዝቡ ከአምላክ ጋር በቃል ኪዳን የተዛመደ ቢሆንና ከውጪ ሲታይ የአምላክን ሥርዓት የሚጠብቅ ቢመስልም መልካም ፍሬ የሌለው እምነተ ቢስ ሕዝብ መሆኑን አሳይቷል። ሕዝቡ እምነት የጎደለው በመሆኑ የራሱን የአምላክን ልጅ አልቀበልም በማለት ላይ ነበር! ስለዚህ ኢየሱስ ፍሬያማ ያልሆነችውን የበለስ ዛፍ እንድትደርቅ በማድረግ ይህ ፍሬ አልባና እምነተ ቢስ የሆነ ሕዝብ በመጨረሻ ምን እንደሚደርስበት ግልጽ በሆነ መንገድ አስረድቷል።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም ገቡ፤ እንደ ልማዳቸውም ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዱና ኢየሱስ በዚያ ማስተማር ጀመረ። የካህናት አለቆቹና የሕዝቡ ሽማግሌዎች “በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?” በማለት ተፈታታኝ ጥያቄ አቀረቡለት። ይህን ጥያቄ ያቀረቡት ኢየሱስ ከዚህ ቀን በፊት በነበረው ዕለት በገንዘብ ለዋጮቹ ላይ የወሰደውን እርምጃ በአእምሯቸው ይዘው እንደሆነ አያጠራጥርም።

ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ:- “እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይን ወይስ ከሰው?”

ካህናቱና ሽማግሌዎቹ ምን ብለው እንደሚመልሱ እርስ በርሳቸው መመካከር ጀመሩ። “ከሰማይ ብንል:- እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ ከሰው ግን ብንል፣ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን” አሉ።

መሪዎቹ ምን ብለው እንደሚመልሱ ግራ ገባቸው። ስለዚህ “አናውቅም” ብለው ለኢየሱስ መለሱለት።

ኢየሱስም መልሶ “እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። ማቴዎስ 21:​19-27፤ ማርቆስ 11:​19-33፤ ሉቃስ 20:​1-8

▪ ማክሰኞ ዕለት የዋለውን ኒሳን 11 ለየት የሚያደርገው ምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ የበለስ ዛፏን በማድረቅ ምን ትምህርቶች ሰጥቷል?

▪ ኢየሱስ የፈጸማቸውን ነገሮች ያከናወነው በምን ሥልጣን እንደሆነ ጥያቄ ላቀረቡለት ሰዎች መልስ የሰጠው እንዴት ነው?