በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ ሐና ከዚያም ወደ ቀያፋ ተወሰደ

ወደ ሐና ከዚያም ወደ ቀያፋ ተወሰደ

ምዕራፍ 119

ወደ ሐና ከዚያም ወደ ቀያፋ ተወሰደ

ኢየሱስ እንደ ማንኛውም ተራ ወንጀለኛ ታስሮ ከፍተኛ ተሰሚነት ወዳለውና ቀደም ሲል ሊቀ ካህናት ወደነበረው ወደ ሐና ተወሰደ። ኢየሱስ በ12 ዓመቱ በቤተ መቅደሱ የነበሩትን የአይሁድ ሃይማኖታዊ አስተማሪዎች በጣም አስደንቋቸው በነበረ ጊዜ ሐና ሊቀ ካህናት ነበር። ከዚያ በኋላ በርከት ያሉ የሐና ልጆች ሊቀ ካህናት ሆነው አገልግለዋል፤ አሁን ደግሞ ይህን ቦታ የያዘው የሐና አማች የሆነው ቀያፋ ነው።

ኢየሱስ መጀመሪያ ወደ ሐና ቤት የተወሰደው ይህ የካህናት አለቃ በአይሁድ ሃይማኖታዊ ሕይወት ውስጥ ለረጅም ጊዜ በነበረው ከፍ ያለ ቦታ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ሐናን ለማነጋገር ወደ እሱ ቤት ጎራ ማለታቸው ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ሳንሄድሪንን ማለትም 71 አባላት ያሉትን የአይሁድ ከፍተኛ ሸንጎና የሐሰት ምሥክሮችን ለመሰብሰብ ጊዜ እንዲያገኝ ረድቶታል።

የካህናት አለቃ የሆነው ሐና አሁን ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ሆኖም ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ:- “እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብና በመቅደስ እኔ ሁልጊዜ አስተማርሁ፣ በስውርም ምንም አልተናገርሁም። ስለ ምን ትጠይቀኛለህ? ለእነርሱ የተናገርሁትን የሰሙትን ጠይቅ፤ እነሆ፣ እነዚህ እኔ የነገርሁትን ያውቃሉ።”

በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አጠገብ ቆመው ከነበሩት መኮንኖች አንዱ “ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልሳለህን?” ብሎ በጥፊ መታው።

ኢየሱስም “ክፉ ተናግሬ እንደ ሆንሁ ስለ ክፉ መስክር፤ መልካም ተናግሬ እንደ ሆንሁ ግን ስለ ምን ትመታኛለህ?” ሲል መለሰለት። ይህን የሐሳብ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ ሐና ኢየሱስን እንደታሠረ ወደ ቀያፋ ላከው።

በዚህ ወቅት የካህናት አለቆቹና የሕዝቡ ሽማግሌዎች እንዲሁም ጻፎቹ ሁሉ፣ ማለትም ጠቅላላው የሳንሄድሪን አባላት መሰብሰብ ጀምረዋል። እየተሰበሰቡ ያሉት በቀያፋ ቤት እንደሆነ ግልጽ ነው። በማለፍ በዓል ሌሊት እንዲህ ዓይነት ችሎት ማካሄድ የአይሁድን ሕግ በቀጥታ የሚጻረር ነው። ሆኖም ይህ የሃይማኖት መሪዎቹ የክፋት ዓላማቸውን ከማከናወን አላገዳቸውም።

ከሳምንታት በፊት ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ባስነሳበት ጊዜ የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ኢየሱስ መገደል እንዳለበት ተስማምተው ወስነዋል። ከሁለት ቀናት በፊት ደግሞ ረቡዕ ዕለት የሃይማኖት ባለ ሥልጣኖቹ ኢየሱስን በተንኮል ዘዴ ይዘው ለመግደል ተማክረው ነበር። እስቲ አስበው፣ ገና ችሎት ፊት ሳይቀርብ ተፈርዶበት ነበር!

አሁን በኢየሱስ ላይ የወንጀል ክስ ማቅረብ እንዲቻል የሐሰት ምሥክርነት የሚሰጡ ሰዎች ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ነው። ይሁን እንጂ እርስ በርሱ የሚስማማ ምሥክርነት የሚሰጡ ሰዎች ሊገኙ አልቻሉም። በመጨረሻ ሁለት ሰዎች ቀረቡና “እኔ ይህን በእጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፈርሰዋለሁ በሦስት ቀንም ሌላውን በእጅ ያልተሠራውን እሠራለሁ ሲል ሰማነው” ብለው ተናገሩ።

“አንዳች አትመልስምን?” ሲል ቀያፋ ጠየቀው። “እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድን ነው?” ኢየሱስ ግን ዝም አለ። በዚህ የሐሰት ክስ እንኳ ምስክሮቹ የሚናገሩት ነገር እርስ በርሱ ሊጣጣም አለመቻሉ የሳንሄድሪንን ሸንጎ የሚያዋርድ ነበር። ስለዚህ ሊቀ ካህናቱ ሌላ ዘዴ ተጠቀመ።

ቀያፋ አይሁዶች የአምላክ ልጅ ነኝ ብሎ የሚናገር ማንኛውም ሰው ምን ያህል እንደሚያስቆጣቸው ያውቅ ነበር። ቀደም ሲል በሁለት የተለያዩ ጊዜያት አይሁዶች ኢየሱስ ከአምላክ ጋር እኩል ነኝ ብሎ እንደተናገረ አድርገው በተሳሳተ መንገድ በመረዳት አምላክን ስለተሳደበ ሞት ይገባዋል ብለው ወዲያውኑ ደምድመው ነበር። አሁን ቀያፋ የተንኮል ዘዴ በመጠቀም “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ” ሲል ጠየቀው።

አይሁዶች ምንም ይምሰላቸው ምን ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ነው። ዝም ካለ ደግሞ ክርስቶስ መሆኑን እንደካደ ተደርጎ ሊተረጎምበት ይችላል። ስለዚህ ኢየሱስ በድፍረት “እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” ሲል መለሰ።

በዚህ ጊዜ ቀያፋ ተውኔት እንደሚያሳይ ሰው ልብሱን ቀደደና “ተሳድቦአል እንግዲህ ወዲህ ምስክሮች ስለ ምን ያስፈልገናል? እነሆ፣ ስድቡን አሁን ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል?” አለ።

የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት “ሞት ይገባዋል” አሉ። ከዚያም ያሾፉበትና ያንቋሽሹት ጀመር። በጥፊ መቱት፤ ምራቃቸውንም ተፉበት። ሌሎቹ ደግሞ ፊቱን በሙሉ ሸፍነው በቡጢ እየመቱ “ክርስቶስ ሆይ፣ . . . የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገርልን” እያሉ ይቀልዱበት ነበር። ይህ ሰብዓዊነት የጎደለው ሕገ ወጥ ድርጊት የተፈጸመው ሌሊት በተካሄደው ችሎት ላይ ነው። ማቴዎስ 26:​57-68፤ 26:​3, 4፤ ማርቆስ 14:​53-65፤ ሉቃስ 22:​54, 63-65፤ ዮሐንስ 18:​13-24፤ 11:​45-53፤ 10:​31-39፤ 5:​16-18

▪ ኢየሱስ መጀመሪያ የተወሰደው ወዴት ነው? እዚያስ ምን ደረሰበት?

▪ ኢየሱስ ቀጥሎ የተወሰደው ወዴት ነው? ወደዚያ የተወሰደውስ ለምን ነበር?

▪ ቀያፋ የሳንሄድሪን ሸንጎ ኢየሱስ ሞት ይገባዋል ብሎ እንዲበይን ማድረግ የቻለው እንዴት ነው?

▪ በችሎቱ ወቅት የተፈጸመው ሰብዓዊነት የጎደለው ሕገ ወጥ ድርጊት ምንድን ነው?