በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ ቅፍርናሆም ተመለሰ

ወደ ቅፍርናሆም ተመለሰ

ምዕራፍ 26

ወደ ቅፍርናሆም ተመለሰ

በዚህ ወቅት የኢየሱስ ዝና በስፋት ተሰራጭቶ ነበር። ብዙ ሰዎችም እሱ ወዳለበት ከከተማ ርቆ ወደሚገኝ ሥፍራ ይጎርፉ ነበር። ይሁን እንጂ ከጥቂት ቀናት በኋላ በገሊላ ባሕር አቋርጦ ወደ ቅፍርናሆም ተመለሰ። ወዲያውኑ ኢየሱስ ወደዚች ከተማ እንደተመለሰ የሚገልጽ ወሬ በከተማይቱ ሁሉ ተዳረሰ። ብዙ ሰዎች እሱ ወዳለበት ቤት መጡ። ከኢየሩሳሌም እንኳን ሳይቀር የመጡ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ነበሩ።

ሰዎቹ በጣም ብዙ ስለነበሩ ደጃፉን ዘጉት። ማንም ሰው ወደ ውስጥ መግባት የሚችልበት ቀዳዳ አልነበረም። ሁኔታው ለአንድ በጣም አስደናቂ የሆነ ክንውን ተመቻችቶ ነበር። በዚህ ወቅት የተፈጸመው ነገር ኢየሱስ ለሰብዓዊ መከራ መንስኤ የሆነውን ነገር የማስወገድና ለመረጣቸው ሁሉ ጤንነትን የመመለስ ኃይል እንዳለው እንድንገነዘብ የሚረዳን በመሆኑ ትልቅ ትርጉም ያዘለ ነው።

ኢየሱስ የተሰበሰቡትን ብዙ ሰዎች እያስተማረ እያለ አራት ሰዎች አንድ ሽባ የሆነ ሰው በቃሬዛ ይዘው መጡ። ኢየሱስ ጓደኛቸውን እንዲፈውስላቸው ፈልገው ነበር፤ ሆኖም ወደ ውስጥ መግባት አልቻሉም። እንዴት የሚያበሳጭ ነው! ሆኖም ሰዎቹ ተስፋ አልቆረጡም። ዝርግ ወደሆነው ጣሪያ ላይ ወጡና በሱት። ከዚያም ሽባው ቃሬዛው ላይ እንደተኛ በቀዳዳው በኩል ወደታች አውርደው ኢየሱስ አጠገብ አሳረፉት።

ኢየሱስ ንግግሩን በማቋረጣቸው ተናደደን? በፍጹም አልተናደደም! ከዚህ ይልቅ በእምነታቸው በጣም ተገረመ። ኢየሱስ ሽባውን “ኃጢአትህ ተሰረየችልህ” አለው። ይሁን እንጂ በእርግጥ ኢየሱስ ኃጢአት ሊያስተሰርይ ይችላልን? ጻፎችና ፈሪሳውያን ኢየሱስ ኃጢአት ሊያስተሰርይ አይችልም የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው። በልባቸው “ይህ ሰው ስለ ምን እንደዚህ ያለ ስድብ ይናገራል? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል?” ብለው አሰቡ።

ኢየሱስ ምን አስተሳሰብ እንዳደረባቸው አውቆ እንዲህ አላቸው:- “በልባችሁ ይህን ስለ ምን ታስባላችሁ? ሽባውን:- ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ከማለት ወይስ:- ተነሣ አልጋህንም ተሸከምና ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል?”

ከዚያም ኢየሱስ ተቺዎቹን ጨምሮ በዚያ የተሰበሰቡት ሰዎች በምድር ላይ ኃጢአት የማስተሰረይ ሥልጣን ያለው መሆኑንና በእርግጥም እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው መሆኑን የሚያሳይ አንድ አስደናቂ ሠርቶ ማሳያ አቀረበላቸው። ወደ ሽባው ዞር አለና “ተነሣ፣ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ ሰዎቹ ሁሉ እያዩ ተነሣና አልጋውን ተሸክሞ ሄደ! ሰዎቹ በመገረም “እንዲህ ያለ ከቶ አላየንም” ብለው አምላክን አከበሩ።

ኢየሱስ ኃጢአትን ከበሽታ ጋር አያይዞ እንደጠቀሰና የኃጢአት ይቅርታ አካላዊ ጤንነት ከማግኘት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ልብ ብለሃልን? መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው ወላጃችን አዳም ኃጢአት እንደሠራና ሁላችንም የኃጢአት ውጤቶች የሆኑትን በሽታንና ሞትን እንደወረስን ይገልጻል። ሆኖም በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ኢየሱስ አምላክን የሚወዱና የሚያገለግሉ ሰዎችን ኃጢአት በሙሉ ያስተሰርያል። ከዚያም በሽታ ሁሉ ይወገዳል። ይህ ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል! ማርቆስ 2:​1-12፤ ሉቃስ 5:​17-26፤ ማቴዎስ 9:​1-8፤ ሮሜ 5:​12, 17-19

▪ አንድ በጣም አስደናቂ የሆነ ክንውን ከመፈጸሙ በፊት የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

▪ ባው ኢየሱስ አጠገብ የደረሰው እንዴት ነው?

▪ ሁላችንም ኃጢአተኞች የሆንነው ለምንድን ነው? ሆኖም ኢየሱስ የኃጢአት ይቅርታና ፍጹም ጤንነት ልናገኝ እንደምንችል የሚያሳይ ተስፋ የሰጠው እንዴት ነው?