በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ ኢየሩሳሌም የተደረገ ምስጢራዊ ጉዞ

ወደ ኢየሩሳሌም የተደረገ ምስጢራዊ ጉዞ

ምዕራፍ 65

ወደ ኢየሩሳሌም የተደረገ ምስጢራዊ ጉዞ

ጊዜው በ32 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የበልግ ወራት ላይ ነው። የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር። ኢየሱስ አይሁዳውያን እሱን ለመግደል ሙከራ ካደረጉበት በ31 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ከተከበረው የማለፍ በዓል ጀምሮ ሥራው በአብዛኛው በገሊላ እንዲወሰን አድርጎ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም የሄደው ሦስቱን ዓመታዊ የአይሁድ በዓሎች ለማክበር ብቻ ሳይሆን አይቀርም።

የኢየሱስ ወንድሞች “ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ” በማለት እንዲሄድ ጎተጎቱት። ኢየሩሳሌም የይሁዳ ዋና ከተማ ከመሆኗም በላይ የመላው አገሪቱ ሃይማኖታዊ ማዕከል ነበረች። ወንድሞቹ “ራሱ ሊገለጥ እየፈለገ በስውር የሚሠራ የለም” የሚል ምክንያት አቀረቡ።

ምንም እንኳ ያዕቆብ፣ ስምዖን፣ ዮሳና ይሁዳ ታላቅ ወንድማቸው ኢየሱስ መሲሕ ነው ብለው ባያምኑበትም በበዓሉ ላይ ለሚሰበሰቡት ሁሉ ተአምራዊ ኃይሉን እንዲያሳይ ፈልገው ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሁኔታው አደገኛ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። “ዓለም እናንተን ሊጠላ አይቻለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ መሆኑን እመሠክርበታለሁና እኔን ይጠላኛል” ሲል ተናገረ። ስለዚህ ኢየሱስ ወንድሞቹን “እናንተ ወደዚህ በዓል ውጡ፤ እኔስ ጊዜዬ ገና ስላልተፈጸመ ወደዚህ በዓል ገና አልወጣም” አላቸው።

የዳስ በዓል ለሰባት ቀናት የሚከበር በዓል ነው። በዓሉ በስምንተኛው ቀን በሚከናወኑ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ይጠናቀቃል። በዓሉ የእርሻው ዓመት መገባደዱን የሚያመለክት ሲሆን ታላቅ ደስታ የሚገኝበትና ምስጋና የሚቀርብበት ጊዜ ነው። የኢየሱስ ወንድሞች በበዓሉ ላይ ለመገኘት ከዋናዎቹ ተጓዦች ጋር አብረው ከሄዱ በርከት ካሉ ቀናት በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከሕዝቡ ዓይን ተሰውረው በምስጢር ተጓዙ። የተጓዙት አብዛኞቹ ሰዎች በሚሄዱበት በዮርዳኖስ ወንዝ አቅራቢያ ባለው መንገድ ሳይሆን በሰማርያ በኩል ነበር።

ኢየሱስና አብረውት ያሉት ሰዎች በአንድ የሳምራውያን መንደር ማረፊያ ያስፈልጋቸው ስለነበረ አንዳንድ ዝግጅቶች እንዲያደርጉ አስቀድሞ መልእክተኞች ላከ። ይሁን እንጂ በዚያ የሚኖሩት ሰዎች ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄደ መሆኑን ሲያውቁ ምንም ነገር ሊያደርጉለት ፈቃደኞች አልሆኑም። ያዕቆብና ዮሐንስ በጣም ተናደው “ጌታ ሆይ! ከሰማይ እሳት ወርዶ እነዚህን ሰዎች ያቃጥላቸው ዘንድ እንድናዝዝ ትፈቅዳለህን?” ብለው ጠየቁት። (የ1980 ትርጉም) ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ሐሳብ በማቅረባቸው ወቀሳቸው። ከዚያም ወደ ሌላ መንደር ተጓዙ።

በመንገድ ላይ እየተጓዙ ሳለ አንድ ጸሐፊ ኢየሱስን “መምህር ሆይ፣ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው።

ኢየሱስም “ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፣ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም” ሲል መለሰለት። ኢየሱስ ጸሐፊው የእሱ ተከታይ ከሆነ መከራ የሚደርስበት መሆኑን መግለጹ ነበር። አባባሉ እንደሚያመለክተው ጸሐፊው በጣም ኩሩ ስለሆነ እንዲህ ዓይነቱን አኗኗር የሚቀበል አይመስልም።

ኢየሱስ አንድን ሌላ ሰው “ተከተለኝ” አለው።

ሰውየውም “አስቀድሜ ልሂድና አባቴን እቀብር ዘንድ ፍቀድልኝ” አለው።

ኢየሱስ “ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤ አንተስ ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ” ሲል መለሰለት። በወቅቱ የሰውየው አባት ገና እንዳልሞተ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል፤ አባትየው ሞቶ ቢሆን ኖሮ ልጁ ወደዚህ ቦታ መጥቶ ከኢየሱስ ጋር ሊነጋገር ባልቻለ ነበር። ልጁ አባቱ እስኪሞት ድረስ ልቆይ ብሎ መጠየቁ ይመስላል። የአምላክን መንግሥት በሕይወቱ ውስጥ ለማስቀደም አልተዘጋጀም።

ወደ ኢየሩሳሌም የሚያደርጉትን ጉዞ ሲቀጥሉ አንድ ሌላ ሰው ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፣ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን አስቀድሜ ከቤቴ ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ” አለው።

ኢየሱስም መልሶ “ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም” አለው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሚሆኑ ሰዎች ዓይኖቻቸው በመንግሥቱ አገልግሎት ላይ እንዲተከሉ ማድረግ አለባቸው። አንድ አራሽ ገበሬ ቀጥ ብሎ ወደፊት የማያይ ከሆነ ትልሙ እንደሚጣመም ሁሉ ወደ ኋላ ዞሮ ይህን አሮጌ የነገሮች ሥርዓት የሚመለከት ማንኛውም ሰው ተደናቅፎ ወደ ዘላለም ሕይወት ከሚወስደው መንገድ ሊወጣ ይችላል። ዮሐንስ 7:​2-10፤ ሉቃስ 9:​51-62፤ ማቴዎስ 8:​19-22

▪ የኢየሱስ ወንድሞች እነማን ናቸው? ስለ እሱስ ምን አመለካከት ነበራቸው?

▪ ሳምራውያን አክብሮት የጎደለው ተግባር የፈጸሙት ለምንድን ነው? ያዕቆብና ዮሐንስ ምን ማድረግ ፈልገው ነበር?

▪ ኢየሱስ በመንገድ ላይ ያደረጋቸው ሦስት ውይይቶች ምንድን ናቸው? የራስን ጥቅም በመሠዋት የማገልገልን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ የገለጸውስ እንዴት ነው?