በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ ኢየሩሳሌም የተደረጉ ጉዞዎች

ወደ ኢየሩሳሌም የተደረጉ ጉዞዎች

ምዕራፍ 10

ወደ ኢየሩሳሌም የተደረጉ ጉዞዎች

የጸደይ ወቅት ደረሰ። የዮሴፍ ቤተሰብ የማለፍን በዓል ለማክበር ከጓደኞቻቸውና ከዘመዶቻቸው ጋር ሆነው በየዓመቱ በጸደይ ወራት ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ የሚያደርጉበት ጊዜ ደርሶ ነበር። ወደ 100 ኪሎ ሜትር የሚጠጋውን መንገድ ሲያያዙት የተለመደው ደስታ ይሰማቸው ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ 12 ዓመት ሆኖት ነበር፤ በዓሉንም በልዩ ስሜት በመጠባበቅ ላይ ነበር።

ለኢየሱስና ለቤተሰቡ የማለፍ በዓል የአንድ ቀን ጉዳይ አልነበረም። የማለፍ በዓሉ ክፍል አድርገው ይመለከቱት የነበረውን ያልቦካ ቂጣ በዓልንም ለማክበር ለቀጣዮቹ ሰባት ቀናት እዚያው ይቆዩ ነበር። ስለዚህ ናዝሬት ከሚገኘው መኖሪያቸው ተነስተው የሚያደርጉት ጉዞ ኢየሩሳሌም የሚቆዩባቸውን ቀናት ጨምሮ ሁለት ሳምንት ገደማ ይወስድ ነበር። ሆኖም በዚህ ዓመት ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ አንድ ሁኔታ ምክንያት ከዚህ የበለጠ ጊዜ ወስዶባቸዋል።

ችግሩ የታወቀው ከኢየሩሳሌም እየተመለሱ በነበረበት ወቅት ነው። ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስ አብረዋቸው ይጓዙ ከነበሩት ዘመዶቻቸውና ወዳጆቻቸው ጋር ያለ መስሏቸው ነበር። ሆኖም ማታ ከጉዞአቸው ሲያርፉ ኢየሱስ የለም። አብረዋቸው ይጓዙ በነበሩት ሰዎች መካከል ፈለጉት። ሆኖም ፈጽሞ ሊያገኙት አልቻሉም። ስለዚህ ዮሴፍና ማርያም እሱን ለመፈለግ እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

ቀኑን ሙሉ ቢፈልጉትም ሊያገኙት አልቻሉም። በሁለተኛውም ቀን አላገኙትም። በመጨረሻ በሦስተኛው ቀን ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዱ። እዚያም በአንዱ አዳራሽ ውስጥ በአይሁድ አስተማሪዎች መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውና ሲጠይቃቸው አገኙት።

“ልጄ ሆይ፣ ለምን እንዲህ አደረግህብን?” ስትል ማርያም ጠየቀችው። “እነሆ፣ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን አለችው።”

ኢየሱስ የት ሊያገኙት እንደሚችሉ ባለማወቃቸው ተገረመ። “ስለ ምን ፈለጋችሁኝ?” ሲል ጠየቃቸው። “በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን? አላቸው።”

ኢየሱስ ወላጆቹ ለምን ይህን እንዳላወቁ ሊገባው አልቻለም። ከዚያም ኢየሱስ ከወላጆቹ ጋር ወደ ቤት ተመለሰ፤ እንደ ቀድሞውም ይታዘዝላቸው ነበር። በአምላክና በሰው ፊት በጥበብና በቁመት በሞገስም እያደገ ሄደ። አዎን፣ ኢየሱስ ከልጅነቱ ጀምሮ መንፈሳዊ ነገሮችን በመከታተል ብቻ ሳይሆን ለወላጆቹ አክብሮት በማሳየትም ጥሩ ምሳሌ ትቷል። ሉቃስ 2:​40-52፤ 22:​7

▪ ኢየሱስ በጸደይ ወራት ዘወትር ከቤተሰቡ ጋር ምን ጉዞ ያደርግ ነበር? ጉዞውስ ምን ያህል ረጅም ነበር?

▪ ኢየሱስ 12 ዓመት ሲሆነው ባደረጉት ጉዞ ምን ነገር ተከስቶ ነበር?

▪ ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ላሉት ወጣቶች ምን ምሳሌ ትቷል?