በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓርብ ተቀበረ፤ እሁድ መቃብሩ ባዶ ሆኖ ተገኘ

ዓርብ ተቀበረ፤ እሁድ መቃብሩ ባዶ ሆኖ ተገኘ

ምዕራፍ 127

ዓርብ ተቀበረ፤ እሁድ መቃብሩ ባዶ ሆኖ ተገኘ

ጊዜው ዓርብ አመሻሹ ላይ ነው፤ ኒሳን 15 ላይ የሚውለው ሰንበት ደግሞ ልክ ፀሐይ ስትጠልቅ ይጀምራል። የኢየሱስ አስከሬን ዝልፍልፍ ብሎ እንጨቱ ላይ ተንጠልጥሏል፤ በጎኑ የተሰቀሉት ሁለቱ ዘራፊዎች ግን አሁንም በሕይወት አሉ። ዓርብ ከሰዓት በኋላ የማዘጋጀት ቀን ተብሎ ይጠራ ነበር፤ ምክንያቱም ሰዎች ምግብ የሚያዘጋጁትና ሰንበት እስኪያልፍ ድረስ ሊቆዩ የማይችሉትን ሌሎች አጣዳፊ ሥራዎች የሚያጠናቅቁበት ጊዜ ስለነበረ ነው።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሚጀምረው ሰንበት መደበኛ ሰንበት (የሳምንቱ ሰባተኛ ቀን) ብቻ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ ድርብ ወይም “ታላቅ” ሰንበትም ነበር። ይህን መጠሪያ ሊያገኝ የቻለው ለሰባት ቀን የሚከበረው ያልቦካ ቂጣ በዓል የመጀመሪያ ቀን የሆነው ኒሳን 15 (ይህ ዕለት በየትኛውም የሳምንቱ ቀን ላይ ቢውል ምንጊዜም ሰንበት ነው) መደበኛው ሰንበት በሚከበርበት ቀን ላይ ስለዋለ ነው።

በአምላክ ሕግ መሠረት አስከሬኖች በእንጨት ላይ ተሰቅለው ማደር የለባቸውም። ስለዚህ አይሁዶች ጲላጦስ ፊት ቀረቡና የተሰቀሉት ሰዎች ጭናቸው ተሰብሮ ሞታቸው እንዲፋጠን ይደረግ ዘንድ ጠየቁት። ስለዚህ ወታደሮቹ የሁለቱን ዘራፊዎች ጭን ሰበሩ። ሆኖም ኢየሱስ ሞቶ ስለነበረ የሱን ጭን አልሰበሩም። ይህ “ከእርሱ አጥንት አይሰበርም” የሚለው ጥቅስ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርጓል።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንደሞተ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ለመሆን ከወታደሮቹ አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው። ጦሩ ልቡ አካባቢ በስቶ ገባና ወዲያውኑ ደምና ውኃ ወጣ። የዓይን ምሥክር የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ ይህ ድርጊት “የወጉትን ያዩታል” የሚለው ሌላ ጥቅስ እንዲፈጸም ያደረገ መሆኑን ገልጿል።

የተከበረ የሳንሄድሪን አባል የነበረው የአርማትያሱ ዮሴፍም ግድያው በተፈጸመበት ቦታ ነበር። ከፍተኛው ፍርድ ቤት በኢየሱስ ላይ የወሰደውን ፍትሃዊ ያልሆነ ድርጊት ደግፎ ድምፅ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም። ዮሴፍ ምንም እንኳ ባደረበት ፍርሃት ምክንያት ማንነቱን በግልጽ ባያሳውቅም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበር። አሁን ግን ድፍረት በማሳየት የኢየሱስን አስከሬን እንዲሰጠው ጲላጦስን ጠየቀው። ጲላጦስ ግድያውን እንዲያስፈጽም ኃላፊነት ተሰጥቶት የነበረውን መቶ አለቃ አስጠርቶ ኢየሱስ መሞቱን ካረጋገጠ በኋላ አስከሬኑን አሳልፎ ሰጠው።

ዮሴፍ አስከሬኑን ወሰደና በንጹሕ ጨርቅ ከፈነው። የሳንሄድሪን አባል የሆነው ኒቆዲሞስም ረድቶታል። ኒቆዲሞስም ሥልጣኑን እንዳያጣ ስለሰጋ በኢየሱስ ላይ ያለውን እምነት አልገለጠም ነበር። አሁን ግን 33 ኪሎ ግራም የሚመዝን የከርቤና በጣም ውድ የሆነ እሬት ቅልቅል አመጣ። የኢየሱስን አስከሬን እነዚህን ቅመሞች በያዙ ጨርቆች በመጠቅለል በአይሁዳውያን የአገናነዝ ልማድ ገነዙት።

ከዚያም አስከሬኑ በአቅራቢያው በሚገኝ የአትክልት ሥፍራ ዮሴፍ ባዘጋጀው ከዓለት ተወቅሮ በተሠራ አዲስ መቃብር ውስጥ ተቀበረ። በመጨረሻም አንድ ትልቅ ድንጋይ አንከባለው መቃብሩን ዘጉት። አስከሬኑን ከሰንበት ቀን በፊት ለመቅበር ሲባል ዝግጅቱ የተከናወነው በጥድፊያ ነበር። ስለዚህ መግደላዊት ማርያምና የታናሹ ያዕቆብ እናት የሆነችው ማርያም ተጨማሪ ቅመሞችና ሽቶ ለማዘጋጀት በፍጥነት ወደ ቤት ሄዱ። እነዚህ ሴቶች አስከሬኑን ለመቅበር ዝግጅት ሲደረግ አስተዋጽኦ ሳያበረክቱ አይቀሩም። የኢየሱስ አስከሬን ረዘም ላለ ጊዜ ተጠብቆ መቆየት እንዲችል ከሰንበት ቀን በኋላ ተጨማሪ ሽቶና ቅባት ለመቀባት አቅደው ነበር።

በሚቀጥለው ቀን ማለትም ቅዳሜ (በሰንበት ቀን) የካህናት አለቆቹና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ሄዱና እንዲህ አሉት:- “ጌታ ሆይ፣ ያ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ:- ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን። እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም:- ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ፣ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ።”

ጲላጦስ “ጠባቆች አሉአችሁ” ሲል መለሰላቸው። “ሄዳችሁ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ” አላቸው። ስለዚህ ሄደው ድንጋዩን በማተምና ሮማውያን ወታደሮችን በቦታው ዘብ በማቆም መቃብሩ እንዲጠበቅ አደረጉ።

እሁድ ጠዋት ማለዳ ላይ መግደላዊት ማርያምና የያዕቆብ እናት ማርያም ከሰሎሜ፣ ከዮሐናና ከሌሎች ሴቶች ጋር ሆነው የኢየሱስን አስከሬን ለመቀባት ሽቶ ይዘው መጡ። ሲመጡ መንገድ ላይ እርስ በርሳቸው “ድንጋዩን ከመቃብር ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል?” ይባባሉ ነበር። ሆኖም መቃብሩ ወዳለበት ቦታ ሲደርሱ የምድር ነውጥ ተከስቶና የይሖዋ መልአክ ድንጋዩን አንከባሎት ነበር። ጠባቂዎቹ ሄደዋል፤ መቃብሩም ባዶ ሆኗል! ማቴዎስ 27:​57 እስከ 28:​2፤ ማርቆስ 15:​42 እስከ 16:​4፤ ሉቃስ 23:​50 እስከ 24:​3, 10፤ ዮሐንስ 19:​14, ዮሐንስ 19:31 እስከ 20:​1፤ 12:​42፤ ዘሌዋውያን 23:​5-7፤ ዘዳግም 21:​22, 23፤ መዝሙር 34:​20፤ ዘካርያስ 12:​10

▪ ዓርብ የማዘጋጀት ቀን የተባለው ለምንድን ነው? “ታላቁ” ሰንበት ምንድን ነው?

▪ ከኢየሱስ አስከሬን ጋር በተያያዘ የትኞቹ ጥቅሶች ተፈጽመዋል?

▪ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከኢየሱስ ቀብር ጋር በተያያዘ ምን ነገር አከናውነዋል? ከኢየሱስ ጋር የነበራቸው ዝምድናስ ምንድን ነው?

▪ ካህናቱ ለጲላጦስ ምን ጥያቄ አቀረቡ? እሱስ ምን ምላሽ ሰጠ?

▪ እሁድ ጠዋት ማለዳ ላይ ምን ተፈጸመ?