በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደ ሰው መፈወስ

ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደ ሰው መፈወስ

ምዕራፍ 70

ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደ ሰው መፈወስ

አይሁዶች ኢየሱስን ለመውገር ሲሞክሩ ኢየሱስ ኢየሩሳሌምን ለቅቆ አልወጣም። ይህ ከሆነ በኋላ በሰንበት ቀን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በከተማይቱ ውስጥ ሲጓዙ ከተወለደ ጀምሮ ዓይነ ስውር የሆነ አንድ ሰው ተመለከቱ። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን “መምህር ሆይ፣ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ወይስ ወላጆቹ?” ብለው ጠየቁት።

ምናልባት ደቀ መዛሙርቱ አንዳንድ ረቢዎች እንደሚያምኑት አንድ ሰው በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሳለ ኃጢአት ሊሠራ ይችላል የሚል እምነት ኖሯቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ “የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም” ሲል መለሰላቸው። ሰውየው ዓይነ ስውር የሆነው እሱ ወይም ወላጆቹ የሆነ ስህተት ወይም ኃጢአት በመፈጸማቸው አይደለም። የመጀመሪያው ሰው አዳም የሠራው ኃጢአት ሁሉንም ሰዎች ፍጽምና አሳጥቷቸዋል፤ በመሆኑም ሰዎች ዓይነ ስውር ሆኖ መወለድን ለመሳሰሉ ጉድለቶች የተጋለጡ ሆነዋል። ይህ በሰውየው ላይ የተከሰተው ጉድለት አሁን ኢየሱስ የአምላክን ሥራዎች ለመግለጥ የሚያስችል አጋጣሚ ከፍቶለታል።

ኢየሱስ እነዚህን ሥራዎች የማከናወኑን አጣዳፊነት ጎላ አድርጎ ገልጾታል። “ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤” አለ። “ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች። በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ።” በቅርቡ ሞት ኢየሱስን ምንም ማድረግ ወደማይችልበት የመቃብር ጨለማ ውስጥ ሊከተው ነው። እስከዚያው ድረስ ግን ለዓለም የብርሃን ምንጭ ነው።

ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ ምራቁን መሬት ላይ ተፋና ትንሽ ጭቃ አቦካ። ጭቃውንም በዓይነ ስውሩ ዓይኖች ላይ ቀባውና “ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ አለው።” ሰውየው የታዘዘውን አደረገ። ሄዶ ሲታጠብ ማየት ቻለ! በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ማየት ችሎ ሲመለስ ምንኛ ተደስቶ ይሆን!

ጎረቤቶቹና የሚያውቁት ሰዎች በጣም ተገረሙ። “ይህ ተቀምጦ ይለምን የነበረ አይደለምን?” ሲሉ ጠየቁ። አንዳንዶቹ “እርሱ ነው” አሉ። ሌሎቹ ግን ሊያምኑ አልቻሉም:- “አይደለም እርሱን ይመስላል እንጂ” አሉ። ሆኖም ሰውየው “እኔ ነኝ” አለ።

ሰዎቹ “ታድያ:- ዓይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” ብለው ጠየቁት።

“ኢየሱስ የሚባለው ሰው ጭቃ አድርጎ ዓይኖቼን ቀባና:- ወደ ሰሊሆም መጠመቂያ ሄደህ ታጠብ አለኝ፤ ሄጄ ታጥቤም አየሁ አለ።”

“ያ ሰው ወዴት ነው?” ብለው ጠየቁት።

“አላውቅም” ብሎ መለሰላቸው።

ሰዎቹ ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው የሃይማኖት መሪዎቻቸው ወደሆኑት ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። እነርሱም እንዴት ማየት እንደቻለ ጠየቁት። ሰውየውም “ጭቃ በዓይኖቼ አኖረ ታጠብሁም አያለሁም” በማለት ገለጸላቸው።

ፈሪሳውያን ከተፈወሰው ለማኝ ጋር አብረው መደሰት ይገባቸው ነበር! ሆኖም በዚያ ፋንታ ኢየሱስን አወገዙት። ‘ይህ ሰው ከእግዚአብሔር አይደለም’ አሉ። እንደዚህ ያሉት ለምንድን ነው? “ሰንበትን አያከብርም” በሚል ምክንያት ነበር። ሆኖም ሌሎች ፈሪሳውያን በነገሩ ተገርመው “ኃጢአተኛ ሰው እንደነዚህ ያሉ ምልክቶች ሊያደርግ እንዴት ይችላል?” አሉ። ስለዚህ በመካከላቸው ልዩነት ተፈጠረ።

ስለዚህ ሰውየውን “አንተ ዓይኖችህን ስለ ከፈተ ስለ እርሱ ምን ትላለህ?” ብለው ጠየቁት።

“ነቢይ ነው” ብሎ መለሰ።

ፈሪሳውያን ይህን ለማመን አልፈለጉም። ይህ ሰውና ኢየሱስ ሰዉን ለማታለል የዶለቱት አንድ ነገር መኖር አለበት የሚል እምነት አድሮባቸዋል። ስለዚህ አንድ እልባት ላይ ለመድረስ ሲሉ ይለምን የነበረውን ሰው ወላጆች ለመጠየቅ አስጠሯቸው። ዮሐንስ 8:​59፤ 9:​1-18

▪ ሰውየው ዓይነ ስውር ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው? ለዚህ ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ የማይችለውስ ነገር ምንድን ነው?

▪ ማንም ሰው ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ምንድን ነው?

▪ ሰውየው ሲፈወስ የሚያውቁት ሰዎች ምን ምላሽ አሳዩ?

▪ የሰውየው መፈወስ በፈሪሳውያን መካከል መከፋፈል የፈጠረው እንዴት ነው?