በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የልደት ቀን ሲከበር የተፈጸመ ነፍስ ግድያ

የልደት ቀን ሲከበር የተፈጸመ ነፍስ ግድያ

ምዕራፍ 51

የልደት ቀን ሲከበር የተፈጸመ ነፍስ ግድያ

ኢየሱስ ለሐዋርያቱ መመሪያ ከሰጣቸው በኋላ ሁለት ሁለት አድርጎ ወደ ክልሉ ላካቸው። ምናልባት ወንድማማች የሆኑት ጴጥሮስና እንድርያስ አንድ ላይ ሄደው ይሆናል፤ ልክ እንደዚሁም ያዕቆብና ዮሐንስ፣ ፊልጶስና በርተሎሜዎስ፣ ቶማስና ማቴዎስ፣ ያዕቆብና ታዴዎስ እንዲሁም ስምዖንና የአስቆሮቱ ይሁዳ ጥንድ ጥንድ ሆነው ሄደው ይሆናል። ስድስቱ ጥንድ ወንጌላውያን በሄዱበት ሁሉ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከማወጃቸውም በላይ ተአምራዊ ፈውስ ፈጽመዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አጥማቂው ዮሐንስ አሁንም በእስር ላይ ነበር። ከታሰረ አሁን ሁለት ዓመት ገደማ ሆኖታል። ሄሮድስ አንቲጳስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን የራሱ ሚስት አድርጎ በመውሰዱ ዮሐንስ በሕዝብ ፊት እንዳወገዘው ታስታውስ ይሆናል። ሄሮድስ አንቲጳስ የሙሴን ሕግ አከብራለሁ የሚል ሰው ስለነበረ ዮሐንስ ይህን የምንዝር ጋብቻ ማጋለጡ ተገቢ ነበር። ስለዚህ ሄሮድስ ዮሐንስን ወኅኒ አወረደው፤ ምናልባትም ይህን ያደረገው በሄሮድያዳ ውትወታ ሊሆን ይችላል።

ሄሮድስ አንቲጳስ ዮሐንስ ጻድቅ ሰው መሆኑን ከመገንዘቡም በላይ የሚናገረውን መስማት ያስደስተው ነበር። ስለዚህ ምን እንደሚያደርገው ግራ ገብቶታል። በሌላ በኩል ደግሞ ሄሮድያዳ ዮሐንስን ስለምትጠላው እሱን የምታስገድልበትን መንገድ ትፈልግ ነበር። በመጨረሻ ስትጠብቀው የነበረውን አጋጣሚ አገኘች።

ሄሮድስ በ32 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ከተከበረው የማለፍ በዓል ጥቂት ቀደም ብሎ የልደት ቀኑን ለማክበር አንድ ትልቅ ድግስ አዘጋጀ። የሄሮድስ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የጦር ሹማምንት እንዲሁም የታወቁ የገሊላ ሰዎች በድግሱ ላይ ተገኝተው ነበር። ጊዜው እየመሸ ሲሄድ ሄሮድያዳ ከቀድሞ ባሏ ከፊልጶስ የወለደቻት ሰሎሜ የተባለችው ልጅዋ በእንግዶቹ ፊት እንድትዘፍን ተላከች። ይመለከቷት የነበሩት ወንዶች በውዝዋዜዋ ተማረኩ።

ሄሮድስ በሰሎሜ እጅግ ተደሰተ። “የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ እሰጥሽማለሁ አላት።” እንዲያውም “የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትለምኚውን ሁሉ እሰጥሻለሁ ብሎ ማለላት።”

ሰሎሜ መልስ ከመስጠቷ በፊት ሄዳ እናቷን አማከረች። “ምን ልለምነው?” ብላ ጠየቀቻት።

በመጨረሻ ስትጠብቀው የነበረውን አጋጣሚ አገኘች! ሄሮድያዳ ምንም ሳታመነታ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ” አለቻት።

ሰሎሜ ወዲያውኑ ወደ ሄሮድስ ተመልሳ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን ልትሰጠኝ እወዳለሁ” ብላ ለመነችው።

ሄሮድስ በጣም ተጨነቀ። ሆኖም ይህ አንድን ንጹሕ ሰው መግደል ማለት ቢሆንም እንኳ መሐላውን እንግዶቹ ሰምተውት ስለነበረ እንዳይከለክላት አፈረ። አንድ የሞት ፍርድ አስፈጻሚ የሄሮድስን ዘግናኝ መመሪያ ተቀብሎ በፍጥነት ሄደ። ብዙም ሳይቆይ የዮሐንስን ራስ በወጭት ይዞ መጣና ለሰሎሜ ሰጣት። እሷም ይዛ ሄደችና ለእናቷ ሰጠቻት። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት የተፈጸመውን ሁኔታ ሲሰሙ መጡና አስከሬኑን ወስደው ቀበሩት፤ ከዚያም የተፈጸመውን ነገር ለኢየሱስ ነገሩት።

ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ሰዎችን እየፈወሰና አጋንንትን እያወጣ መሆኑን ሄሮድስ ሲሰማ ዮሐንስ ከሞት እንደተነሣና ኢየሱስ የተባለው እሱ እንደሆነ አድርጎ በማሰብ ፍርሃት አደረበት። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስን ለማየት በጣም ይፈልግ ነበር። ዓላማው ግን ስብከቱን ለመስማት ሳይሆን ጥርጣሬው ትክክል መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ነበር። ማቴዎስ 10:​1-5፤ 11:​1፤ 14:​1-12፤ ማርቆስ 6:​14-29፤ ሉቃስ 9:​7-9

▪ ዮሐንስ የታሰረው ለምንድን ነው? ሄሮድስ ሊገድለው ያልፈለገው ለምን ነበር?

▪ ሄሮድያዳ በመጨረሻ ዮሐንስ እንዲገደል ማድረግ የቻለችው እንዴት ነው?

▪ ዮሐንስ ከሞተ በኋላ ሄሮድስ ኢየሱስን ማየት የፈለገው ለምንድን ነው?