በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጀመሪያው የኢየሱስ ተአምር

የመጀመሪያው የኢየሱስ ተአምር

ምዕራፍ 15

የመጀመሪያው የኢየሱስ ተአምር

እንድርያስ፣ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ፣ ፊልጶስ፣ ናትናኤልና ምናልባትም ያዕቆብ የኢየሱስ የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርት ከሆኑ ገና አንድ ወይም ሁለት ቀን ቢሆናቸው ነው። አሁን የሁሉም የትውልድ አገር ወደሆነችው የገሊላ አውራጃ እየተጓዙ ነው። የናትናኤል የትውልድ ከተማ ወደሆነችው ወደ ቃና በመሄድ ላይ ናቸው። ቃና ኢየሱስ ካደገባት ከናዝሬት ብዙም ሳትርቅ በኮረብታማ ሥፍራ ላይ የምትገኝ ከተማ ነች። ቃና ውስጥ በአንድ የሠርግ ድግስ ላይ እንዲገኙ ተጋብዘዋል።

የኢየሱስ እናትም ወደ ሠርጉ መጥታለች። ማርያም ልጃቸውን የሚድሩት ቤተሰቦች ወዳጅ በመሆኗ ወደ ሠርጉ የተጠሩትን ብዙ እንግዶች በማስተናገድ ላይ የነበረች ይመስላል። ስለዚህ እጥረት መኖሩን ወዲያው በማስተዋል “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” ብላ ለኢየሱስ ነገረችው።

ማርያም የወይን ጠጅ እጥረት በመፈጠሩ ኢየሱስ አንድ ነገር እንዲያደርግ መጠቆሟ ነበር። ኢየሱስ መጀመሪያ ላይ አቅማምቶ ነበር። “ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?” ሲል ጠየቃት። በአምላክ የተሾመ ንጉሥ እንደ መሆኑ መጠን ቤተሰቡ ወይም ጓደኞቹ ለሥራው አመራር ሊሰጡት አይችሉም። ስለዚህ ማርያም የጥበብ እርምጃ በመውሰድ ጉዳዩን ለልጅዋ ተወችና አገልጋዮቹን “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው።

እያንዳንዳቸው አርባ ሊትር ያህል ሊይዙ የሚችሉ ስድስት ትልልቅ የድንጋይ ጋኖች ነበሩ። ኢየሱስ እንግዶችን ለሚያስተናግዱት ሰዎች “ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው” አላቸው። አስተናጋጆቹም ጋኖቹን እስከ አፋቸው ድረስ ሞሏ⁠ቸው። ከዚ⁠ያም ኢየሱስ “አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት” አላቸው።

አሳዳሪው በወይን ጠጁ ጣዕምና ጥራት በጣም ተደነቀ። ተአምራዊ በሆነ መንገድ የተገኘ መሆኑን አላወቀም ነበር። ሙሽራውን ጠርቶ “ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፣ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል” አለው።

ይህ የመጀመሪያው የኢየሱስ ተአምር ነበር። አዲሶቹ ደቀ መዛሙርት ይህን ሲያዩ እምነታቸው ጠነከረ። ከዚያ በኋላ ከእናቱና ከግማሽ ወንድሞቹ ጋር ሆነው ከገሊላ ባሕር አጠገብ ወደምትገኘው ወደ ቅፍርናሆም ተጓዙ። ዮሐንስ 2:​1-12

▪ የቃናው ሠርግ የተከናወነው በየትኛው የኢየሱስ አገልግሎት ወቅት ላይ ነበር?

▪ ኢየሱስ የእናቱን ሐሳብ የተቃወመው ለምን ነበር?

▪ ኢየሱስ ምን ተአምር ፈጸመ? ይህስ በሌሎች ላይ ምን ውጤት አስከትሏል?