በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት

የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት

ምዕራፍ 14

የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት

ኢየሱስ ለ40 ቀናት በምድረ በዳ ከቆየ በኋላ ቀደም ሲል ወዳጠመቀው ወደ ዮሐንስ ተመልሶ ሄደ። ኢየሱስ እየቀረበ ሲመጣ ዮሐንስ ምናልባትም በእጁ እያመለከተ አብረውት ለነበሩት ሰዎች እንዲህ አለ:- “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፣ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው።” ምንም እንኳ ዮሐንስ የአክስቱ ልጅ ከሆነው ከኢየሱስ በዕድሜ የሚበልጥ ቢሆንም ኢየሱስ ከእሱ በፊት መንፈሳዊ አካል ሆኖ በሰማይ ይኖር እንደነበር ያውቃል።

ሆኖም፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኢየሱስ ሊጠመቅ ወደእሱ ሲመጣ ዮሐንስ መሲሕ የሚሆነው ኢየሱስ መሆኑን በእርግጠኝነት ያውቅ የነበረ አይመስልም። “እኔም አላውቀውም ነበር” ሲል ዮሐንስ ገልጿል፤ “ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ” አለ።

ዮሐንስ ንግግሩን በመቀጠል ኢየሱስ ሲጠመቅ የተፈጸመውን ሁኔታ ያዳምጡት ለነበሩት ሰዎች እንዲህ ሲል ገለጸ:- “መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ። እኔም አላውቀውም ነበር፣ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ:- መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፣ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ።”

በነጋታው ዮሐንስ ከሁለት ደቀ መዛሙርቱ ጋር ቆሞ ነበር። አሁንም ኢየሱስ ወደነሱ እየቀረበ ሲመጣ ዮሐንስ “እነሆ የእግዚአብሔር በግ” አለ። በዚህ ጊዜ እነዚህ ሁለቱ የአጥማቂው ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን ተከተሉት። አንደኛው እንድርያስ ነበር፤ ሁለተኛው ደግሞ እነዚህን ነገሮች የመዘገበው ሰው ራሱ እንደሆነ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። የእሱም ስም ዮሐንስ ነው። ሁኔታዎቹ እንደሚያመለክቱት ይኸኛውም ዮሐንስ የኢየሱስ የአክስት ልጅ ነው። የማርያም እህት የሆነችው የሰሎሜ ልጅ ሳይሆን አይቀርም።

ኢየሱስ ወደ ኋላ ዞር ብሎ እንድርያስና ዮሐንስ ሲከተሉት ተመለከተና “ምን ትፈልጋላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

“ረቢ፣ ወዴት ትኖራለህ?” ሲሉ ጠየቁት።

ኢየሱስም “መጥታችሁ እዩ” አላቸው።

ጊዜው ከቀትር በኋላ አሥር ሰዓት ገደማ ላይ ነበር። እንድርያስና ዮሐንስ የቀረውን ጊዜ ከኢየሱስ ጋር አሳለፉ። ከዚያም እንድርያስ በጣም ስለተደሰተ ጴጥሮስ የሚባለውን ወንድሙን ለማግኘት ሮጦ ሄደ። “መሢሕን አግኝተናል” አለው። ጴጥሮስንም ኢየሱስ ዘንድ ወሰደው። ዮሐንስም በዚሁ ጊዜ ወንድሙን ያዕቆብን አግኝቶ ወደ ኢየሱስ ሳያመጣው አይቀርም። ሆኖም ዮሐንስ በሌሎች ቦታዎችም ላይ እንደሚያደርገው እሱን በግል የሚመለከተውን ይህን ማብራሪያ በወንጌሉ ውስጥ አላሰፈረውም።

በሚቀጥለው ቀን ኢየሱስ ፊልጶስ የተባለውን የቤተ ሳይዳ ሰው አገኘው። ቤተ ሳይዳ የእንድርያስና የጴጥሮስም የትውልድ ከተማ ነች። ኢየሱስ ፊልጶስን “ተከተለኝ” የሚል ግብዣ አቀረበለት።

ከዚያም ፊልጶስ በርተሎሜዎስ ተብሎም የሚጠራውን ናትናኤልን አገኘውና “ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል” አለው። ናትናኤል ተጠራጠረ። “ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን?” ሲል ጠየቀው።

ፊልጶስ “መጥተህ እይ” አለው። ወደ ኢየሱስ እየመጡ ሳለ ኢየሱስ ናትናኤልን አስመልክቶ “ተንኮል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ አለ።”

“ከወዴት ታውቀኛለህ?” ሲል ናትናኤል ጠየቀው።

ኢየሱስም “ፊልጶስ ሳይጠራህ፣ ከበለስ በታች ሳለህ፣ አየሁህ” አለው።

ናትናኤል ተገረመ። “መምህር ሆይ፣ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለው።

“ከበለስ በታች አየሁህ ስላልሁህ አመንህን?” ሲል ኢየሱስ ጠየቀው። “ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ” አለው። ከዚያም “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” ሲል ቃል ገባላቸው።

ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ ከአዳዲሶቹ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ከዮርዳኖስ ሸለቆ ተነስቶ ወደ ገሊላ ተጓዘ። ዮሐንስ 1:​29-51

▪ የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እነማን ናቸው?

▪ ጴጥሮስና ምናልባትም ያዕቆብ ከኢየሱስ ጋር የተዋወቁት እንዴት ነው?

▪ ናትናኤል፣ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ነው ብሎ እንዲያምን ያደረገው ምንድን ነው?