በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጨረሻዎቹ ቀኖች ምልክት

የመጨረሻዎቹ ቀኖች ምልክት

ምዕራፍ 111

የመጨረሻዎቹ ቀኖች ምልክት

አሁን ጊዜው ማክሰኞ ከቀትር በኋላ ነው። ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ቤተ መቅደሱን ቁልቁል እየተመለከተ ሳለ ጴጥሮስ፣ እንድርያስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ብቻቸውን ሆነው ወደ እርሱ መጡ። ከጥቂት ጊዜ በፊት ኢየሱስ በዚህ ሥፍራ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም በማለት ተንብዮ ስለነበረ የቤተ መቅደሱ ሁኔታ አሳስቧቸዋል።

ሆኖም ወደ ኢየሱስ ሲመጡ ሌላም ጉዳይ በአእምሯቸው ይዘው የነበረ ይመስላል። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ‘የሰው ልጅ ስለሚገለጥበት’ ወቅት ማለትም ስለ ‘መገኘቱ’ ተናግሮ ነበር። ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ ‘ስለ ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ ነግሯቸው ነበር። ስለዚህ ሐዋርያቱ ከፍተኛ የሆነ የማወቅ ጉጉት አድሮባቸዋል።

“ንገረን እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ? [ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ የሚጠፉበት ማለት ነው] የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምን ይሆናል?” ብለው ጠየቁት። (NW) ጥያቄያቸው ሦስት ክፍል ያለው ነው ማለት ይቻላል። በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ ቤተ መቅደሷ ፍጻሜ፣ ከዚያም ኢየሱስ በመንግሥቱ ሥልጣን ስለመገኘቱና በመጨረሻ ደግሞ ስለ ጠቅላላው የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ማወቅ ፈልገዋል።

ኢየሱስ ረጅም በሆነው መልሱ ለሦስቱም የጥያቄው ክፍሎች ምላሽ ሰጥቷል። የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት የሚያበቃበትን ጊዜ የሚጠቁም ምልክት ሰጥቷል፤ ሆኖም ሌላ ተጨማሪ ምልክትም ሰጥቷል። ወደፊት የሚኖሩት ደቀ መዛሙርቱ በሥልጣኑ ላይ በተገኘበትና ጠቅላላው የነገሮች ሥርዓት የሚያከትምበት ጊዜ በተቃረበበት ወቅት ላይ የሚኖሩ መሆናቸውን እንዲያውቁ የሚያስችል ምልክት ሰጥቷል።

ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ሐዋርያቱ የኢየሱስን ትንቢት ፍጻሜ ተመልክተዋል። አዎን፣ ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገራቸው ነገሮች በእነርሱ ዘመን መፈጸም ጀምረዋል። በመሆኑም ከ37 ዓመታት በኋላ በ70 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በሕይወት የነበሩ ክርስቲያኖች የአይሁድ ሥርዓት ከቤተ መቅደሱ ጋር ሲጠፋ ዱብ ዕዳ አልሆነባቸውም።

ይሁን እንጂ ክርስቶስ በመንግሥቱ ሥልጣን ላይ የተገኘው በ70 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር አይደለም። ኢየሱስ በመንግሥቱ ሥልጣን የተገኘው ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው። ይህ የሆነው ግን መቼ ነው? የኢየሱስን ትንቢት መመርመራችን ለዚህ መልስ እንድናገኝ ይረዳናል።

ኢየሱስ ‘ጦርነትና የጦርነት ወሬ’ እንደሚኖር ተንብዮአል። “ሕዝብ በሕዝብ ላይ” እንደሚነሣና የምግብ እጥረት፣ የመሬት መንቀጥቀጥና ቸነፈር እንደሚኖር ተናገረ። ደቀ መዛሙርቱ ጥላቻ ይደርስባቸዋል፤ እንዲሁም ይገደላሉ። የሐሰት ነቢያት ተነስተው ብዙዎችን ያስታሉ። ዓመፅ ይጨምራል፤ የብዙ ሰዎች ፍቅርም ይቀዘቅዛል። በዚሁ ጊዜ ደግሞ የአምላክ መንግሥት ምሥራች ምሥክር እንዲሆን ለሁሉም ብሔራት ይሰበካል።

ምንም እንኳ የኢየሱስ ትንቢት ኢየሩሳሌም በ70 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ከመጥፋቷ በፊት በተወሰነ ደረጃ የተፈጸመ ቢሆንም ዋነኛ ፍጻሜውን የሚያገኘው ኢየሱስ በሥልጣኑ ላይ በሚገኝበትና በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን ላይ ነው። ከ1914 ወዲህ የተከናወኑትን የዓለም ሁኔታዎች በሚገባ ስንመረምር ኢየሱስ የተናገረው ታላቅ ትንቢት ከዚያ ዓመት አንስቶ ዋነኛ ፍጻሜውን በማግኘት ላይ እንዳለ እንረዳለን።

ኢየሱስ የሰጠው ሌላው የምልክቱ ክፍል ‘የጥፋት ርኩሰት’ መታየት ነው። በ66 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የሮም ‘ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከብቦ’ የቤተ መቅደሱን ግንብ በሰረሰረበት ጊዜ ይህ ርኩሰት ታይቶ ነበር። ‘ርኩሰቱ’ መቆም በማይገባው ሥፍራ ቆሞ ነበር።

በምልክቱ ዋነኛ ፍጻሜ ርኩሰቱ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርና በእሱ እግር የተተካው የተባበሩት መንግሥታት ነው። ሕዝበ ክርስትና ለዓለም ሰላም ተብሎ የተቋቋመውን ይህን ድርጅት የአምላክ መንግሥት ምትክ አድርጋ ትመለከተዋለች። እንዴት ያለ ርኩሰት ነው! ስለዚህ ከጊዜ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት አባል የሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች በሕዝበ ክርስትና (በታላቂቱ ኢየሩሳሌም) ላይ ተነስተው ድምጥማጧን ያጠፏታል።

በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና።” በ70 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው ጥፋት ከአንድ ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች እንደተገደሉበት የሚነገርለት ታላቅ መከራ ነው። የዚህኛው የኢየሱስ ትንቢት ክፍል ዋነኛ ፍጻሜ ከዚህ እጅግ የከፋ ይሆናል።

በመጨረሻዎቹ ቀኖች ውስጥ ተማምኖ መኖር

ኒሳን 11 ማክሰኞ ዕለት እየተገባደደ ሲሄድ ኢየሱስ በመንግሥቱ ሥልጣን የሚገኝበትን ጊዜና የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜን የሚጠቁመውን ምልክት በተመለከተ ከሐዋርያቱ ጋር የሚያደርገውን ውይይት ቀጠለ። ሐሰተኛ ክርስቶሶችን እንዳይከተሉ አስጠነቀቃቸው። ‘ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ ለማሳት’ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናገረ። ሆኖም እነዚህ የተመረጡ ሰዎች ልክ ከርቀት እንደሚመለከቱት ንስሮች እውነተኛው መንፈሳዊ ምግብ ወደሚገኝበት ማለትም በማይታይ ሁኔታ በሥልጣኑ ላይ ወደተገኘው ወደ እውነተኛው ክርስቶስ ይሰበሰባሉ። ተታልለው ወደ አንድ ሐሰተኛ ክርስቶስ አይሰበሰቡም።

ሐሰተኛ ክርስቶሶች በሚታይ ሁኔታ ብቅ ከማለት በቀር ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር የለም። በአንጻሩ ግን ኢየሱስ በሥልጣኑ የሚገኘው በማይታይ ሁኔታ ነው። ኢየሱስ ታላቁ መከራ ከፈነዳ በኋላ “ፀሐይ ይጨልማል፣ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም” ሲል ገልጿል። አዎን፣ ይህ ወቅት በሰው ዘር ሕይወት ውስጥ ታይቶ የማያውቅ የጨለማ ዘመን ይሆናል። ፀሐይ በቀን እንደጨለመችና ጨረቃ ደግሞ በሌሊት ብርሃንዋን እንደማትሰጥ ያህል ይሆናል።

ኢየሱስ በመቀጠል “የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ” ሲል ተናገረ። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ግዑዙ ሰማይ አስፈሪ መልክ እንደሚኖረው አመልክቷል። ፍርሃቱና ዓመፁ ቀደም ባለው የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ካጋጠሙት ነገሮች ሁሉ የከፋ ይሆናል።

በዚህም ምክንያት ኢየሱስ “አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ እያመነቱ ይጨነቃሉ፤ ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ” በማለት ተናግሯል። በእርግጥም ይህ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ታይቶ የማያውቅ የጨለማ ዘመን ወደ ፍጻሜው ሲቃረብ “የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፣ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ።”

ሆኖም “የሰው ልጅ” ይህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ለማጥፋት ‘በኃይል ሲመጣ’ ዋይ ዋይ የሚሉት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። “የተመረጡት” ማለትም ከክርስቶስ ጋር የሰማያዊ መንግሥት ተካፋዮች የሚሆኑት 144,000ዎችም ሆኑ ቀደም ሲል ኢየሱስ “ሌሎች በጎች” ብሎ የጠራቸው ተባባሪዎቻቸው አያለቅሱም። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማያውቅ የጨለማ ዘመን ውስጥ የሚኖሩ ቢሆንም እንኳ ኢየሱስ “ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ [“ደኅንነታችሁ፣” የ1980 ትርጉም] ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ” በማለት ለሰጠው ማበረታቻ አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣሉ።

ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀኖች የሚኖሩት ደቀ መዛሙርቱ ፍጻሜው ምን ያህል እንደቀረበ መረዳት እንዲችሉ የሚከተለውን ምሳሌ ሰጠ:- “በለስንና ዛፎችን ሁሉ እዩ፤ ሲያቈጠቍጡ ተመልክታችሁ በጋ አሁን እንደ ቀረበ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።”

በዚህ መንገድ ደቀ መዛሙርቱ የምልክቱ የተለያዩ ገጽታዎች በመፈጸም ላይ መሆናቸውን ሲመለከቱ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ መቅረቡንና የአምላክ መንግሥት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ክፋትን ሁሉ ጠራርጎ እንደሚያጠፋ መገንዘብ አለባቸው። ኢየሱስ ታላላቅ ነገሮች በሚከናወኑባቸው የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ የሚኖሩትን ደቀ መዛሙርት ሲመክር እንዲህ አለ:-

“ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፣ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና። እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፣ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ።”

ልባሞቹና ሰነፎቹ ቆነጃጅት

ኢየሱስ ሐዋርያቱ በመንግሥቱ ሥልጣን መገኘቱን የሚጠቁም ምልክት እንዲሰጣቸው ላቀረቡለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ቆይቷል። አሁን ሦስት ምሳሌዎችን በመጠቀም የምልክቱን ተጨማሪ ገጽታዎች ተናገረ።

ኢየሱስ በሥልጣኑ በሚገኝበት ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ ሰዎች የእያንዳንዱን ምሳሌ ፍጻሜ ይመለከታሉ። የመጀመሪያውን ምሳሌ በሚከተሉት ቃላት ገለጸ:- “በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቈነጃጅትን ትመስላለች። ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ።”

ኢየሱስ ‘መንግሥተ ሰማያት አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች’ ሲል ሰማያዊውን መንግሥት ከሚወርሱት ሰዎች መካከል ግማሾቹ ሰነፎች ግማሾቹ ደግሞ ልባሞች ናቸው ማለቱ አይደለም! ከዚህ ይልቅ ከመንግሥተ ሰማያት ጋር በተያያዘ ይህን የመሰለ ሁኔታ አለ ብሎ ለመጥቀስ ወይም ደግሞ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ እንዲህ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች አሉ ብሎ ለመግለጽ ፈልጎ ነው።

አሥሩ ቆነጃጅት መንግሥተ ሰማያትን የመውረስ አጋጣሚ ያላቸውን ወይም ደግሞ መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን የሚሉ ክርስቲያኖችን በሙሉ ያመለክታሉ። የክርስቲያን ጉባኤ ከሞት ተነሥቶ ክብር ለተቀዳጀው ሙሽራ ለኢየሱስ ክርስቶስ የታጨችው በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ነው። ሆኖም ጋብቻው ወደፊት ተለይቶ ባልተጠቀሰ ጊዜ ላይ በሰማይ ይከናወናል።

በምሳሌው ላይ እንደተገለጸው አሥሩ ቆነጃጅት የወጡት ሙሽራውን ለመቀበልና በሠርጉ አጀብ ውስጥ ለመቀላቀል ነው። ሙሽራው ሙሽራይቱን ወደተዘጋጀላት ቤት ሲያመጣት አጀቡን በመብራታቸው በማድመቅ ለእሱ ያላቸውን አክብሮት ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ። ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ።”

ሙሽራው ረዘም ላለ ጊዜ መዘግየቱ ክርስቶስ ንጉሣዊ ገዥ ሆኖ በሥልጣኑ ላይ የሚገኘው ከረጅም ጊዜ በኋላ እንደነበረ ያመለክታል። ከረጅም ጊዜ በኋላ በ1914 በዙፋኑ ላይ ተቀምጧል። ከዚህ በፊት በነበረው ረጅም ሌሊት ቆነጃጅቱ በሙሉ ተኝተው ነበር። ሆኖም በዚህ አልተነቀፉም። ሰነፎቹ ቆነጃጅት የተነቀፉት በዕቃቸው ውስጥ ዘይት ባለመያዛቸው ነው። ኢየሱስ ቆነጃጅቱ ሙሽራው ከመምጣቱ በፊት እንዴት እንደነቁ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “እኩል ሌሊትም ሲሆን:- እነሆ ሙሽራው ይመጣል፣ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ። በዚያን ጊዜ እነዚያ ቈነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። ሰነፎቹም ልባሞቹን:- መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው። ልባሞቹ ግን መልሰው:- ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው።”

ዘይቱ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ብርሃን አብሪዎች ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያስችላቸውን ነገር ያመለክታል። ይህም ክርስቲያኖች ዘወትር አጥብቀው የሚይዙት በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ቃልና ይህን ቃል ማስተዋል እንዲችሉ የሚረዳቸው መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈሳዊው ዘይት ልባሞቹ ቆነጃጅት ወደ ሠርጉ ድግስ በሚደረገው ጉዞ መብራታቸውን አብርተው ሙሽራውን እንዲቀበሉ ያስችላቸዋል። ሰነፎቹ ቆነጃጅት ግን በውስጣቸው ማለትም በዕቃቸው ውስጥ አስፈላጊው መንፈሳዊ ዘይት የላቸውም። ስለዚህ ኢየሱስ የተፈጸመውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ገለጸ:-

“[ሰነፎቹ ቆነጃጅት ዘይት] ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፣ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፣ ደጁም ተዘጋ። በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነጃጅት መጡና:- ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፣ ክፈትልን አሉ። እርሱ ግን መልሶ:- እውነት እላችኋለሁ፣ አላውቃችሁም አለ።”

ክርስቶስ ወደ ሰማያዊ መንግሥቱ በመጣ ጊዜ የልባሞቹ ቆነጃጅት ክፍል የሆኑት እውነተኛ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ተመልሶ ለመጣው ሙሽራ ክብር በዚህ በጨለማ ዓለም ውስጥ ብርሃን የማብራት ልዩ መብታቸውን ለመጠቀም ንቁዎች ሆነዋል። በሰነፎቹ ቆነጃጅት የተመሰሉት ግን ይህን ክብራማ አቀባበል ለማድረግ ዝግጁዎች አልነበሩም። ስለዚህ ጊዜው ሲደርስ ክርስቶስ ወደ ሰማያዊው ሠርግ የሚያስገባውን በር አይከፍትላቸውም። ከሌሎች ዓመፅ አድራጊዎች ጋር እንዲጠፉ ውጪ በዓለም የሌሊት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ይተዋቸዋል። ኢየሱስ “ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ” ሲል ደመደመ።

የመክሊቱ ምሳሌ

ኢየሱስ ከሦስቱ ተከታታይ ምሳሌዎች ውስጥ ሁለተኛውን ምሳሌ በመናገር ከሐዋርያቱ ጋር በደብረ ዘይት ተራራ ላይ እያደረገ ያለውን ውይይት ቀጠለ። ከጥቂት ቀናት በፊት በኢያሪኮ እያለ መንግሥቱ የሚመጣው ገና ከረጅም ጊዜ በኋላ እንደሆነ ለማመልከት የምናኑን ምሳሌ ተናግሮ ነበር። አሁን የተናገረው ምሳሌ በርከት ያሉ ተመሳሳይ የሆኑ ገጽታዎች ቢኖሩትም ክርስቶስ በመንግሥቱ ሥልጣን በሚገኝበት ጊዜ የሚፈጸሙትን ሁኔታዎች የሚገልጽ ነው። ምሳሌው ደቀ መዛሙርቱ በምድር ላይ ሳሉ “ንብረቱን” ለማሳደግ መሥራት እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው።

ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምሳሌውን መናገር ጀመረ:- “ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ [“ንብረቱን፣” የ1980 ትርጉም] እንደ ሰጣቸው [ከመንግሥቱ ጋር የተያያዘው ሁኔታም] እንዲሁ ይሆናልና።” ወደ ሌላ አገር ማለትም ወደ ሰማይ ከመሄዱ በፊት ለባሮቹ ማለትም ሰማያዊውን መንግሥት የመውረስ አጋጣሚ ላላቸው ደቀ መዛሙርቱ ንብረቱን የሰጠው ሰው ኢየሱስ ነው። ይህ ንብረት ቁሳዊ ነገር ሳይሆን ኢየሱስ ያዘጋጀውን ተጨማሪ ደቀ መዛሙርት ለማፍራት የሚያስችል የለማ እርሻ ያመለክታል።

ኢየሱስ ንብረቱን ለባሪያዎቹ በአደራ የሰጠው ወደ ሰማይ ከማረጉ ጥቂት ቀደም ብሎ ነው። ይህን ያደረገው እንዴት ነው? የመንግሥቱን መልእክት እስከ ምድር ዳርቻዎች በመስበክ በለማው እርሻ ላይ መሥራታቸውን እንዲቀጥሉ መመሪያ በመስጠት ነው። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፣ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር . . . ሄደ።”

በዚህ መንገድ ስምንቱ መክሊት ማለትም የክርስቶስ ንብረት እንደ ባሪያዎቹ ችሎታ ወይም መንፈሳዊ አቅም ተከፋፈለ። ባሪያዎቹ የደቀ መዛሙርት ቡድኖችን ያመለክታሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን አምስት መክሊት የተቀበለው ቡድን ሐዋርያትን እንደሚጨምር ግልጽ ነው። ኢየሱስ በመቀጠል አምስትና ሁለት መክሊት የተቀበሉት ባሪያዎች ሁለቱም በመንግሥቱ የስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራቸው መክሊቶቹን እጥፍ አደረጓቸው። አንድ መክሊት የተቀበለው ባሪያ ግን መክሊቱን መሬት ውስጥ ደበቀው።

ኢየሱስ በመቀጠል “ከብዙ ጊዜ በኋላ የነዚያ አገልጋዮች ጌታ መጣና ከአገልጋዮቹ ጋር መተሳሰብ ጀመረ” ሲል ተናገረ። (የ1980 ትርጉም) ክርስቶስ ከባሪያዎቹ ጋር ለመተሳሰብ ተመልሶ የመጣው ከ1,900 ዓመታት በኋላ በ20ኛው መቶ ዘመን ላይ በመሆኑ በእርግጥም የተመለሰው “ከብዙ ጊዜ በኋላ” ነው። ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:-

“አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ:- ጌታ ሆይ፣ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ፣ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም:- መልካም፣ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፣ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው።” በተመሳሳይም ሁለት መክሊት የተቀበለው ባሪያ መክሊቱን እጥፍ አድርጎ በማትረፉ ተመሳሳይ የሆነ ምስጋናና ወሮታ አገኘ።

ይሁን እንጂ እነዚህ ታማኝ ባሪያዎች ወደ ጌታቸው ደስታ የሚገቡት እንዴት ነው? የጌታቸው የኢየሱስ ክርስቶስ ደስታ ወደ ሌላ አገር ማለትም አባቱ ወደሚገኝበት ወደ ሰማይ በሄደ ጊዜ መንግሥቱን በባለቤትነት መረከቡ ነው። በዘመናችን ያሉት ታማኝ ባሪያዎች እምነት ተጥሎባቸው ተጨማሪ የመንግሥቱን ኃላፊነቶች በመቀበላቸው ታላቅ ደስታ አግኝተዋል፤ ምድራዊ ሕይወታቸውን ሲጨርሱም ከሞት ተነሥተው ሰማያዊውን መንግሥት በመውረስ የመጨረሻውን ደስታ ያገኛሉ። ይሁን እንጂ ሦስተኛው ባሪያስ?

ይህ ባሪያ “ጌታ ሆይ፣ . . . ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ” ሲል ተቃውሞውን ገለጸ። “ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፣ መክሊትህ አለህ።” ባሪያው በመስበክና ደቀ መዛሙርት በማድረግ በለማው እርሻ ላይ ለመሥራት ሆን ብሎ አሻፈረኝ ብሏል። ስለዚህ ጌታው “ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ” አለው፤ ከዚያም የሚከተለውን ፍርድ በየነበት:- “መክሊቱን ውሰዱበት . . . የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” የዚህ ክፉ ባሪያ ክፍል አባላት ወደ ውጭ ስለተጣሉ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ደስታ የላቸውም።

ይህ የክርስቶስ ተከታዮች ነን ለሚሉ ሁሉ ከበድ ያለ ትምህርት ያስተላልፋል። የእሱን ምስጋናና ወሮታ እንዲያገኙና ውጭ ወዳለው ጨለማ ተወርውረው ለአንዴና ለመጨረሻ እንዳይጠፉ ከፈለጉ በስብከቱ ሥራ ሙሉ በሙሉ በመካፈል የሰማያዊ ጌታቸው ንብረት እንዲጨምር መሥራት አለባቸው። በዚህ ረገድ ትጉህ ነህን?

ክርስቶስ በመንግሥቱ ሥልጣን በሚመጣበት ጊዜ

ኢየሱስ አሁንም ያለው ከሐዋርያቱ ጋር በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ነው። ስለ መገኘቱና ስለ ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት እንዲሰጣቸው ላቀረቡለት ጥያቄ መልስ በመስጠት አሁን ከሦስቱ ተከታታይ ምሳሌዎች የመጨረሻውን ተናገረ። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምሳሌውን መናገር ጀመረ:- “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል።”

ኢየሱስ የሚመጣው የዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ በጣም በሚቃረብበት ጊዜ ላይ ነው። የሚመጣው ግን ለምን ዓላማ ነው? ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፣ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል።”

ኢየሱስ ሞገሱን ወዳገኙበት ጎን የተለዩት ሰዎች ስለሚያጋጥማቸው ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ አለ:- “ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል:- እናንተ የአባቴ ብሩካን፣ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።” በዚህ ምሳሌ ላይ የተገለጹት በጎች ከክርስቶስ ጋር በሰማይ አይገዙም፤ ከዚህ ይልቅ የመንግሥቱ ምድራዊ ተገዥዎች በመሆን መንግሥቱን ይወርሳሉ። ‘ዓለም የተፈጠረው’ አዳምና ሔዋን አምላክ የሰውን ዘር ለመቤዠት ባዘጋጀው ዝግጅት መጠቀም የሚችሉ ልጆችን መውለድ በጀመሩበት ጊዜ ነው።

ይሁን እንጂ በጎቹ የንጉሡን ሞገስ ወዳገኙበት ወደ ቀኝ ጎኑ የተለዩት ለምንድን ነው? ንጉሡ “ተርቤ አብልታችሁኛልና፣” ሲል ተናገረ፤ “ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፣ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፣ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፣ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፣ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና።”

በጎቹ ያሉት ምድር ላይ ስለሆነ እነዚህን መልካም ነገሮች ለሰማያዊ ንጉሣቸው ሊያደርጉ የቻሉት እንዴት እንደሆነ ማወቅ ፈለጉ። “ጌታ ሆይ፣ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ?” ሲሉ ጠየቁት፤ “ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን?”

ንጉሡም “እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት” ሲል መለሰላቸው። የክርስቶስ ወንድሞች የተባሉት ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚገዙ በዚህ ምድር ላይ ያሉ የ144,000 ቀሪዎች ናቸው። ኢየሱስ ለእነርሱ ጥሩ ነገር ማድረግ ለእሱ ጥሩ ነገር እንደማድረግ የሚቆጠር መሆኑን ተናግሯል።

ከዚህ በመቀጠል ንጉሡ ፍየሎቹን እንዲህ አላቸው:- “እናንተ ርጉማን፣ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፣ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፣ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፣ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፣ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና።”

ይሁን እንጂ ፍየሎቹ እንዲህ ሲሉ አቤቱታቸውን አቀረቡ:- “ጌታ ሆይ፣ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም?” በጎቹ ጥሩ ፍርድ እንዲፈረድላቸውና ፍየሎቹ ደግሞ መጥፎ ፍርድ እንዲፈረድባቸው ያደረገው ነገር አንድ ነው። ኢየሱስ “ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ [ወንድሞቼ] ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም” በማለት መልሱን ሰጥቷል።

ስለዚህ ይህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት በታላቁ መከራ ከመጥፋቱ በፊት ያለው ክርስቶስ በመንግሥታዊ ሥልጣኑ ላይ የሚገኝበት ጊዜ የፍርድ ወቅትንም የሚጨምር ይሆናል። ፍየሎቹ “ወደ ዘላለም ቅጣት፣ ጻድቃን [በጎቹ] ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።” ማቴዎስ 24:​2 እስከ 25:​46፤ 13:​40, 49፤ ማርቆስ 13:​3-37፤ ሉቃስ 21:​7-36፤ 19:​43, 44፤ 17:​20-30፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5፤ ዮሐንስ 10:​16፤ ራእይ 14:​1-3

▪ ሐዋርያቱ ጥያቄ እንዲያነሱ የገፋፋቸው ምን ነበር? ሆኖም ምን ሌላ ተጨማሪ ነገር በአእምሯቸው ሳይዙ አይቀርም?

▪ በ70 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የተፈጸመው የትኛው የኢየሱስ ትንቢት ክፍል ነው? በዚያ ጊዜ ያልተፈጸመውስ ነገር የትኛው ነው?

▪ የኢየሱስ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው መቼ ነበር? ሆኖም ዋነኛ ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ ነው?

▪ ርኩሰቱ በመጀመሪያውና በመጨረሻው ፍጻሜ ላይ የሚያመለክተው ማንን ነው?

▪ ታላቁ መከራ ኢየሩሳሌም ስትጠፋ የመጨረሻ ፍጻሜውን ያላገኘው ለምንድን ነው?

▪ የክርስቶስን መገኘት የሚያመለክቱት የትኞቹ የዓለም ሁኔታዎች ናቸው?

▪ ‘የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ የሚሉት’ መቼ ነው? ሆኖም በዚያን ጊዜ የክርስቶስ ተከታዮች ምን ያደርጋሉ?

▪ ኢየሱስ የወደፊቶቹ ደቀ መዛሙርቱ መጨረሻው ሲቀርብ ማስተዋል እንዲችሉ ለመርዳት ምን ምሳሌ ሰጠ?

▪ ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀኖች ለሚኖሩት ደቀ መዛሙርቱ ምን ምክር ሰጥቷል?

▪ በአሥሩ ቆነጃጅት የተመሰሉት እነማን ናቸው?

▪ የክርስቲያን ጉባኤ ለሙሽራው የታጨችው መቼ ነው? ሆኖም ሙሽራው ሙሽራይቱን ወደ ሠርጉ ድግስ ለመውሰድ የመጣው መቼ ነው?

▪ ዘይቱ ምን ያመለክታል? ልባሞቹ ቆነጃጅት ዘይቱን መያዛቸው ምን ለማድረግ ያስችላቸዋል?

▪ የሠርጉ ድግስ የሚካሄደው የት ነው?

▪ ሰነፎቹ ቆነጃጅት ምን ታላቅ ሽልማት አጥተዋል? የመጨረሻ ዕጣቸውስ ምንድን ነው?

▪ የመክሊቱ ምሳሌ ምን ትምህርት ያስተላልፋል?

▪ ባሪያዎቹ እነማን ናቸው? በአደራ የተሰጣቸው ንብረትስ ምንድን ነው?

▪ ጌታው ሒሳቡን ለመተሳሰብ የመጣው መቼ ነው? ያገኘውስ ነገር ምን ነበር?

▪ ታማኞቹ ባሪያዎች የገቡት ወደ የትኛው ደስታ ነው? ክፉ የሆነው ሦስተኛው ባሪያስ ምን ደረሰበት?

▪ ክርስቶስ በሥልጣኑ ላይ በተገኘበት ዘመን ምን የፍርድ ሥራ ያከናውናል?

▪ በጎቹ መንግሥቱን የሚወርሱት በምን መንገድ ነው?

▪ ‘ዓለም የተፈጠረው’ መቼ ነው?

▪ ሰዎች በጎች ወይም ፍየሎች ተብለው የሚፈረድባቸው በምን መሠረት ነው?