በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምሕረት ተልዕኮ ለመፈጸም ወደ ይሁዳ መጓዝ

የምሕረት ተልዕኮ ለመፈጸም ወደ ይሁዳ መጓዝ

ምዕራፍ 89

የምሕረት ተልዕኮ ለመፈጸም ወደ ይሁዳ መጓዝ

አይሁዶች ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኢየሩሳሌም በተከበረው የመቅደስ መታደስ በዓል ላይ ኢየሱስን ሊገድሉት ሞክረው ነበር። ስለዚህ በስተ ሰሜን ከገሊላ ባሕር ብዙም ወደማይርቅ ቦታ ተጓዘ።

ከጥቂት ጊዜ በፊት ደግሞ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ በምትገኘው የፍርጊያ አውራጃ ውስጥ ባሉ መንደሮች እየሰበከ እንደገና በደቡብ በኩል ወደ ኢየሩሳሌም አቀና። ስለ ሀብታሙ ሰውና ስለ አልዓዛር የሚገልጸውን ምሳሌ ከተናገረ በኋላ ቀደም ሲል በገሊላ ያስተማራቸውን ነገሮች ለደቀ መዛሙርቱ ማስተማር ጀመረ።

ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው አምላክ ከመረጣቸው “ታናናሾች” መካከል አንዱን ከሚያሰናክል “የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል” እንደሚሻለው ተናግሯል። በተጨማሪም ይቅር የማለትን አስፈላጊነት በማጉላት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “[ወንድምህ] በቀንም ሰባት ጊዜ እንኳ ቢበድልህ በቀንም ሰባት ጊዜ:- ተጸጸትሁ እያለ ወደ አንተ ቢመለስ፣ ይቅር በለው።”

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ “እምነት ጨምርልን” ብለው ሲጠይቁት “የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህን ሾላ:- ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት፣ ይታዘዝላችሁ ነበር” ሲል መለሰላቸው። ስለዚህ ትንሽ እምነት እንኳን ትልቅ ነገር ማከናወን ይችላል።

ኢየሱስ በመቀጠል ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ የሚያገለግል ሰው ሊኖረው የሚገባውን ትክክለኛ አመለካከት የሚገልጽ በዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ የሚንጸባረቅ ሁኔታ በመጥቀስ ተናገረ። እንዲህ አለ:- “ከእናንተም የሚያርስ ወይም ከብትን የሚጠብቅ ባሪያ ያለው፣ ከእርሻ ሲመለስ:- ወዲያው ቅረብና በማዕድ ተቀመጥ የሚለው ማን ነው? የምበላውን እራቴን አሰናዳልኝ፣ እስክበላና እስክጠጣ ድረስ ታጥቀህ አገልግለኝ፣ በኋላም አንተ ብላና ጠጣ የሚለው አይደለምን? ያንን ባሪያ ያዘዘውን ስላደረገ ያመሰግነዋልን? እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ:- የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፣ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ።” ስለዚህ የአምላክ አገልጋዮች አምላክን ሲያገለግሉ ውለታ እየዋሉለት እንዳሉ ሊሰማቸው አይገባም። ከዚህ ይልቅ የቤተሰቡ የታመኑ አባላት በመሆን ያገኙትን እርሱን የማምለክ መብት ሁልጊዜ ማስታወስ አለባቸው።

ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ከሰጠ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሳይሆን አይቀርም፣ አንድ መልእክተኛ መጣ። ሰውየውን የላኩት በይሁዳ በምትገኘው በቢታንያ የሚኖሩት የአልዓዛር እህቶች ማርያምና ማርታ ነበሩ። መልእክተኛው “ጌታ ሆይ፣ እነሆ፣ የምትወደው ታሞአል” ብሎ ነገረው።

ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ:- “ይህ ሕመም የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይደለም።” ኢየሱስ በነበረበት ሥፍራ ሁለት ቀን ከቆየ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “ወደ ይሁዳ ደግሞ እንሂድ” አላቸው። እነርሱ ግን “መምህር ሆይ፣ አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፣ ደግሞም ወደዚያ ትሄዳለህን?” በማለት አሳሰቡት።

ኢየሱስ መልሶ “በቀን ውስጥ ያለው ጊዜ ዐሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን”? ሲል ጠየቃቸው። “በቀን የሚመላለስ የዚህን ዓለም ብርሃን ስለሚያይ አይሰናከልም። ነገር ግን በሌሊት የሚመላለስ ብርሃን ስለሌለው ይሰናከላል።”​—የ1980 ትርጉም

ኢየሱስ ‘በቀን ውስጥ ያለው ሰዓት’ ወይም አምላክ ለኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት የወሰነው ጊዜ አለማለቁንና እስከሚያልቅ ድረስ ማንም ሰው ጉዳት ሊያደርስበት እንደማይችል መናገሩ ሳይሆን አይቀርም። ከጊዜ በኋላ ጠላቶቹ እሱን የሚገድሉበት “ሌሊት” ስለሚመጣ አሁን የቀረውን ‘የቀኑን’ አጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ ሊጠቀምበት ይፈልጋል።

ኢየሱስ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” ሲል አክሎ ተናገረ።

ደቀ መዛሙርቱ አልዓዛር እንቅልፍ እንደተኛና ይህም የሚያገግም መሆኑን የሚያሳይ ተስፋ ሰጪ ፍንጭ እንደሆነ አድርገው በማሰብ “ጌታ ሆይ፣ ተኝቶስ እንደ ሆነ ይድናል” ብለው መለሱለት።

በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በግልጽ እንዲህ ሲል ነገራቸው:- “አልዓዛር ሞተ፤ እንድታምኑም በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ወደ እርሱ እንሂድ።”

ቶማስ ምንም እንኳ ኢየሱስ በይሁዳ ሊገደል እንደሚችል ቢገነዘብም እሱን ለመርዳት በመፈለጉ ሌሎቹን ደቀ መዛሙርት “ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛ ደግሞ እንሂድ” በማለት አበረታታቸው። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ በሕይወታቸው ቆርጠው ኢየሱስን ተከትለው የምሕረት ተልእኮ ለመፈጸም ወደ ይሁዳ በተደረገው በዚህ ጉዞ አብረውት ተጓዙ። ሉቃስ 13:​22፤ 17:​1-10፤ ዮሐንስ 10:​22, 31, 40-42፤ 11:​1-16

▪ ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በፊት የት ሲሰብክ ነበር?

▪ ኢየሱስ የትኞቹን ትምህርቶች በድጋሚ አስተምሯል? የትኛውን ነጥብ በምሳሌ ለማስረዳት ሲል በዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ የተመሠረተ ምን ሁኔታ ገልጿል?

▪ ኢየሱስ ምን መልእክት ደረሰው? “ቀን” እና “ሌሊት” ሲልስ ምን ማለቱ ነው?

▪ ቶማስ ‘ከእርሱ ጋር እንድንሞት እንሂድ’ ሲል ምን ማለቱ ነው?