በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምናኑ ምሳሌ

የምናኑ ምሳሌ

ምዕራፍ 100

የምናኑ ምሳሌ

ኢየሱስ አሁንም ያለው ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ እግረ መንገዱን ጎራ ባለበት በዘኬዎስ ቤት ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሩሳሌም ሲደርሱ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን በይፋ አሳውቆ መንግሥቱን ያቋቁማል የሚል እምነት ነበራቸው። ኢየሱስ ይህን አስተሳሰብ ለማረምና መንግሥቱ ገና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ መሆኑን ለማመልከት አንድ ምሳሌ ሰጠ።

“አንድ መኰንን” በማለት ኢየሱስ መተረክ ጀመረ፤ “ለራሱ መንግሥትን ይዞ ሊመለስ ወደ ሩቅ አገር ሄደ።” “መኰንን” የተባለው ኢየሱስ ሲሆን “ሩቅ አገር” የተባለው ደግሞ ሰማይ ነው። ኢየሱስ እዚያ ሲሄድ አባቱ ንጉሣዊ ሥልጣን ይሰጠዋል።

ይሁን እንጂ መኰንኑ ከመሄዱ በፊት አሥር ባሪያዎች ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው አንድ የብር ምናን ሰጣቸውና “እስክመጣ ድረስ ነግዱ” አላቸው። በመጀመሪያው የምሳሌው ፍጻሜ ላይ አሥሩ ባሪያዎች የመጀመሪያዎቹን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያመለክታሉ። ሰፋ ባለ መልኩ ሲታይ ደግሞ ሰማያዊውን መንግሥት ከኢየሱስ ጋር የሚወርሱትን ሰዎች በሙሉ ያመለክታሉ።

የብር ምናኑ ውድ ዋጋ ያለው ገንዘብ ነበር፤ እያንዳንዱ ምናን ለአንድ የእርሻ ሠራተኛ የሦስት ወር ደሞዝ ያህል ይሆን ነበር። ሆኖም ምናኖቹ ምን ያመለክታሉ? ባሪያዎቹ በምናኖቹ የሚያካሄዱት ንግድስ ምን ዓይነት ነው?

ምናኖቹ በመንፈስ የተወለዱት ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት መንግሥት ንጉሥ ሆኖ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ተጨማሪ የሰማያዊ መንግሥት ወራሾች ለማፍራት የሚጠቀሙበትን ንብረት ያመለክታሉ። ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ ለደቀ መዛሙርቱ ከተገለጠላቸው በኋላ ተጨማሪ ደቀ መዛሙርት አፍርተው የሰማያዊውን መንግሥት አባላት እንዲጨምሩ ምሳሌያዊ ምናን ሰጥቷቸዋል።

ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “የአገሩ ሰዎች ግን [መኰንኑን] ይጠሉት ነበርና:- ይህ በላያችን ሊነግሥ አንወድም ብለው በኋላው መልክተኞችን ላኩ።” የአገሩ ሰዎች የተባሉት ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ውጭ ያሉትን እስራኤላውያን ወይም አይሁዶች በሙሉ ያመለክታሉ። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ እነዚህ አይሁዶች ደቀ መዛሙርቱን በማሳደድ ኢየሱስ ንጉሣቸው እንዲሆን የማይፈልጉ መሆናቸውን አሳይተዋል። በዚህ መንገድ መልክተኞችን በኋላው የላኩት የአገሩ ሰዎች የፈጸሙትን ዓይነት ድርጊት ፈጽመዋል።

አሥሩ ባሪያዎች ምናኖቻቸውን የተጠቀሙባቸው እንዴት ነው? ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “መንግሥትንም ይዞ በተመለሰ ጊዜ፣ ገንዘብ የሰጣቸውን እነዚህን ባሪያዎች ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ያውቅ ዘንድ እንዲጠሩለት አዘዘ። የፊተኛውም ደርሶ:- ጌታ ሆይ፣ ምናንህ አሥር ምናን አተረፈ አለው። እርሱም:- መልካም፣ አንተ በጎ ባርያ፣ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በአሥር ከተማዎች ላይ ሥልጣን ይሁንልህ አለው። ሁለተኛውም መጥቶ:- ጌታ ሆይ፣ ምናንህ አምስት ምናን አተረፈ አለው። ይህንም ደግሞ:- አንተም በአምስት ከተማዎች ላይ ሁን አለው።”

አሥር ምናን ያተረፈው ባሪያ ሐዋርያትን ጨምሮ በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ከተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል አንስቶ እስካሁን ድረስ ያሉትን ደቀ መዛሙርት ያቀፈን አንድ ክፍል ወይም ቡድን ያመለክታል። አምስት ምናን ያተረፈው ባሪያም ሁኔታቸውና ችሎታቸው በፈቀደላቸው መጠን በምድር ላይ ያለው የንጉሣቸው ንብረት እንዲበዛ ያደረጉትን አባላት ያቀፈ በዚሁ ጊዜ ያለን አንድ ቡድን ያመለክታል። ሁለቱም ቡድኖች ምሥራቹን በቅንዓት ይሰብካሉ፤ በውጤቱም ቅን ልብ ያላቸው ብዙ ሰዎች ክርስቲያኖች ሆነዋል። ዘጠኙ ባሪያዎች የተሳካ ንግድ በማካሄድ ንብረታቸውን አሳድገዋል።

ኢየሱስ ቀጥሎ እንዲህ አለ:- “ሌላውም መጥቶ:- ጌታ ሆይ፣ በጨርቅ ጠቅልዬ የጠበቅኋት ምናንህ እነሆ፤ ፈርቼሃለሁና፣ ጨካኝ ሰው ስለ ሆንህ፤ ያላኖርኸውን ትወስዳለህ ያልዘራኸውንም ታጭዳለህ አለው። እርሱም:- አንተ ክፉ ባሪያ፣ አፍህ በተናገረው እፈርድብሃለሁ። እኔ ያላኖርሁትን የምወስድና ያልዘራሁትን የማጭድ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ አወቅህ፤ ምን ነው ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ያልሰጠኸው? እኔም መጥቼ ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር አለው። በዚያም ቆመው የነበሩትን:- ምናኑን ውሰዱበት አሥሩ ምናን ላለውም ስጡት አላቸው።”

ክፉው ባሪያ ምሳሌያዊውን ምናን ማጣቱ በሰማያዊ መንግሥት ያለውን ቦታ ማጣቱን ያመለክታል። አዎን፣ በምሳሌያዊ አነጋገር አሥር ከተሞችን ወይም አምስት ከተሞችን የመግዛት መብት አጥቷል። በተጨማሪም ባሪያው ክፉ የተባለው መጥፎ ድርጊት ፈጽሞ ሳይሆን ለጌታው መንግሥት ሀብት እድገት የሚጠቅም ሥራ ባለመሥራቱ ነው።

የክፉው ባሪያ ምናን ለመጀመሪያው ባሪያ ሲሰጥ “ጌታ ሆይ፣ አሥር ምናን አለው” የሚል ተቃውሞ ቀርቦ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ የሚከተለውን መልስ ሰጠ:- “ላለው ሁሉ ይሰጠዋል፣ ከሌለው ግን ያው ያለው ስንኳ ይወሰድበታል። ነገር ግን እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡአቸው በፊቴም እረዱአቸው።” ሉቃስ 19:​11-27፤ ማቴዎስ 28:​19, 20

▪ ኢየሱስ የምናኑን ምሳሌ እንዲናገር ያነሳሳው ምንድን ነው?

▪ መኰንኑ ማን ነው? የሄደበት አገርስ ምንድን ነው?

▪ ባሪያዎቹ እነማን ናቸው? ምናኖቹ የሚያመለክቱትስ ምንድን ነው?

▪ የአገሩ ሰዎች የተባሉት እነማን ናቸው? ጥላቻቸውን ያሳዩትስ እንዴት ነው?

▪ አንዱ ባሪያ ክፉ የተባለው ለምንድን ነው? ምናኑን ማጣቱስ ምን ያመለክታል?