በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሠርጉ ድግስ ምሳሌ

የሠርጉ ድግስ ምሳሌ

ምዕራፍ 107

የሠርጉ ድግስ ምሳሌ

ኢየሱስ ሁለት ምሳሌዎች በመናገር ጻፎቹንና የካህናት አለቆቹን ስላጋለጣቸው ሊገድሉት ፈለጉ። ሆኖም ኢየሱስ በዚህ ብቻ አላበቃም። አሁንም እንዲህ በማለት ሌላ ምሳሌ ነገራቸው:-

“መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሰርግ ያደረገ ንጉሥን ትመስላለች። የታደሙትንም ወደ ሰርጉ ይጠሩ ዘንድ ባሮቹን ላከ ሊመጡም አልወደዱም።”

ሠርጉን ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ የደገሰው ንጉሥ ይሖዋ አምላክ ነው። መቶ አርባ አራት ሺዎቹን ቅቡዓን ተከታዮች ያቀፈችው ሙሽራ በመጨረሻ በሰማይ ከኢየሱስ ጋር ትጣመራለች። የንጉሡ ተገዥዎች በ1513 ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት ወደ ሕጉ ቃል ኪዳን በመግባት “የካህናት መንግሥት” የመሆን አጋጣሚ የተቀበሉት የእስራኤል ሕዝብ ናቸው። ስለዚህ በዚያ ወቅት ወደ ሠርጉ ድግስ እንዲመጡ በመጀመሪያ የተጋበዙት እነርሱ ነበሩ።

ይሁን እንጂ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ (የንጉሡ ባሮች) የመንግሥቱን ስብከት ሥራቸውን እስከ ጀመሩበት እስከ 29 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የመከር ወራት ድረስ ኑ የሚለው ጥሪ ለተጋበዙት ሰዎች አልቀረበም ነበር። ሆኖም ከ29 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር አንስቶ እስከ 33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ድረስ በባሮቹ አማካኝነት ይህ ጥሪ የቀረበላቸው ሥጋዊ እስራኤላውያን ለመምጣት ፈቃደኞች አልሆኑም። ስለዚህ አምላክ ለተጋባዡ ሕዝብ ሌላ አጋጣሚ ሰጠ፤ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገልጿል:-

“ደግሞ ሌሎችን ባሮች ልኮ:- የታደሙትን:- እነሆ፣ ድግሴን አዘጋጀሁ፣ ኮርማዎቼና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፣ ሁሉም ተዘጋጅቶአል፤ ወደ ሰርጉ ኑ በሉአቸው አለ።” ይህ ለተጋበዙት ሰዎች የቀረበው ሁለተኛውና የመጨረሻው ጥሪ የጀመረው በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ተከታዮች ላይ በፈሰሰበት ጊዜ ነበር። ይህ ጥሪ እስከ 36 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ድረስ ቀጥሏል።

ይሁን እንጂ አብዛኞቹ እስራኤላውያን አሁንም ይህን ጥሪ ንቀዋል። “እነርሱ ግን ቸል ብለው” አለ ኢየሱስ፤ “አንዱ ወደ እርሻው፣ ሌላውም ወደ ንግዱ ሄደ፤ የቀሩትም ባሮቹን ይዘው አንገላቱአቸው ገደሉአቸውም።” ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “ንጉሡም ተቈጣ፣ ጭፍሮቹንም ልኮ እነዚያን ገዳዮች አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ።” ይህ ኢየሩሳሌም በ70 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በሮማውያን በወደመችበትና እነዚያ ነፍሰ ገዳዮች በተገደሉበት ጊዜ ፍጻሜውን አግኝቷል።

ኢየሱስ በዚህ መካከል የተፈጸመውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “በዚያን ጊዜ [ንጉሡ] ባሮቹን:- ሰርጉስ ተዘጋጅቶአል፣ ነገር ግን የታደሙት የማይገባቸው ሆኑ፤ እንግዲህ ወደ መንገድ መተላለፊያ ሄዳችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ አለ።” ባሮቹ የታዘዙትን አደረጉ፤ “የሰርጉንም ቤት ተቀማጮች ሞሉት።”

ከተጋባዦቹ ከተማ ውጪ ካሉ መንገዶች እንግዶችን የመሰብሰቡ ሥራ የጀመረው በ36 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ነው። ወደ ሠርጉ ከተሰበሰቡት ያልተገረዙ አሕዛብ መካከል የመጀመሪያዎቹ የሮማ ሠራዊት አለቃ የሆነው ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ ናቸው። መጀመሪያ የቀረበላቸውን ጥሪ አልቀበልም ያሉትን ሰዎች የሚተኩትን እነዚህን አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች የመሰብሰቡ ሥራ እስከ 20ኛው መቶ ዘመን ድረስ ቀጥሏል።

ሠርጉ የተደገሰበት ቤት የሞላው በ20ኛው መቶ ዘመን ነው። ኢየሱስ ከዚያ በኋላ የተፈጸመውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ንጉሡም የተቀመጡትን ለማየት በገባ ጊዜ በዚያ የሰርግ ልብስ ያልለበሰ አንድ ሰው አየና:- ወዳጄ ሆይ፣ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ? አለው፤ እርሱም ዝም አለ። በዚያን ጊዜ ንጉሡ አገልጋዮቹን:- እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል አለ።”

የሠርግ ልብስ ያልለበሰው ሰው የሕዝበ ክርስትናን አስመሳይ ክርስቲያኖች ይወክላል። አምላክ እነዚህን ሰዎች የመንፈሳዊ እስራኤላውያን ትክክለኛ መለያ እንዳላቸው አድርጎ በመቁጠር እውቅና አልሰጣቸውም። አምላክ የመንግሥቱ ወራሾች አድርጎ በቅዱስ መንፈሱ አልቀባቸውም። ስለዚህ ጥፋት ወደሚያገኛቸው ወደ ጨለማው ተጥለዋል።

ኢየሱስ “የተጠሩ [“የተጋበዙ፣” NW] ብዙዎች፣ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና” በማለት ምሳሌውን ደመደመ። አዎን፣ የክርስቶስ ሙሽራ አባላት እንዲሆኑ ከእስራኤል ሕዝብ የተጋበዙ ሰዎች ብዙ ነበሩ፤ የተመረጡት ሥጋዊ እስራኤላውያን ግን ጥቂቶች ናቸው። ሰማያዊ ሽልማት ከሚያገኙት 144,000 እንግዶች መካከል አብዛኞቹ እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎች ናቸው። ማቴዎስ 22:​1-14፤ ዘጸአት 19:​1-6፤ ራእይ 14:​1-3

▪ ወደ ሠርጉ ድግስ በመጀመሪያ የተጋበዙት እነማን ነበሩ? ግብዣው የቀረበላቸውስ መቼ ነበር?

▪ ለተጋበዙት ሰዎች ኑ የሚለው ጥሪ በመጀመሪያ የቀረበው መቼ ነበር? ጥሪውን እንዲያደርሱ የተላኩት ባሮችስ እነማን ናቸው?

▪ ሁለተኛው ጥሪ የተሰማው መቼ ነው? ከዚያ በኋላ የተጋበዙትስ እነማን ናቸው?

▪ የሠርግ ልብስ ባልለበሰው ሰው የተመሰሉት እነማን ናቸው?

▪ የተጠሩት ብዙዎችና የተመረጡት ጥቂቶች እነማን ናቸው?