በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሥጋ ደዌ ለያዘው ሰው ርኅራኄ ማሳየት

የሥጋ ደዌ ለያዘው ሰው ርኅራኄ ማሳየት

ምዕራፍ 25

የሥጋ ደዌ ለያዘው ሰው ርኅራኄ ማሳየት

ኢየሱስና አራቱ ደቀ መዛሙርቱ በገሊላ ውስጥ ከከተማ ወደ ከተማ ሲዘዋወሩ ኢየሱስ ስለፈጸማቸው ተአምራት የሚገልጸው ወሬ በአውራጃዋ በሙሉ ተሰራጨ። ኢየሱስ ስለፈጸመው ተአምር የሚገልጸው ወሬ አንድ በሥጋ ደዌ የተያዘ ሰው ወደሚኖርባት ከተማ ደረሰ። ሐኪሙ ሉቃስ “የሥጋ ደዌ የወረሰው” [NW] ሲል ገልጾታል። ይህ አሠቃቂ በሽታ የከፋ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ጊዜ ቀስ በቀስ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን ይቆራርጣል። ስለዚህ ይህ የሥጋ ደዌ የያዘው ሰው በሚያሳዝን ሁኔታ ውስጥ ነበር።

ኢየሱስ ወደ ከተማይቱ ሲመጣ ሕመምተኛው ወደ እሱ ቀረበ። የአምላክ ሕግ በሚለው መሠረት አንድ የሥጋ ደዌ የያዘው ሰው ሌሎች ወደ እሱ በጣም ቀርበው በበሽታው እንዳይያዙ “ርኩስ ርኩስ ነኝ” እያለ መጮኽ አለበት። ሕመምተኛው በፊቱ ተደፍቶ “ጌታ ሆይ፣ ብትወድስ፣ ልታነጻኝ ትችላለህ” ሲል ኢየሱስን ለመነው።

ይህ ሰው በኢየሱስ ላይ እንዴት ያለ እምነት ነበረው! ሆኖም በሽታው በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ጎድቶት ነበር! ኢየሱስ ምን ያደርግ ይሆን? አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር? ኢየሱስ በርኅራኄ ስሜት በመገፋፋት እጁን ዘርግቶ ሰውየውን ዳሰሰውና “እወዳለሁ፣ ንጻ” አለው። ወዲያውኑ የሥጋ ደዌው ለቀቀው።

እንዲህ ያለ ርኅራኄ ያለው ሰው ንጉሥህ እንዲሆን አትፈልግምን? ኢየሱስ፣ የሥጋ ደዌ ይዞት ለነበረው ለዚህ ሰው ያሳየው ርኅራኄ “ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በንጉሣዊ አገዛዙ ወቅት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል። አዎን፣ ኢየሱስ በዚያን ጊዜ መከራና ሥቃይ የደረሰባቸውን ሰዎች ሁሉ ለመርዳት ያለውን ልባዊ ፍላጎት ይፈጽማል።

ይህ ሕመምተኛ ከመፈወሱ በፊት እንኳ የኢየሱስ አገልግሎት በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ስሜት ፈጥሮ ነበር። በኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት ኢየሱስ የተፈወሰውን ሰው “ለማንም አንዳች እንዳትናገር ተጠንቀቅ” ብሎ አዘዘው። ከዚያም “ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ ያዘዘውን አቅርብ” አለው።

ሆኖም ሰውየው በጣም ስለተደሰተ ተአምሩን ሊደብቅ አልቻለም። ሄዶ ወሬውን በየቦታው አዳረሰው። ይህም የሕዝቡን ስሜትና ጉጉት በጣም ሳይቀሰቅሰው አይቀርም። በመሆኑም ኢየሱስ በግልጽ ወደ ከተማ መግባት አልቻለም። ስለዚህ ኢየሱስ ሰው በማይኖርባቸው ራቅ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች ቆየ። ብዙ ሰዎችም ሊሰሙትና ከበሽታቸው ሊፈወሱ ከየቦታው ይመጡ ነበር። ሉቃስ 5:​12-16፤ ማርቆስ 1:​40-45፤ ማቴዎስ 8:​2-4፤ ዘሌዋውያን 13:​45፤ 14:​10-13፤ መዝሙር 72:​13፤ ኢሳይያስ 42:​1, 2

▪ የሥጋ ደዌ ምን ሊያስከትል ይችላል? በሥጋ ደዌ የተያዘ አንድ ሰው ምን ማስጠንቀቂያ ማሰማት ነበረበት?

▪ በሥጋ ደዌ የተያዘ አንድ ሰው ኢየሱስን የለመነው እንዴት ነው? ኢየሱስ ከሰጠው ምላሽስ ምን ልንማር እንችላለን?

▪ የተፈወሰው ሰው ኢየሱስን ሳይታዘዝ የቀረው እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት አስከተለ?