በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የበጎች በረቶችና እረኛው

የበጎች በረቶችና እረኛው

ምዕራፍ 80

የበጎች በረቶችና እረኛው

ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ ዳግመኛ ለይሖዋ በሚወሰንበት የዳግም ምረቃ በዓል ወይም ሃኑካ ላይ ለመገኘት ወደ ኢየሩሳሌም መጥቷል። ከ200 ዓመት ገደማ ቀደም ብሎ በ168 ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት አንቲዮከስ አራተኛ ኢፒፋንስ ኢየሩሳሌምን በመያዝ ቤተ መቅደሱንና መሠዊያውን አርክሶ ነበር። ይሁን እንጂ ከሦስት ዓመታት በኋላ ኢየሩሳሌምን መልሰው ያዙ፤ ቤተ መቅደሱም ዳግመኛ ለአምላክ ተወሰነ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ ቤተ መቅደሱ ዳግመኛ ለአምላክ የሚወሰንበት ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል።

ይህ የቤተ መቅደስ መታደስ በዓል የሚካሄደው በዘመናችን ባለው የጎርጎሮሳውያን የቀን አቆጣጠር ከኅዳር የመጨረሻ አጋማሽ አንስቶ እስከ ታኅሣሥ የመጀመሪያ አጋማሽ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በሚውለው የአይሁዶች ወር ማለትም በኪስሌቭ 25 ነው። ስለዚህ በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የሚከበረው ታሪካዊ የማለፍ በዓል ሊደርስ የቀረው ጊዜ ከመቶ ቀናት ብዙም አይበልጥም። ቀዝቃዛ አየር ያለበት ወቅት ስለነበረ ሐዋርያው ዮሐንስ “ክረምት” ብሎ ጠርቶታል።

ኢየሱስ ስለ ሦስት የበግ በረቶችና መልካም እረኛ ሆኖ ስለሚያከናውነው የሥራ ድርሻ የገለጸበትን አንድ ምሳሌ ተናገረ። በመጀመሪያ የጠቀሰው የበጎች በረት የሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን ዝግጅት ነው። ሕጉ አይሁዶችን ከአምላክ ጋር በተደረገው በዚህ ልዩ ቃል ኪዳን ያልተካተቱት ሕዝቦች ካሏቸው ብልሹ ልማዶች በመለየት እንደ አጥር ሆኖ አገልግሏል። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፤ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው።”

ሌሎች ሰዎች ተነስተው መሲሕ ወይም ክርስቶስ ነኝ ብለው ነበር፤ ሆኖም ኢየሱስ እንዲህ በማለት የተናገረለት እውነተኛው እረኛ አልነበሩም:- “ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፣ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል። . . . ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፣ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና።”

የመጀመሪያው የበጎች በረት “በረኛ” አጥማቂው ዮሐንስ ነው። ዮሐንስ የበሩ ጠባቂ እንደመሆኑ መጠን ኢየሱስ ወደ መስክ እንደሚያሰማራቸው ለምሳሌያዊዎቹ በጎች በመግለጽ በሩን ለኢየሱስ “ይከፍትለታል።” ኢየሱስ በስም ጠርቶ የሚወስዳቸው እነዚህ በጎች ትንሽ ቆየት ብሎ ወደ ሌላ የበጎች በረት እንዲገቡ ይደረጋል። ኢየሱስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ እኔ የበጎች በር ነኝ” ሲል ገልጿል፤ ይህም የአንድ አዲስ የበጎች በረት በር መሆኑን የሚያሳይ ነው። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አዲሱን ቃል ኪዳን ሲያቋቁምና ከዚያ በኋላ በተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል ላይ ከሰማይ መንፈስ ቅዱስ ሲወርድባቸው ወደዚህ አዲስ የበጎች በረት እንዲገቡ ተፈቅዶላቸዋል።

ኢየሱስ የሥራ ድርሻውን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ በመስጠት እንዲህ አለ:- “በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፣ ይገባልም ይወጣልም መሰማሪያም ያገኛል። . . . እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። . . . መልካም እረኛ እኔ ነኝ፣ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።”

ከጥቂት ጊዜ በፊት ኢየሱስ “አንተ ታናሽ መንጋ፣ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ” በማለት ተከታዮቹን አጽናንቷቸው ነበር። በመጨረሻ ቁጥሩ 144,000 የሚደርሰው ይህ ታናሽ መንጋ ወደ አዲሱ ወይም ወደ ሁለተኛው የበጎች በረት ይገባል። ሆኖም ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፣ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ።”

‘ሌሎቹ በጎች ከዚህ በረት’ ስላልሆኑ ሌላ ሦስተኛ በረት ውስጥ ያሉ በጎች መሆን አለባቸው። እነዚህ መጨረሻ ላይ የተጠቀሱት ሁለት በረቶች ወይም የበግ ጉረኖዎች የተለያየ ተስፋ አላቸው። በአንደኛው በረት ውስጥ ያለው “ታናሽ መንጋ” አባላት ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ይገዛሉ፤ በሌላኛው በረት ውስጥ ያሉት “ሌሎች በጎች” ደግሞ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ይኖራሉ። ሆኖም፣ ምንም እንኳ በሁለት በረቶች ውስጥ ያሉ ቢሆንም ኢየሱስ ‘በአንድ እረኛ’ ሥር ያሉ ‘አንድ መንጋ እንደሚሆኑ’ ስለተናገረ በጎቹ የቅናት ስሜት አያድርባቸውም፤ በመካከላቸው መከፋፈል እንዳለ አድርገውም አያስቡም።

መልካሙ እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ በሁለቱም በረቶች ውስጥ ላሉት በጎች በፈቃደኝነት ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል። “እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ” ብሏል። “ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።” ኢየሱስ ይህን ሲናገር በአይሁዶች መካከል መከፋፈል ተፈጠረ።

ከሕዝቡ መካከል ብዙዎቹ “ጋኔን አለበት አብዶአልም፤ ስለ ምንስ ትሰሙታላችሁ?” አሉ። ሌሎቹ ግን “ይህ ጋኔን ያለበት ሰው ቃል አይደለም” አሉ። አክለውም “ጋኔን የዕውሮችን ዓይኖች ሊከፍት ይችላልን?” በማለት ተናገሩ። ይህን ያሉት ኢየሱስ ከሁለት ወራት በፊት የፈወሰውን ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደ ሰው በማውሳት እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ዮሐንስ 10:​1-22፤ 9:​1-7፤ ሉቃስ 12:​32፤ ራእይ 14:​1, 3፤ 21:​3, 4፤ መዝሙር 37:​29

▪ ቤተ መቅደሱ ለአምላክ በድጋሚ የተወሰነበት በዓል ምንድን ነው? የሚከበረውስ መቼ ነው?

▪ የመጀመሪያው የበጎች በረት ምንድን ነው? በር ጠባቂውስ ማን ነው?

▪ በር ጠባቂው ለእረኛው የሚከፍትለት እንዴት ነው? ከዚያ በኋላስ በጎቹ ወዴት እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል?

▪ የመልካሙ እረኛ ሁለት በረቶች አባላት እነማን ናቸው? ስንት መንጋስ ይሆናሉ?