በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ ድምፅ ለሦስተኛ ጊዜ ተሰማ

የአምላክ ድምፅ ለሦስተኛ ጊዜ ተሰማ

ምዕራፍ 104

የአምላክ ድምፅ ለሦስተኛ ጊዜ ተሰማ

ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሆኖ በቅርቡ ስለሚደርስበት ሞት እያሰበ በመጨነቅ ላይ ነበር። በጣም ያሳሰበው ነገር ሁኔታው በአባቱ ስም ላይ የሚያስከትለው ውጤት ነበር። ስለዚህ “አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው” ሲል ጸለየ።

በዚህ ጊዜ ከሰማይ የመጣ አንድ ታላቅ ድምፅ “አከበርሁት ደግሞም አከብረዋለሁ” ሲል አወጀ።

በቦታው ቆሞ የነበረው ሕዝብ ግራ ተጋባ። አንዳንዶቹ “መልአክ ተናገረው” አሉ። ሌሎቹ ደግሞ ነጎድጓድ ነው አሉ። የተናገረው ግን ይሖዋ አምላክ ነበር! ሆኖም ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ የአምላክ ድምፅ ሲሰማ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አልነበረም።

ከሦስት ዓመት ተኩል በፊት ኢየሱስ በተጠመቀበት ጊዜ አምላክ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ ስለ ኢየሱስ ሲናገር አጥማቂው ዮሐንስ ሰምቶ ነበር። ከዚያም ከዚህ በፊት በነበረው ዓመት ከተከበረው የማለፍ በዓል በኋላ ጥቂት ቆየት ብሎ ኢየሱስ በያዕቆብ፣ በዮሐንስና በጴጥሮስ ፊት ተአምራዊ በሆነ መንገድ በተለወጠበት ጊዜ አምላክ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” ብሎ ሲናገር ሰምተዋል። አሁን ደግሞ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት አራት ቀናት ቀደም ብሎ ኒሳን 10 ላይ ለሦስተኛ ጊዜ የአምላክ ድምፅ እንደገና በሰዎች ፊት ተሰማ። ሆኖም ይሖዋ በዚህኛው ጊዜ የተናገረው በጣም ብዙ ሰዎች መስማት እንዲችሉ ነው!

ኢየሱስ “ይህ ድምፅ ስለ እናንተ መጥቶአል እንጂ ስለ እኔ አይደለም” ሲል ገለጸ። ኢየሱስ በእርግጥም የአምላክ ልጅና ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነበር። ኢየሱስ በመቀጠል “አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደርሶአል” ሲል ተናገረ፤ “አሁን የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጭ ይጣላል።” ኢየሱስ በታማኝነት ያሳለፈው ሕይወት የዚህ ዓለም ገዥ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ‘መጣል’ ማለትም መጥፋት እንደሚገባው የሚያረጋግጥ ነው።

ኢየሱስ እየቀረበ ያለው ሞቱ የሚያስከትለውን ውጤት በማመልከት “እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ” ሲል ተናገረ። ኢየሱስ በሞቱ አማካኝነት ሌሎች የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ወደ እርሱ የሚስባቸው በመሆኑ የእሱ መሞት በምንም መንገድ ሽንፈት ሊሆን አይችልም።

ሆኖም ሕዝቡ እንዲህ ሲሉ ተቃወሙ:- “እኛስ ክርስቶስ ለዘላለም እንዲኖር ከሕጉ ሰምተናል፤ አንተስ የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ይል ዘንድ እንዲያስፈልገው እንዴት ትላለህ? ይህ የሰው ልጅ ማን ነው?”

የራሱን የአምላክን ድምፅ መስማትን ጨምሮ ብዙ ማስረጃዎችን የተመለከቱ ቢሆንም አብዛኞቹ ኢየሱስ እውነተኛው የሰው ልጅ ማለትም ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ መሆኑን አላመኑም። ሆኖም ኢየሱስ ከስድስት ወራት በፊት በዳስ በዓል ላይ እንዳደረገው ሁሉ አሁንም እርሱ “ብርሃን” እንደሆነ በመናገር አድማጮቹን “የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃኑ እመኑ” በማለት አበረታታቸው። ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ አካባቢውን ለቆ ተሰወረባቸው። ይህን ያደረገው ሕይወቱ አደጋ ላይ ወድቆ ስለነበረ እንደሆነ ግልጽ ነው።

አይሁዶች በኢየሱስ አለማመናቸው ኢሳይያስ ‘ለመፈወስ እንዳይመለሱ ዓይኖቻቸው ስለታወሩና ልባቸው ስለደነደነ ሰዎች’ የተናገረው ቃል እንዲፈጸም አድርጓል። ኢሳይያስ ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በይሖዋ ዘንድ የነበረውን ክብር ጨምሮ የይሖዋን ሰማያዊ አደባባዮች በራእይ ተመልክቷል። ሆኖም አይሁዶች ኢሳይያስ በጻፈው ትንቢት ፍጻሜ መሠረት ይህ ሰው ተስፋ የተሰጠበት አዳኛቸው መሆኑን የሚያሳየውን ማስረጃ ለመቀበል አሻፈረኝ ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ብዙዎች፣ አልፎ ተርፎም ከሕዝቡ አለቆች (የአይሁድ ከፍተኛ ሸንጎ የሆነው የሳንሄድሪን አባላት እንደሆኑ ግልጽ ነው) መካከል አንዳንዶቹ በኢየሱስ አምነዋል። ከእነዚህ የሕዝብ አለቆች መካከል ሁለቱ ኒቆዲሞስና የአርማትያሱ ዮሴፍ ናቸው። ሆኖም የሕዝብ አለቆቹ በምኩራብ ውስጥ ያላቸውን ቦታ እንዳያጡ በመፍራት ለጊዜውም ቢሆን እምነታቸውን ከመግለጽ ወደ ኋላ ብለዋል። እነዚህ ሰዎች ይህን ባለማድረጋቸው ምንኛ ተጎድተዋል!

ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “በእኔ የሚያምን በላከኝ ማመኑ ነው እንጂ በእኔ አይደለም፤ እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል። . . . ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም። . . . እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል።”

ይሖዋ ለሰው ዘር ዓለም ያለው ፍቅር በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ መዳን እንዲችሉ ኢየሱስን ወደ ምድር እንዲልክ ገፋፍቶታል። የሰዎች መዳን የሚወሰነው አምላክ ኢየሱስን እንዲያስተምር ያዘዘውን ነገር በመታዘዛቸው ላይ ነው። ፍርዱ የሚካሄደው “በመጨረሻው ቀን” ማለትም በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ነው።

ኢየሱስ እንዲህ ሲል ደመደመ:- “እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ። ትእዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደ ሆነች አውቃለሁ። ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደ ነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ።” ዮሐንስ 12:​28-50፤ 19:​38, 39፤ ማቴዎስ 3:​17፤ 17:​5፤ ኢሳይያስ 6:​1, 8-10

▪የአምላክ ድምፅ ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የተሰማው በየትኞቹ ሦስት ጊዜያት ነው?

▪ ነቢዩ ኢሳይያስ የኢየሱስን ክብር የተመለከተው እንዴት ነው?

▪ በኢየሱስ ያመኑት የሕዝብ አለቆች እነማን ናቸው? ሆኖም በእሱ ላይ ያላቸውን እምነት በሰው ፊት ያልገለጹት ለምንድን ነው?

▪ ‘የመጨረሻው ቀን’ የተባለው የትኛው ጊዜ ነው? በዚያን ጊዜ ሰዎች የሚፈረድባቸው በምን መሠረት ይሆናል?