በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአባትነት ጥያቄ

የአባትነት ጥያቄ

ምዕራፍ 69

የአባትነት ጥያቄ

በበዓሉ ወቅት ኢየሱስ ከአይሁድ መሪዎች ጋር ያደረገው ውይይት ይበልጥ እየከረረ ሄደ። “የአብርሃም ዘር መሆናችሁንስ አውቃለሁ” ሲል ኢየሱስ ተናገረ፤ “ነገር ግን ቃሌ በእናንተ አይኖርምና ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ። እኔ በአባቴ ዘንድ ያየሁትን እናገራለሁ፤ እናንተም ደግሞ በአባታችሁ ዘንድ ያያችሁትን ታደርጋላችሁ።”

ኢየሱስ ምንም እንኳ አባታቸውን ለይቶ ባይጠቅስም የእነሱ አባት ከእሱ አባት የተለየ መሆኑን ገልጿል። የሃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ የተናገረው ማንን በአእምሮው ይዞ እንደሆነ ባለማወቅ “አባታችንስ አብርሃም ነው” አሉት። የአምላክ ወዳጅ የነበረው የአብርሃም ዓይነት እምነት እንዳላቸው አድርገው ያስቡ ነበር።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ “የአብርሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር” በማለት የሰጣቸው መልስ አበሳጫቸው። በእርግጥም እውነተኛ ልጅ አባቱን ይመስላል። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:- “ነገር ግን አሁን ከእግዚአብሔር የሰማሁትን እውነት የነገርኋችሁን ሰው ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ፤ አብርሃም እንዲህ አላደረገም።” ስለዚህ ኢየሱስ በድጋሚ “እናንተ የአባታችሁን ሥራ ታደርጋላችሁ” አላቸው።

አሁንም ኢየሱስ ስለ ማን እየተናገረ እንዳለ አልገባቸውም። “እኛስ ከዝሙት አልተወለድንም” በማለት እውነተኛ የአብርሃም ልጆች ነን ብለው ተከራከሩ። በመሆኑም እንደ አብርሃም እውነተኛ አምላኪዎች ነን በማለት “አንድ አባት አለን እርሱም እግዚአብሔር ነው” ሲሉ ተናገሩ።

ሆኖም በእርግጥ አምላክ አባታቸው ነበርን? ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው:- “እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና። ንግግሬን የማታስተውሉ ስለ ምንድር ነው?”

ኢየሱስ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች እርሱን አንቀበልም ማለታቸው የሚያስከትልባቸውን መዘዝ ሊያመለክታቸው ሞክሯል። አሁን ግን በቀጥታ “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ” አላቸው። ዲያብሎስ ምን ዓይነት አባት ነው? ኢየሱስ ዲያብሎስ ነፍሰ ገዳይ እንደሆነ ከመግለጹም በላይ “ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነው” ብሏል። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ደመደመ:- “ከእግዚአብሔር የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል፤ እናንተ ግን ከእግዚአብሔር አይደላችሁምና ስለዚህ አትሰሙም።”

አይሁዶች ኢየሱስ በሰነዘረባቸው ውግዘት በመናደድ “ሳምራዊ እንደ ሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ በማለታችን እኛ መልካም እንል የለምን?” አሉት። አይሁዶች ሳምራውያንን ይጠሏቸው ስለነበረ “ሳምራዊ” የሚለው ቃል ንቀትንና ነቀፋን ለመግለጽ የገባ ቃል ነው።

ኢየሱስ ሳምራዊ ነህ በማለት በንቀት የሰነዘሩበትን ትችት ወደ ጎን በመተው “እኔስ ጋኔን የለብኝም፤ ነገር ግን አባቴን አከብራለሁ እናንተም ታዋርዱኛላችሁ” አላቸው። ኢየሱስ በመቀጠል “ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አያይም” በማለት አስደናቂ ተስፋ ሰጠ። እርግጥ ኢየሱስ እሱን የሚከተሉ ሁሉ ቃል በቃል ሞትን አያዩም ማለቱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ዘላለማዊ ሞት ወይም ትንሣኤ የሌለው “ሁለተኛ ሞት” አይደርስባቸውም ማለቱ ነበር።

ይሁን እንጂ አይሁዶቹ ኢየሱስ የተናገረውን ቃል የተረዱት ቃል በቃል ነበር። በመሆኑም እንዲህ አሉ:- “ጋኔን እንዳለብህ አሁን አወቅን። አብርሃም ስንኳ ሞተ ነቢያትም፤ አንተም:- ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አይቀምስም ትላለህ። በእውኑ አንተ ከሞተው ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህን? ነቢያትም ሞቱ፤ ራስህን ማንን ታደርጋለህ?”

ይህ ሁሉ ውይይት ሲደረግ ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ መሆኑን ለእነዚህ ሰዎች እየጠቆማቸው እንደነበረ ግልጽ ነው። ሆኖም ኢየሱስ ስለ ማንነቱ ለቀረበለት ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ አልሰጠም፤ ከዚህ ይልቅ እንዲህ አለ:- “እኔ ራሴን ባከብር ክብሬ ከንቱ ነው፤ የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው፤ አላወቃችሁትምም፣ እኔ ግን አውቀዋለሁ። አላውቀውም ብል እንደ እናንተ ሐሰተኛ በሆንሁ።”

ኢየሱስ በመቀጠል ታማኙን አብርሃም ድጋሚ በመጥቀስ እንዲህ አለ:- “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፣ አየም ደስም አለው።” አዎን፣ አብርሃም ተስፋ የተሰጠበትን መሲሕ መምጣት በእምነት ዓይኑ ተመልክቷል። አይሁዶች የተናገረውን ባለማመን “ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን?” አሉት።

ኢየሱስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ” ሲል መለሰላቸው። ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ኃያል መንፈሳዊ አካል ሆኖ በሰማይ ይኖር በነበረበት ጊዜ የነበረውን ሕልውና ማመልከቱ ነበር።

ኢየሱስ ከአብርሃም በፊት እኖር ነበር በማለቱ አይሁዶች በጣም ተናደዱና ሊወግሩት ድንጋይ አነሱ። ሆኖም ተደበቀና ምንም ጉዳት ሳይደርስበት ከቤተ መቅደሱ ወጣ። ዮሐንስ 8:​37-59፤ ራእይ 3:​14፤ 21:​8

▪ ኢየሱስ እሱና ጠላቶቹ የተለያዩ አባቶች እንዳሏቸው ያመለከተው እንዴት ነው?

▪ አይሁዶች ኢየሱስን ሳምራዊ ብለው መጥራታቸው ምን ትርጉም አለው?

▪ ኢየሱስ ተከታዮቹ ሞትን እንደማያዩ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?