በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኢሳይያስን ትንቢት መፈጸም

የኢሳይያስን ትንቢት መፈጸም

ምዕራፍ 33

የኢሳይያስን ትንቢት መፈጸም

ኢየሱስ ፈሪሳውያንና የሄሮድስ የፖለቲካ ቡድን ተከታዮች እሱን ለመግደል እንዳሴሩ ካወቀ በኋላ አካባቢውን ለቅቆ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ገሊላ ባሕር ሄደ። ከመላው የፍልስጤም ምድር አልፎ ተርፎም ከፍልስጤም ድንበር ውጪ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች እሱ ወዳለበት ጎረፉ። ብዙ ሰዎችን ፈወሰ፤ በዚህም የተነሣ በከባድ በሽታ የሚሠቃዩ ሁሉ እሱን ለመንካት ይንጠራሩ ነበር።

ሰዎቹ በጣም ብዙ ስለነበሩ ኢየሱስ አገልግሎቱን ጀምሮ እስኪጨርስ ድረስ ሊጠቀምበት የሚችል ጀልባ እንዲያመጡለት ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። ከባሕሩ ዳርቻ ራቅ በማለት ሕዝቡ እንዳይጋፉት ማድረግ ይችላል። በጀልባው ላይ ሆኖ ሊያስተምራቸው ወይም በባሕሩ ዳርቻ ወደ ሌላ ቦታ በመንቀሳቀስ በዚያ ያሉትን ሰዎች መርዳት ይችላል።

ደቀ መዝሙሩ ማቴዎስ “በነቢዩ በኢሳይያስ የተባለው” ነገር ኢየሱስ ባከናወነው ሥራ እንደተፈጸመ ገልጿል። ከዚያም ማቴዎስ ኢየሱስ የፈጸመውን ትንቢት ጠቅሶታል:-

“እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፣ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፣ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል። አይከራከርም አይጮህምም፣ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፣ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም። አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”

አምላክ ደስ የተሰኘበት የተወደደ አገልጋይ የተባለው ኢየሱስ እንደሆነ ግልጽ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ በሐሰት ሃይማኖታዊ ወጎች የተጋረደውን እውነተኛ ፍትህ ግልጽ አድርጓል። ፈሪሳውያን የአምላክን ሕግ አግባብ ባልሆነ መንገድ በመተርጎማቸው የተነሣ በሰንበት ቀን አንድን የታመመ ሰው እንኳ አይረዱም ነበር! ኢየሱስ የአምላክን ፍትህ ግልጽ በማድረግ ሰዎችን ሸክም ሆነውባቸው ከነበሩ አግባብነት ከሌላቸው ወጎች አላቋቸዋል። ይህንንም በማድረጉ የሃይማኖት መሪዎቹ ሊገድሉት ሞከሩ።

‘አይከራከርም፣ ድምፁም በአደባባይ እንዲሰማ አይጮህም’ ማለት ምን ማለት ነው? ኢየሱስ ሰዎችን ሲፈውስ ‘ማንነቱን እንዳይገልጹ አጥብቆ ያስጠነቅቃቸው ነበር።’ በየመንገዱ ስለ እሱ እንዲለፈፍ ወይም በስሜት የተዛባ ወሬ ከአንዱ ወደ ሌላው እንዲዛመት አልፈለገም።

በተጨማሪም ኢየሱስ በምሳሌያዊ ሁኔታ ታጥፎ በእግር እንደተቀጠቀጠ ሸምበቆ ለሆኑት ሰዎች አጽናኝ መልእክት ያሰማቸው ነበር። ሊጠፋ እንደተቃረበ የጥዋፍ ክር ነበሩ። ኢየሱስ የተቀጠቀጠ ሸምበቆን አይሰብርም፤ ወይም ሊጠፋ የተቃረበን የሚጤስ ክር አያጠፋም። ሆኖም በአሳቢነትና በፍቅር መንፈስ ቅኖችን በዘዴ ቀና ያደርጋቸዋል። በእርግጥም አሕዛብ በኢየሱስ ተስፋ ማድረግ ይችላሉ! ማቴዎስ 12:​15-21፤ ማርቆስ 3:​7-12፤ ኢሳይያስ 42:​1-4

▪ ኢየሱስ ፍትሕን ግልጽ የሚያደርገውና የማይከራከረው ወይም ድምፁን በአደባባይ የማያሰማው እንዴት ነው?

▪ እንደተቀጠቀጠ ሸምበቆና እንደ ጥዋፍ ክር የሆኑት እነማን ናቸው? ኢየሱስ የያዛቸውስ እንዴት ነበር?