በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኢየሱስ ጥምቀት

የኢየሱስ ጥምቀት

ምዕራፍ 12

የኢየሱስ ጥምቀት

ዮሐንስ መስበክ ከጀመረ ከስድስት ወር ገደማ በኋላ ኢየሱስ እሱ ወዳለበት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መጣ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ 30 ዓመት ሆኖት ነበር። ወደ ዮሐንስ የመጣው ለምንድን ነው? እንዲሁ ሊጠይቀው አስቦ ነውን? ዮሐንስ እያከናወነው ያለው ሥራ እንዴት እየተካሄደ እንዳለ ለማየት ብሎ ነውን? አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ እንዲያጠምቀው ዮሐንስን ጠየቀው።

ወዲያውኑ ዮሐንስ “እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን?” ሲል ለማከላከል ሞከረ። ዮሐንስ ከአክስቱ የተወለደው ኢየሱስ የአምላክ ልዩ ልጅ መሆኑን ያውቃል። እንዲያውም ማርያም ኢየሱስን ጸንሳ ሳለ ልትጠይቃቸው ስትመጣ ዮሐንስ በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሆኖ በደስታ ዘሏል! የዮሐንስ እናት ኤልሳቤጥ በኋላ ይህን ለዮሐንስ እንደነገረችው ምንም አያጠራጥርም። በተጨማሪም መልአኩ ስለ ኢየሱስ መወለድ የተናገረውን ነገርና ኢየሱስ በተወለደበት ሌሊት ለእረኞች ስለ ታዩት መላእክት እንደምትነግረው የታወቀ ነው።

ስለዚህ ኢየሱስ ለዮሐንስ እንግዳ ሰው አልነበረም። በተጨማሪም ዮሐንስ የእሱ ጥምቀት ለኢየሱስ የታሰበ አለመሆኑን ያውቃል። የእሱ ጥምቀት የሚያገለግለው ከኃጢአታቸው ንስሐ ለገቡ ሰዎች ነው። ኢየሱስ ደግሞ ምንም ኃጢአት የለበትም። ሆኖም ዮሐንስ ቢቃወምም እንኳ ኢየሱስ በአቋሙ በመጽናት “አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል” አለው።

ኢየሱስ መጠመቁ ተገቢ የነበረው ለምንድን ነው? የኢየሱስ ጥምቀት ለኃጢአት ንስሐ መግባቱን ሳይሆን የአባቱን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን ማቅረቡን የሚያሳይ ምልክት ስለነበረ ነው። ኢየሱስ አናጢ ሆኖ ሲሠራ ቆይቷል፤ አሁን ግን ይሖዋ ወደ ምድር ሲልከው እንዲያከናውነው የሰጠውን አገልግሎት የሚጀምርበት ጊዜ ደርሷል። ዮሐንስ ኢየሱስን በሚያጠምቅበት ጊዜ እንግዳ የሆነ ነገር ይፈጸማል ብሎ ጠብቆ ነበር ብለህ ታስባለህን?

ዮሐንስ ከጊዜ በኋላ እንዲህ ሲል ሁኔታውን ገልጿል:- “በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ:- መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፣ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ።” ስለዚህ ዮሐንስ እርሱ በሚያጠምቀው ሰው ላይ የአምላክ መንፈስ እንደሚወርድ ይጠብቅ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ ከውኃው ውስጥ በወጣ ጊዜ ‘የአምላክ መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድበት’ ሲያይ ይህን ያህል አልተገረመ ይሆናል።

ሆኖም ኢየሱስ ሲጠመቅ ከዚህም ሌላ የተፈጸመ ነገር ነበር። ‘ሰማያት ተከፈቱለት።’ ይህ ምን ማለት ነው? ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ሲጠመቅ ሰው ከመሆኑ በፊት በሰማይ ያሳለፈውን ሕይወት ማስታወስ ቻለ ማለት ነው። በመሆኑም አሁን ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት በሰማይ ሲኖር አምላክ የነገረውን ነገር ሁሉ ጨምሮ የይሖዋ አምላክ መንፈሳዊ ልጅ ሆኖ ያሳለፈውን ሕይወት ሙሉ በሙሉ አስታወሰ።

ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ሲጠመቅ አንድ ድምፅ ከሰማይ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” አለ። ይህ ድምፅ የማን ነው? የኢየሱስ የራሱ ድምፅ ነውን? አይደለም! የእግዚአብሔር ድምፅ ነው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንጂ አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ራሱ እግዚአብሔር እንዳይደለ በግልጽ እንረዳለን።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ ልክ እንደ መጀመሪያው ሰው እንደ አዳም የአምላክ ሰብዓዊ ልጅ ነበር። ደቀ መዝሙሩ ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ጥምቀት ከገለጸ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ኢየሱስም ሊያስተምር ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ሆኖት ነበር፤ እንደመሰላቸው የዮሴፍ ልጅ ሆኖ፣ የኤሊ ልጅ፣ . . . የዳዊት ልጅ፣ . . . የአብርሃም ልጅ፣ . . . የኖኅ ልጅ፣ . . . የአዳም ልጅ፣ የእግዚአብሔር ልጅ።”

አዳም ‘የአምላክ ሰብዓዊ ልጅ’ እንደነበረ ሁሉ ኢየሱስም የአምላክ ሰብዓዊ ልጅ ነበር። የኢየሱስን ሕይወት ስንመረምር በግልጽ መረዳት እንደምንችለው ኢየሱስ እስከ ዛሬ ድረስ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሲጠመቅ የአምላክ መንፈሳዊ ልጅም በመሆን ከአምላክ ጋር አዲስ ዝምድና መሥርቷል። በዚህ ጊዜ አምላክ ኩነኔ ውስጥ ለገቡት የሰው ልጆች ሰብዓዊ ሕይወቱን ለዘላለም መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብበትን የሕይወት ጎዳና እንዲጀምር በማድረግ ወደ ሰማይ እንደጠራው የሚቆጠር ነበር። ማቴዎስ 3:​13-17፤ ሉቃስ 3:​21-38፤ 1:​34-36, 44፤ 2:​10-14፤ ዮሐንስ 1:​32-34፤ ዕብራውያን 10:​5-9

▪ ኢየሱስ ለዮሐንስ እንግዳ ሰው ያልሆነው ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ ምንም ኃጢአት ያልፈጸመ ሰው ሆኖ ሳለ የተጠመቀው ለምንድን ነው?

▪ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ከሚያውቀው አንጻር ሲታይ የአምላክ መንፈስ በኢየሱስ ላይ ሲወርድ እምብዛም አልተገረመም ይሆናል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?