በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የክርስቶስ መንግሥታዊ ክብር አጭር እይታ

የክርስቶስ መንግሥታዊ ክብር አጭር እይታ

ምዕራፍ 60

የክርስቶስ መንግሥታዊ ክብር አጭር እይታ

ኢየሱስ ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር መጥቷል። ሐዋርያቱን ጨምሮ ብዙ ሕዝብ እያስተማረ ነው። የሚከተለውን አስገራሚ መግለጫ ሰጠ:- “እውነት እላችኋለሁ፣ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።”

ደቀ መዛሙርቱ ‘ኢየሱስ ምን ማለቱ ይሆን?’ ብለው ሳያስቡ አይቀርም። ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ወጣ። ደቀ መዛሙርቱ እንቅልፍ እንቅልፍ ብሏቸው ስለነበር ይህ የሆነው ማታ ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ እየጸለየ ሳለ በፊታቸው ተለወጠ። ፊቱ እንደ ፀሐይ ማብራት ጀመረ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ።

ከዚያም ሁለት ሰዎች ማለትም “ሙሴና ኤልያስ” የተባሉ ተገለጡና ‘በኢየሩሳሌም ስለሚፈጸመው ስለ መውጣቱ’ ከኢየሱስ ጋር ይነጋገሩ ጀመር። መውጣት ሲባል የኢየሱስን ሞትና ከዚያ በኋላ የሚከናወነውን ትንሣኤውን እንደሚያመለክት መረዳት ይቻላል። ስለዚህ ይህ ውይይት በኢየሱስ ላይ የሚደርሰው የውርደት ሞት ጴጥሮስ እንደተመኘው የሚቀር ነገር እንዳልሆነ ያረጋግጣል።

ደቀ መዛሙርቱ አሁን ሙሉ በሙሉ ንቁ ሆነው በመገረም እየተመለከቱና እያዳመጡ ነው። ምንም እንኳ ነገሩ ራእይ ቢሆንም በእውን እየተፈጸመ ያለ ነገር ይመስል ስለነበር ጴጥሮስም እንዲህ በማለት በትዕይንቱ መሳተፍ ጀመረ:- “ጌታ ሆይ፣ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፣ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ።”

ጴጥሮስ እየተናገረ ሳለ አንድ ብሩህ ደመና ሸፈናቸው፤ ከደመናውም ውስጥ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ። ደቀ መዛሙርቱ ድምፁን ሲሰሙ በፊታቸው ተደፉ። ሆኖም ኢየሱስ “ተነሡ አትፍሩም” አላቸው። ሲነሱ በቦታው የነበረው ኢየሱስ ብቻ ነበር።

በሚቀጥለው ቀን ከተራራው እየወረዱ ሳለ ኢየሱስ “የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ” ብሎ አዘዛቸው። ኤልያስ በራእዩ ላይ መታየቱ በደቀ መዛሙርቱ አእምሮ ውስጥ ጥያቄ ፈጠረ። “ጻፎች:- ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ ይገባዋል ስለ ምን ይላሉ?” ብለው ጠየቁት።

ኢየሱስ “ኤልያስ ከዚህ በፊት መጣ፤ . . . አላወቁትም” አላቸው። ኢየሱስ የኤልያስን ዓይነት ሚና ስለተጫወተው ስለ አጥማቂው ዮሐንስ መናገሩ ነበር። ኤልያስ ለኤልሳዕ መንገዱን እንዳዘጋጀ ሁሉ ዮሐንስም ለክርስቶስ መንገዱን አዘጋጅቷል።

ይህ ራእይ ኢየሱስንም ሆነ ደቀ መዛሙርቱን ምንኛ የሚያበረታ ነው! ራእዩ የክርስቶስ መንግሥታዊ ክብር አጭር እይታ ነበር። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ከአንድ ሳምንት በፊት በገባው ቃል መሠረት “የሰው ልጅ በመንግሥቱ ክብር ሲመጣ” አይተዋል ማለት ይቻላል። ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ጴጥሮስ ‘ከእርሱ ጋር በቅዱሱ ተራራ ላይ በነበሩበት ጊዜ የክርስቶስን ግርማ እንደተመለከቱ’ በመግለጽ ጽፏል።

ፈሪሳውያን ኢየሱስ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተስፋ የተሰጠበት አምላክ የመረጠው ንጉሥ መሆኑን ለማረጋገጥ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠይቀውት ነበር። እነርሱ እንዲህ ዓይነት ምልክት አልተሰጣቸውም። በሌላ በኩል ግን የኢየሱስ የቅርብ ደቀ መዛሙርት የመንግሥቱን ትንቢቶች የሚያረጋግጠውን የኢየሱስን ተአምራዊ ለውጥ እንዲያዩ ተደርጓል። በመሆኑም ጴጥሮስ ከጊዜ በኋላ “እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን” ሲል ጽፏል። ማቴዎስ 16:​13, ማቴ 16:28 እስከ 17:​13፤ ማርቆስ 9:​1-13፤ ሉቃስ 9:​27-37፤ 2 ጴጥሮስ 1:​16-19

▪ አንዳንዶች ሞትን ከመቅመሳቸው በፊት ክርስቶስ በመንግሥቱ ሲመጣ የሚያዩት እንዴት ነው?

▪ በራእዩ ላይ ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር የተነጋገሩት ስለ ምን ነገር ነው?

▪ ራእዩ የደቀ መዛሙርቱን እምነት ለማጠንከር የሚረዳ የሆነው ለምንድን ነው?