በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወይኑ አትክልት ሠራተኞች

የወይኑ አትክልት ሠራተኞች

ምዕራፍ 97

የወይኑ አትክልት ሠራተኞች

ኢየሱስ “ብዙዎቹ ፊተኞች ኋለኞች፣ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ” ሲል ተናግሯል። አሁን አንድ ታሪክ በመናገር ይህ ምን ማለት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ። “መንግሥተ ሰማያት” ሲል ታሪኩን መናገር ጀመረ፤ “ለወይኑ አትክልት ሠራተኞችን ሊቀጥር ማልዶ የወጣ ባለቤት ሰውን ትመስላለች።”

ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “[ባለቤቱ] ሠራተኞችንም በቀን አንድ ዲናር ተስማምቶ ወደ ወይኑ አትክልት ሰደዳቸው። በሦስት ሰዓትም ወጥቶ ሥራ የፈቱ ሌሎችን በአደባባይ ቆመው አየ፣ እነዚያንም:- እናንተ ደግሞ ወደ ወይኔ አትክልት ሂዱ የሚገባውንም እሰጣችኋለሁ አላቸው። እነርሱም ሄዱ። ደግሞም በስድስትና በዘጠኝ ሰዓት ወጥቶ እንዲሁ አደረገ። በአሥራ አንደኛውም ሰዓት ወጥቶ ሌሎችን ቆመው አገኘና:- ሥራ ፈትታችሁ ቀኑን ሁሉ በዚህ ስለ ምን ትቆማላችሁ? አላቸው። የሚቀጥረን ስለ አጣን ነው አሉት። እርሱም:- እናንተ ደግሞ ወደ ወይኔ አትክልት ሂዱ . . . አላቸው።”

ባለቤቱ ወይም የወይኑ አትክልት ባለ ንብረት ይሖዋ አምላክ ሲሆን የወይኑ አትክልት ደግሞ የእስራኤል ሕዝብ ነው። በወይኑ አትክልት ሥፍራ የሚሠሩት ሠራተኞች ደግሞ በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ የተካተቱት ሰዎች በተለይ ደግሞ በሐዋርያት ዘመን ይኖሩ የነበሩት አይሁዶች ናቸው። የደመወዝ ስምምነት የተደረገው ሙሉ ቀን ከሚሠሩት ሠራተኞች ጋር ብቻ ነው። ለአንድ ቀን ሥራ የሚከፈለው ደመወዝ አንድ ዲናር ነው። በ3 ሰዓት፣ በ6 ሰዓት፣ በ9 ሰዓትና በ11 ሰዓት የተጠሩት ሠራተኞች የሠሩት በቅደም ተከተላቸው መሠረት 9፣ 6፣ 3፣ እና 1 ሰዓት ብቻ ነው።

አሥራ ሁለት ሰዓት ወይም ሙሉ ቀን የሠሩት ሠራተኞች ያለማቋረጥ በሃይማኖታዊ አገልግሎት የተጠመዱትን የአይሁድ መሪዎች ያመለክታሉ። አብዛኛውን የሕይወት ዘመናቸውን በዓሣ አጥማጅነት ወይም በሌላ ሰብዓዊ ሥራ ተጠምደው ካሳለፉት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የተለዩ ናቸው። ‘ባለቤቱ’ ደቀ መዛሙርቱ ይሆኑ ዘንድ እነዚህን ሰዎች እንዲሰበስብ ኢየሱስ ክርስቶስን የላከው በ29 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የመከር ወራት ነበር። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ‘የኋለኞቹ’ ወይም በ11 ሰዓት የመጡት የወይኑ አትክልት ሠራተኞች ሆነዋል።

በመጨረሻ፣ ኢየሱስ ሲሞት ምሳሌያዊው የሥራ ቀን አበቃና ለሠራተኞቹ የሚከፈልበት ጊዜ ደረሰ። በታሪኩ ላይ በተገለጸው መሠረት ያልተለመደ የአሠራር ደንብ በመከተል ለኋለኞቹ ሠራተኞች በቅድሚያ ተከፈላቸው:- “በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ጌታ አዛዡን:- ሠራተኞችን ጥራና ከኋለኞች ጀምረህ እስከ ፊተኞች ድረስ ደመወዝ ስጣቸው አለው። በአሥራ አንደኛው ሰዓትም የገቡ መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። ፊተኞችም በመጡ ጊዜ አብዝተው የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። ተቀብለውም:- እነዚህ ኋለኞች አንድ ሰዓት ሠሩ፣ የቀኑንም ድካምና ትኲሳት ከተሸከምን ከእኛ ጋር አስተካከልሃቸው ብለው በባለቤቱ ላይ አንጐራጐሩ። እርሱ ግን መልሶ ከእነርሱ ለአንዱ እንዲህ አለው:- ወዳጄ ሆይ፣ አልበደልሁህም በአንድ ዲናር አልተስማማኸኝምን? ድርሻህን ውሰድና ሂድ፤ እኔ ለዚህ ለኋለኛው እንደ አንተ ልሰጠው እወዳለሁ፤ በገንዘቤ የወደድሁትን አደርግ ዘንድ መብት የለኝምን? ወይስ እኔ መልካም ስለ ሆንሁ ዓይንህ ምቀኛ ናትን?” ኢየሱስ ሲደመድም ቀደም ሲል የተናገረውን ነጥብ በድጋሚ በመጥቀስ “እንዲሁ ኋለኞች ፊተኞች፣ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ” አለ።

ዲናሩን የተቀበሉት ኢየሱስ በሞተበት ጊዜ ሳይሆን “አዛዡ” ማለትም ክርስቶስ በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በጰንጠቆስጤ ዕለት በደቀ መዛሙርቱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ባፈሰሰ ጊዜ ነው። እነዚህ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደ ‘ኋለኞቹ’ ወይም በ11 ሰዓት መጥተው እንደሠሩት ሠራተኞች ናቸው። ዲናሩ የሚያመለክተው ራሱን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን አይደለም። ዲናሩ ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ምድር ላይ የሚጠቀሙበትን ነገር የሚያመለክት ነው። ሕልውናቸው ማለትም የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝላቸው ነገር ነው። ስለ አምላክ መንግሥት ለመስበክ የተቀቡ መንፈሳዊ እስራኤላውያን የመሆን መብት ነው።

ብዙም ሳይቆይ መጀመሪያ የተቀጠሩት ሰዎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደተከፈላቸው ተገነዘቡ። ምሳሌያዊውን ዲናር ሲጠቀሙበትም ተመለከቱ። ሆኖም ከመንፈስ ቅዱስና ከእሱ ጋር ከተያያዙት የመንግሥቱ መብቶች የበለጠ ነገር ፈለጉ። ‘የኋለኞቹን’ የወይኑ አትክልት ሠራተኞች ማለትም የክርስቶስን ደቀ መዛሙርት በማሳደድ እንዳጉረመረሙና እንደተቃወሙ አሳይተዋል።

የኢየሱስ ምሳሌ ፍጻሜውን ያገኘው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብቻ ነውን? አይደለም፤ በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በያዟቸው ቦታዎችና ኃላፊነቶች የተነሣ በምሳሌያዊው የአምላክ የወይን አትክልት ቦታ ለመሥራት ‘የፊተኞቹ’ ተቀጣሪዎች ሆነው ነበር። የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር አባላት የሆኑትን ሰባኪዎች በአምላክ አገልግሎት ውስጥ ምንም ዓይነት ዋጋማ ሥራ የማያከናውኑ “ኋለኞች” አድርገው ተመለከቷቸው። ሆኖም ዲናሩን ማለትም የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ቅቡዓን አምባሳደሮች ሆነው የማገልገል ልዩ መብት ያገኙት ቀሳውስቱ የናቋቸው እነዚሁ ሰዎች ናቸው። ማቴዎስ 19:​30 እስከ 20:​16

▪ የወይኑ አትክልት የሚያመለክተው ምንድን ነው? የወይኑ አትክልት ባለቤት እንዲሁም ለ12 ሰዓትና ለ1 ሰዓት የሠሩት ሠራተኞችስ እነማንን ያመለክታሉ?

▪ ምሳሌያዊው የሥራ ቀን ያበቃው መቼ ነው? ክፍያው የተካሄደውስ መቼ ነው?

▪ የዲናሩ ክፍያ ምን ያመለክታል?