በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የውርስ ጥያቄ

የውርስ ጥያቄ

ምዕራፍ 77

የውርስ ጥያቄ

ሕዝቡ ኢየሱስ በፈሪሳዊው ቤት ምሳ እንደተጋበዘ አውቀው እንደነበረ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ስለዚህ ውጪ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ተሰብስበው ኢየሱስ የሚወጣበትን ጊዜ እየጠበቁ ነበር። ኢየሱስን ከሚቃወሙትና አንድ ያልሆነ ነገር እንዲናገር በማድረግ እሱን ለመያዝ ጥረት ከሚያደርጉት ፈሪሳውያን በተለየ ሁኔታ ሕዝቡ በጉጉትና በአድናቆት ያዳምጡታል።

ኢየሱስ በመጀመሪያ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዞረና “ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ፣ እርሱም ግብዝነት ነው” አላቸው። ምሳ ይበሉ በነበረበት ወቅት እንደታየው የፈሪሳውያን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በጠቅላላው በግብዝነት የተሞላ ነበር። የፈሪሳውያን ክፋት በአስመሳይ ሃይማኖተኛነታቸው ቢሸፈንም እንኳ በመጨረሻ መጋለጡ አይቀርም። ኢየሱስ “የማይገለጥ የተከደነ፣ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለም” ሲል ተናገረ።

ከዚያም ኢየሱስ አሥራ ሁለቱን በገሊላ የስብከት ዙር እንዲያደርጉ በላካቸው ጊዜ ሰጥቷቸው የነበረውን ማበረታቻ ደገመው። “ሥጋን የሚገድሉትን በኋላም አንድ ስንኳ የሚበልጥ ሊያደርጉ የማይችሉትን አትፍሩ” አለ። አምላክ አንዲት ድንቢጥ እንኳ የማይረሳ በመሆኑ እነርሱንም የማይረሳቸው መሆኑን ኢየሱስ ለተከታዮቹ አረጋገጠላቸው። “ወደ ምኩራቦችና ወደ መኳንንቶችም ወደ ገዢዎችም ሲጎትቱአችሁ፣ . . . መንፈስ ቅዱስ በዚያች ሰዓት ልትናገሩት የሚገባችሁን ያስተምራችኋል” አላቸው።

ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው ጮክ ብሎ ተናገረ። “መምህር ሆይ፣ ርስቱን ከእኔ ጋር እንዲካፈል ለወንድሜ ንገረው” በማለት አቤቱታ አቀረበ። የሙሴ ሕግ ከውርሱ መካከል ሁለቱን እጅ የበኩር ልጁ መውሰድ እንዳለበት በግልጽ የሚናገር በመሆኑ ምንም የሚያከራክር ነገር መኖር አልነበረበትም። ሆኖም ሰውየው ከሚያገኘው ሕጋዊ ውርስ የበለጠ ማግኘት ፈልጎ የነበረ ይመስላል።

ኢየሱስ በዚህ ጉዳይ ውስጥ እጁን ለማስገባት አለመፈለጉ ተገቢ ነበር። “አንተ ሰው፣ ፈራጅና አካፋይ በላያችሁ እንድሆን ማን ሾመኝ?” ሲል ጠየቀው። ከዚያም ለሕዝቡ የሚከተለውን እጅግ አስፈላጊ የሆነ ምክር ሰጣቸው:- “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፣ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ።” አዎን፣ አንድ ሰው ምንም ያህል ቁሳዊ ሀብት ቢያካብት ሁሉንም ትቶ መሞቱ አይቀርም። ይህን ሐቅ ጎላ አድርጎ ለማሳየትና በአምላክ ዘንድ ጥሩ ስም ሳያተርፉ መቅረት ምን ያህል ሞኝነት እንደሆነ ለማሳየት ኢየሱስ አንድ ምሳሌ ተጠቀመ። እንዲህ ሲል ገለጸ:-

“አንድ ባለ ጠጋ ሰው እርሻ እጅግ ፍሬያም ሆነችለት። እርሱም:- ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ። እንዲህ አደርጋለሁ፤ ጐተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ፣ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ፤ ነፍሴንም:- አንቺ ነፍሴ፣ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፣ ብዪ፣ ጠጪ፣ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ። እግዚአብሔር ግን:- አንተ ሰነፍ፣ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል? አለው።”

ኢየሱስ ሲደመድም እንዲህ አለ:- “ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፣ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው።” ደቀ መዛሙርቱ ሀብትን በማከማቸት ወጥመድ ተታልለው ሊያዙ ባይችሉም እንኳ ለዕለታዊ ኑሮ ሲጨነቁ ሐሳባቸው በቀላሉ ተከፋፍሎ ይሖዋን በሙሉ ነፍሳቸው እንዳያገለግሉት ሊያደርጋቸው ይችላል። ስለዚህ ኢየሱስ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በፊት በተራራ ስብከቱ ላይ የሰጠውን ጥሩ ምክር ደገመው። ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዞረና እንዲህ አለ:-

“ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ። . . . ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም፣ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፣ እግዚአብሔርም ይመግባቸዋል፤ . . . አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አልለበሰም። . . .

“እናንተም የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፣ አታወላውሉም፤ ይህንስ ሁሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፤ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል። ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።”

የኢየሱስን ቃላት በተለይ የኢኮኖሚ ችግር ባለባቸው ጊዜያት በጥልቀት ልናስብባቸው ይገባል። ስለሚያስፈልጉት ቁሳዊ ነገሮች ከልክ በላይ የሚጨነቅና መንፈሳዊ ነገሮችን ችላ ማለት የጀመረ ሰው አምላክ ለአገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በማቅረብ ረገድ ባለው ችሎታ ላይ እምነት እንደጎደለው ያሳያል። ሉቃስ 12:​1-31፤ ዘዳግም 21:​17

▪ ሰውየው ስለ ውርስ ጉዳይ ጥያቄ ያቀረበው ለምን ሊሆን ይችላል? ኢየሱስስ ምን ምክር ሰጠ?

▪ ኢየሱስ ምን ምሳሌ ተጠቀመ? ለማስተላለፍ የፈለገው ፍሬ ነገርስ ምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ የደገመው የትኛውን ምክር ነው? ይህስ ተገቢ የነበረው ለምንድን ነው?