በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የደስታ ምንጭ

የደስታ ምንጭ

ምዕራፍ 75

የደስታ ምንጭ

ኢየሱስ በገሊላ ያገለግል በነበረበት ጊዜ ተአምራት ፈጽሟል፤ አሁን ደግሞ እነዚህን ተአምራት በይሁዳ ውስጥ ፈጸመ። ለምሳሌ ያህል አንድን ሰው መናገር እንዳይችል አግዶት የነበረን ጋኔን አውጥቷል። ሕዝቡ በጣም ተደነቁ፤ ሆኖም አንዳንድ ተቺዎች በገሊላ ተነሥቶ የነበረው ዓይነት ተቃውሞ አስነሡ። “በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል” አሉ። ሌሎቹ ደግሞ ኢየሱስ ማንነቱን የሚመሠክር ከዚህ የበለጠ ማስረጃ እንዲሰጣቸው ፈለጉ። ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው በመጠየቅ ሊፈትኑት ሞከሩ።

ኢየሱስ ምን እንዳሰቡ ስላወቀ በገሊላ ለነበሩት ተቺዎች የሰጠውን መልስ በይሁዳ ለነበሩት ተቺዎችም ደገመላቸው። እርስ በርሱ የተከፋፈለ መንግሥት ሁሉ እንደሚወድቅ ተናገረ። “ሰይጣን ደግሞ እርስ በርሱ ከተለያየ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች?” ሲል ጠየቃቸው። ኢየሱስ ተቺዎቹን “እኔ ግን በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፣ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት [“ሳትዘጋጁ፣” NW] ወደ እናንተ ደርሳለች” በማለት ያሉበትን አደገኛ ሁኔታ አመልክቷቸዋል።

ኢየሱስ ተአምራት ሲፈጽም ያዩት ሰዎች ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ሙሴ ተአምር ሲፈጽም ያዩት ሰዎች ያሳዩትን ዓይነት ምላሽ መስጠት ነበረባቸው። እነዚያ ሰዎች “ይህስ የእግዚአብሔር ጣት ነው” በማለት በመደነቅ ተናግረው ነበር። አሥርቱን ትእዛዛት በድንጋይ ጽላቶች ላይ የጻፈውም የ“እግዚአብሔር ጣት” ነው። ኢየሱስ አጋንንትን እንዲያስወጣና ሕሙማንን እንዲፈውስ ያስቻለውም “የእግዚአብሔር ጣት” ማለትም ቅዱስ መንፈሱ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይሉ ነው። ስለዚህ የተሾመው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ማለትም ኢየሱስ በመካከላቸው ይገኝ ስለነበረ በእርግጥም የአምላክ መንግሥት ሳይዘጋጁ ደርሶባቸው ነበር።

ከዚያም ኢየሱስ ትልቁን ቤቱን በደንብ ታጥቆ የሚጠብቅን ሰው አንድ ኃይለኛ ሰው መጥቶ እንደሚያሸንፈው ሁሉ እሱም አጋንንትን ማስወጣት መቻሉ በሰይጣን ላይ ያለውን ኃይል የሚያሳይ ማስረጃ መሆኑን ገልጿል። በተጨማሪም አንድን ርኩስ መንፈስ አስመልክቶ በገሊላ የተናገረውን ምሳሌ ደገመው። ክፉው መንፈስ ከሰውየው ወጥቷል፤ ሆኖም ሰውየው ባዶውን ቦታ በመልካም ነገሮች ካልሞላው ክፉው መንፈስ ከሌሎች ሰባት መናፍስት ጋር ሆኖ ይመለስበትና የሰውየው ሁኔታ ከመጀመሪያው ይበልጥ የከፋ ይሆናል።

በሕዝቡ መካከል የነበረች ሴት እነዚህን ትምህርቶች ስትሰማ በአድናቆት ስሜት ተገፋፍታ “የተሸከመችህ ማኅፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው” በማለት ጮክ ብላ ተናገረች። አይሁዳውያን ሴቶች በሙሉ የነቢይ በተለይ ደግሞ የመሲሑ እናት የመሆን ፍላጎት ስለነበራቸው ይህች ሴት እንዲህ ብላ መናገሯ አያስደንቅም። ማርያም የኢየሱስ እናት በመሆኗ ይበልጥ ደስተኛ ልትሆን እንደምትችል አስባ ይሆናል።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ ወዲያውኑ ሴትዮዋን በማረም እውነተኛውን የደስታ ምንጭ ገልጾላታል። “ብፁዓንስ [“ደስተኞችስ፣” NW] የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው” ሲል መለሰላት። ኢየሱስ እናቱ ማለትም ማርያም ልዩ ክብር ሊሰጣት እንደሚገባ ፈጽሞ አላመለከተም። ከዚህ ይልቅ እውነተኛ ደስታ የሚገኘው በሥጋዊ ዝምድና ወይም በማንኛውም የሥራ ውጤት ሳይሆን ታማኝ የአምላክ አገልጋይ በመሆን እንደሆነ ገልጿል።

ኢየሱስ በገሊላ እንዳደረገው ሁሉ በይሁዳ ያሉ ሰዎችም ከሰማይ ምልክት በመጠየቃቸው ወቅሷቸዋል። ከዮናስ ምልክት በስተቀር ምንም ዓይነት ሌላ ምልክት እንደማይሰጣቸው ነገራቸው። ዮናስ ለሦስት ቀናት በዓሣ ሆድ ውስጥ በመቆየቱና የነነዌን ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ ባነሳሳቸው ድፍረት የተሞላበት ምሥክርነቱ ምልክት ሆኗል። “እነሆም፣” አለ ኢየሱስ፤ “ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።” በተመሳሳይም የሳባ ንግሥት በሰሎሞን ጥበብ በጣም ተደንቃ ነበር። ኢየሱስ “እነሆም፣ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ” በማለት ጨምሮ ተናግሯል።

ኢየሱስ አንድ ሰው መብራት ሲያበራ ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል እንጂ ከእንቅብ በታች ወይም ሰዋራ ቦታ እንደማያስቀምጠው ገለጸ። ምናልባትም በአድማጮቹ መካከል የሚገኙትን እነዚህን ልበ ደንዳና ሰዎች ማስተማርና በፊታቸው ተአምራት መፈጸም የአንድን መብራት ብርሃን ከመደበቅ ጋር የሚመሳሰል መሆኑን መግለጹ ይሆናል። የእነዚህ ተመልካቾች ዓይን ቀና ወይም የተስተካከለ አልነበረም፤ ስለዚህ ተአምራቱን የፈጸመበት ዓላማ ግቡን አልመታም።

ኢየሱስ በዚያ ወቅት አንድ ጋኔን አስወጥቶ ዲዳ ሆኖ የነበረውን ሰው እንዲናገር አስችሎታል። ይህ ተአምር ቀና ወይም የተስተካከለ ዓይን ያላቸው ሰዎች ይህን ታላቅ ሥራ እንዲያደንቁና ምሥራቹን እንዲያውጁ ሊያነሳሳቸው ይገባል! ሆኖም እነዚህ ተቺዎች ይህን አላደረጉም። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ደመደመ:- “እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ እንዳይሆን ተመልከት። እንግዲህ ሰውነትህ ሁሉ የጨለማ ቍራጭ የሌለበት ብሩህ ቢሆን፣ መብራት በደመቀ ብርሃን እንደሚያበራልህ በጭራሽ ብሩህ ይሆናል።” ሉቃስ 11:​14-36፤ ዘጸአት 8:​18, 19፤ 31:​18፤ ማቴዎስ 12:​22, 28

▪ ኢየሱስ ሰውየውን በመፈወሱ ሰዎቹ ያሳዩት ምላሽ ምን ነበር?

▪ “የእግዚአብሔር ጣት” ምንድን ነው? ኢየሱስን ሲያዳምጡ የነበሩት ሰዎች የአምላክ መንግሥት ሳይዘጋጁ የደረሰባቸውስ እንዴት ነው?

▪ የእውነተኛ ደስታ ምንጭ ምንድን ነው?

▪ አንድ ሰው ቀና ዓይን ሊኖረው የሚችለው እንዴት ነው?