በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጠፋውን ፈልጎ ማግኘት

የጠፋውን ፈልጎ ማግኘት

ምዕራፍ 85

የጠፋውን ፈልጎ ማግኘት

ኢየሱስ አምላክን በትህትና የሚያገለግሉ ሰዎችን ፈልጎ የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ስለዚህ በኃጢአተኝነታቸው የሚታወቁ ሰዎችን ጨምሮ እያንዳንዱን ሰው እየፈለገ ስለ መንግሥቱ ይናገር ነበር። አሁን እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ኢየሱስን ለመስማት ወደ እሱ ቀረቡ።

ፈሪሳውያንና ጻፎች ይህን ተመለከቱና ኢየሱስ እነርሱ ከንቱዎች እንደሆኑ አድርገው ከሚቆጥሯቸው ሰዎች ጋር በመቀራረቡ ነቀፉት። “ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል ከእነርሱም ጋር ይበላል” ብለው አጉረመረሙ። ይህ ከእነርሱ ክብር ምንኛ ዝቅ ያለ ነበር! ፈሪሳውያንና ጻፎች ተራውን ሕዝብ ከእግራቸው ሥር እንዳለ ቆሻሻ አድርገው ይመለከቱት ነበር። እንዲያውም ለእነዚህ ሰዎች ያላቸውን ንቀት ለመግለጽ “የምድር [የመሬት] ሰዎች” የሚል ትርጉም ያለውን አምሃሬትስ የሚለውን የዕብራይስጥ አባባል ይጠቀሙ ነበር።

በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ እያንዳንዱን ሰው በአክብሮት፣ በደግነትና በርኅራኄ መንፈስ ይመለከት ነበር። በዚህም ምክንያት በኃጢአት ድርጊታቸው በስፋት የሚታወቁትን ሰዎች ጨምሮ ከነዚህ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ኢየሱስን ለመስማት ጉጉት አድሮባቸዋል። ይሁን እንጂ ፈሪሳውያን ከንቱ እንደሆኑ አድርገው የሚቆጥሯቸውን ሰዎች ኢየሱስ ለመርዳት ጥረት በማድረጉ የሰነዘሩትን ነቀፋ በተመለከተ ምን ማለት ይቻላል?

ኢየሱስ አንድ ምሳሌ በመጠቀም ለሰነዘሩት ተቃውሞ መልስ ሰጥቷል። ፈሪሳውያን ራሳቸው ያላቸውን አመለካከት በመመርኮዝ እነርሱ ጻድቅ እንደሆኑና በአምላክ በረት ውስጥ እንዳሉ፣ አምሃሬትስ እያሉ የሚጠሯቸው የተናቁ ሰዎች ግን እንደ ባዘኑና በሚጠፉበት ሁኔታ ላይ እንዳሉ አድርጎ ተናግሯል። እንዲህ ሲል ጠየቃቸው:-

“መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፣ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፤ ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ:- የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል።”

ከዚያም ኢየሱስ ታሪኩ ያዘለውን ፍሬ ነገር እንዲህ ሲል ገለጸ:- “እላችኋለሁ፣ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።”

ፈሪሳውያን ራሳቸውን ጻድቃን አድርገው ይቆጥሩ ነበር፤ ስለዚህ ንስሐ መግባት እንደማያስፈልጋቸው ሆኖ ይሰማቸው ነበር። ከሁለት ዓመት በፊት ከፈሪሳውያን መካከል አንዳንዶቹ ኢየሱስን ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር በመብላቱ በነቀፉት ጊዜ “ኃጢአተኞችን . . . እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም” ብሏቸዋል። ንስሐ መግባት እንዳለባቸው ማስተዋል ያልቻሉት ራሳቸውን የሚያመጻድቁት ፈሪሳውያን በሰማይ ምንም የሚያስገኙት ደስታ የለም። ከልባቸው ንስሐ የሚገቡት ኃጢአተኞች ግን በሰማይ ደስታ ያስገኛሉ።

ኢየሱስ የጠፉ ኃጢአተኞች መመለሳቸው ታላቅ ደስታ የሚያመጣ መሆኑን ይበልጥ ጠበቅ አድርጎ ለመግለጽ ሌላ ምሳሌ ተናገረ። እንዲህ አለ:- “ወይም አሥር ድሪም ያላት አንድ ድሪም ቢጠፋባት፣ መብራት አብርታ ቤትዋንም ጠርጋ እስክታገኘው ድረስ አጥብቃ የማትፈልግ ሴት ማን ናት? ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆችዋንና ጐረቤቶችዋን በአንድነት ጠርታ:- የጠፋውን ድሪሜን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ትላቸዋለች።”

ከዚያም ኢየሱስ ይሄኛውንም ምሳሌ ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ተጠቀመበት። “እላችኋለሁ፣ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል” ሲል ተናገረ።

የአምላክ መላእክት ለጠፉት ኃጢአተኞች መመለስ ያላቸው ይህ ፍቅራዊ አሳቢነት ምንኛ የሚያስደንቅ ነው! በተለይ እነዚህ በአንድ ወቅት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበሩ የተናቁ አምሃሬትስ በመጨረሻ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት አባላት መሆን ወደሚችሉበት ደረጃ መድረሳቸው ሁኔታውን አስደናቂ ያደርገዋል። በመሆኑም በሰማይ ከራሳቸው ከመላእክቱም የላቀ ሥልጣን ያገኛሉ! ይሁን እንጂ መላእክቱ የቅናት ስሜት አያድርባቸውም፤ እንደተናቁ ሆኖም አይሰማቸውም። ከዚህ ይልቅ እነዚህ ኃጢአተኛ ሰዎች ርኅሩኅና መሐሪ የሆኑ ሰማያዊ ነገሥታትና ካህናት ሆነው ለማገልገል ብቁ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በሕይወታቸው ውስጥ እንደገጠሟቸውና እነዚህን ሁኔታዎች በድል እንደተወጡ በትህትና አምነው ይቀበላሉ። ሉቃስ 15:​1-10፤ ማቴዎስ 9:​13፤ 1 ቆሮንቶስ 6:​2, 3፤ ራእይ 20:​6

▪ ኢየሱስ በኃጢአተኝነታቸው ከታወቁ ሰዎች ጋር የተቀራረበው ለምንድን ነው? ይህስ ከፈሪሳውያን ምን ነቀፋ አስከትሎበታል?

▪ ፈሪሳውያን ተራውን ሕዝብ የሚመለከቱት እንዴት ነበር?

▪ ኢየሱስ የትኞቹን ምሳሌዎች ተናግሯል? ከእነዚህ ምሳሌዎችስ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

▪ መላእክት መደሰታቸው አስደናቂ የሆነው ለምንድን ነው?