በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጠፋው ልጅ ታሪክ

የጠፋው ልጅ ታሪክ

ምዕራፍ 86

የጠፋው ልጅ ታሪክ

ኢየሱስ የጠፋን በግና የጠፋን ድሪም መልሶ ስለ ማግኘት የሚገልጹ ምሳሌዎችን ለፈሪሳውያን ከነገራቸው በኋላ አሁን ደግሞ ሌላ ምሳሌ መናገር ጀመረ። ይህ ምሳሌ ስለ አንድ አፍቃሪ አባትና እያንዳንዳቸው የየራሳቸው የሆነ ከባድ ጉድለት ያላቸውን ሁለት ልጆቹን ስለያዘበት ሁኔታ የሚገልጽ ነው።

በመጀመሪያ በምሳሌው ላይ ዋነኛ ገጸ ባሕርይ ሆኖ የተገለጸው ታናሹ ልጅ ተጠቅሷል። አባቱ ያላንዳች ማመንታት የሰጠውን ውርስ ሰበሰበ። ከዚያም ቤቱን ለቆ በመሄድ ምግባረ ብልሹ የሆነ ሕይወት መኖር ጀመረ። እስቲ ኢየሱስ ታሪኩን ሲናገር ተከታተልና በታሪኩ ላይ የተገለጹት ገጸ ባሕርያት እነማንን እንደሚያመለክቱ ለማወቅ ሞክር።

“አንድ ሰው” በማለት ኢየሱስ ታሪኩን መናገር ጀመረ፤ “ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ አባቱን:- አባቴ ሆይ፣ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ አለው። [አባትየው] ገንዘቡንም አካፈላቸው።” ይህ ታናሽየው ልጅ የተቀበለውን ገንዘብ ምን ያደርግበት ይሆን?

“ከጥቂት ቀንም በኋላ” ሲል ኢየሱስ ገለጸ፤ “ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፣ ከዚያም እያባከነ ገንዘቡን በተነ።” ገንዘቡን ያባከነው ከጋለሞታዎች ጋር በመኖር ነበር። ከዚያ በኋላ፣ ኢየሱስ ቀጥሎ እንደገለጸው አስቸጋሪ ጊዜ መጣ:-

“ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፣ እርሱም ይጨነቅ ጀመር። ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፣ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው። እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፣ የሚሰጠውም አልነበረም።”

በአምላክ ሕግ መሠረት እሪያዎች ርኩስ ስለነበሩ የእሪያዎች እረኛ ለመሆን መገደድ እንዴት ያለ ውርደት ነበር! ሆኖም ልጁን እጅግ ያሠቃየው ነገር ሆዱን የሚሞረሙረው ረሃብ ነበር፤ በዚህም የተነሣ እሪያዎቹ የሚበሉትን ምግብ እስከ መመኘት ደርሶ ነበር። በደረሰበት ክፉ መከራ የተነሣ ‘ወደ ልቡ እንደተመለሰ’ ኢየሱስ ተናግሯል።

ኢየሱስ ታሪኩን መናገሩን በመቀጠል እንዲህ ሲል ገለጸ:- “[ለራሱ] እንዲህ አለ:- እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና:- አባቴ ሆይ፣ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፣ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ። ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ።”

እዚህ ላይ አንድ ልብ ልንለው የሚገባ ነገር አለ:- ልጅየው ከቤት በወጣበት ጊዜ አባትየው ክፉ ቃል ተናግሮትና በኃይል ተቆጥቶት ቢሆን ኖሮ ልጁ ማድረግ ያለበትን ነገር በተመለከተ አንድ ቁርጥ ያለ ሐሳብ ላይ ሊደርስ አይችልም ነበር። ወደ አገሩ ተመልሶ የአባቱን ፊት ሳያይ በሌላ ቦታ ሥራ ፈልጎ ለማግኘት ሊወስን ይችል ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ሐሳብ ወደ አእምሮው አልመጣም። መመለስ የፈለገው ወደ ቤቱ ነበር!

ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው አባት አፍቃሪና መሐሪ የሆነውን ሰማያዊ አባታችንን ይሖዋ አምላክን እንደሚያመለክት ግልጽ ነው። በተጨማሪም የጠፋው ወይም አባካኙ ልጅ በኃጢአተኝነታቸው የሚታወቁትን ሰዎች እንደሚያመለክት ተገንዝበህ ይሆናል። ኢየሱስ ታሪኩን እየነገራቸው ያሉት ፈሪሳውያን ቀደም ሲል ኢየሱስ ከእነዚህ ኃጢአተኞች ጋር በመብላቱ ነቅፈውት ነበር። ታዲያ ትልቁ ልጅ የሚያመለክተው ማንን ነው?

የጠፋው ልጅ ሲገኝ

በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው የጠፋው ወይም አባካኙ ልጅ ወደ አባቱ ቤት ሲመለስ ምን ዓይነት አቀባበል ይደረግለት ይሆን? የተደረገለትን አቀባበል በተመለከተ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:-

“እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፣ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው።” ሰማያዊ አባታችንን ይሖዋን በሚገባ የሚወክል እንዴት ያለ መሐሪና ደግ አባት ነው!

አባትየው ስለ ልጁ ብልሹ አኗኗር ሳይሰማ አይቀርም። ሆኖም ልጁ ዝርዝር ማብራሪያ እስኪሰጠው ሳይጠብቅ እጁን ዘርግቶ ተቀብሎታል። ኢየሱስም ራሱ ቀዳሚ ሆኖ በምሳሌው ላይ በአባካኙ ልጅ የተመሰሉትን ኃጢአተኞችና ቀረጥ ሰብሳቢዎች በመቅረብ እንዲህ ዓይነት በደስታ የመቀበል መንፈስ እንዳለው አሳይቷል።

እርግጥ ነው፣ በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው አስተዋይ አባት ልጁ ሲመለስ በፊቱ ላይ ይነበብ የነበረውን ሐዘንና የኀፍረት ስሜት በመመልከት ልጁ የተጸጸተ መሆኑን በተወሰነ ደረጃ መረዳት እንደቻለ ጥርጥር የለውም። ሆኖም አባትየው ቀድሞ ፍቅራዊ እርምጃ መውሰዱ ልጁ ኃጢአቱን በቀላሉ መናዘዝ እንዲችል ረድቶታል፤ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “ልጁም:- አባቴ ሆይ፣ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፣ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም። ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ አለው።”

ሆኖም ልጁ ተናግሮ ሳይጨርስ አባትየው ወዲያውኑ እርምጃ በመውሰድ ባሪያዎቹን እንዲህ ሲል አዘዛቸው:- “ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፣ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ፤ የሰባውን ፍሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፣ እንብላም ደስም ይበለን፤ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም።” ከዚያም “ደስም ይላቸው ጀመር።”

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአባትየው “ታላቁ ልጁ በእርሻ ነበረ።” የቀረውን ታሪክ ተከታተልና ይሄኛው ልጅ ማንን እንደሚያመለክት ለማወቅ ሞክር። ኢየሱስ ስለ ታላቁ ልጅ ሲናገር እንዲህ አለ:- “መጥቶም ወደ ቤት በቀረበ ጊዜ የመሰንቆና የዘፈን ድምፅ ሰማ፤ ከብላቴናዎችም አንዱን ጠርቶ:- ይህ ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀ። እርሱም:- ወንድምህ መጥቶአልና በደኅና ስላገኘው አባትህ የሰባውን ፍሪዳ አረደለት አለው። ተቈጣም ሊገባም አልወደደም፤ አባቱም ወጥቶ ለመነው። እርሱ ግን መልሶ አባቱን:- እነሆ፣ ይህን ያህል ዓመት እንደ ባሪያ ተገዝቼልሃለሁ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ ለእኔም ከወዳጆቼ ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ ጠቦት ስንኳ አልሰጠኸኝም፤ ነገር ግን ገንዘብህን ከጋለሞቶች ጋር በልቶ ይህ ልጅህ በመጣ ጊዜ፣ የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት አለው።”

ልክ እንደ ትልቁ ልጅ ለኃጢአተኞች የተደረገውን ምሕረትና ልዩ ትኩረት የነቀፉት እነማን ናቸው? ጻፎችና ፈሪሳውያን አይደሉምን? ኢየሱስ ይህን ምሳሌ እንዲናገር ያነሳሳው ኃጢአተኞችን ወዳጃዊ በሆነ መንፈስ በመቀበሉ የሰነዘሩበት ትችት በመሆኑ በትልቁ ልጅ የተመሰሉት እነርሱ መሆን አለባቸው።

ኢየሱስ ታሪኩን የደመደመው አባትየው ለትልቁ ልጁ ያቀረበውን ልመና በመግለጽ ነበር:- “ልጄ ሆይ፣ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፣ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል።”

ኢየሱስ ታላቁ ልጅ በመጨረሻ ምን እንዳደረገ አልገለጸም። እርግጥ ኢየሱስ ከሞተና ከተነሣ በኋላ “ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ” ሆነዋል፤ ከእነዚህም መካከል ኢየሱስ በዚህ ወቅት ሲያነጋግራቸው ከነበሩት ‘የትልቁ ልጅ’ ክፍል አባላት አንዳንዶቹ ሳይገኙበት አይቀሩም።

ይሁን እንጂ በዘመናችን ሁለቱ ልጆች እነማንን ያመለክታሉ? ሁለቱ ልጆች የሚያመለክቱት ከይሖዋ ጋር ዝምድና ለመመሥረት ስለ ይሖዋ ዓላማዎች በቂ እውቀት ያገኙትን ሰዎች መሆን አለበት። ትልቁ ልጅ ‘የታናሹን መንጋ’ ወይም ‘በሰማያት የተጻፉትን የበኩራት ማኅበር’ አንዳንድ አባላት ያመለክታል። እነዚህ የትልቁን ልጅ ዓይነት አመለካከት ያዙ። የምድራዊው ክፍል አባላት የሆኑትን “ሌሎች በጎች” መቀበል አልፈለጉም፤ በእነሱ ላይ ያረፈውን ልዩ ትኩረት እንደ ሰረቁባቸው ሆኖ ይሰማቸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ አባካኙ ልጅ ዓለም የሚሰጠውን ደስታ ለማግኘት የሄዱ የአምላክ ሕዝቦችን ያመለክታል። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ንስሐ ገብተው በመመለስ እንደገና ትጉ የአምላክ አገልጋዮች ይሆናሉ። በእርግጥም ይቅርታ መጠየቅ እንዳለባቸው ተገንዝበው ወደ እሱ ለሚመለሱት ሰዎች አባታቸው ምንኛ አፍቃሪና መሐሪ ነው! ሉቃስ 15:​11-32፤ ዘሌዋውያን 11:​7, 8፤ ሥራ 6:​7፤ ሉቃስ 12:​32፤ ዕብራውያን 12:​23፤ ዮሐንስ 10:​16

▪ ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ወይም ታሪክ የተናገረው ለእነማን ነው? ለምንስ?

▪ በታሪኩ ውስጥ ዋነኛ ገጸ ባሕርይ ሆኖ የተጠቀሰው ማን ነው? የደረሰበት ሁኔታስ ምን ነበር?

▪ በኢየሱስ ዘመን አባትየውና ታናሹ ልጅ የሚያመለክቱት እነማንን ነው?

▪ ኢየሱስ በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሰውን ርኅሩኅ አባት አርአያ የተከተለው እንዴት ነው?

▪ ትልቁ ልጅ ለወንድሙ የተደረገውን አቀባበል የተመለከተው እንዴት ነው? ፈሪሳውያን የትልቁን ልጅ ዓይነት ባሕርይ ያሳዩትስ እንዴት ነው?

▪ የኢየሱስ ምሳሌ በዘመናችን ምን ተፈጻሚነት አለው?