በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ”

“ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ”

ምዕራፍ 126

“ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ”

ኢየሱስ እንጨቱ ላይ ተሰቅሎ ብዙም ሳይቆይ እኩለ ቀን ላይ ለሦስት ሰዓት የቆየ እንግዳ የሆነ ጨለማ ተከሰተ። ይህ የሆነው በፀሐይ ግርዶሽ ሳቢያ አይደለም። ምክንያቱም የፀሐይ ግርዶሽ የሚፈጠረው አዲስ ጨረቃ በምትኖርበት ጊዜ ብቻ ነው፤ በማለፍ በዓል ጊዜ ደግሞ ጨረቃ ሙሉ ነች። ከዚህም በላይ የፀሐይ ግርዶሽ የሚቆየው ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ነው። ስለዚህ ጨለማው በመለኮታዊ ኃይል የተፈጸመ ነበር! በኢየሱስ ላይ ሲያላግጡ የነበሩት ሰዎች ጋብ እንዲሉና አልፎ ተርፎም ፌዛቸውን እንዲያቆሙ ሳያደርጋቸው አልቀረም።

ይህ ያልተለመደ ሁኔታ የተከሰተው አንደኛው ክፉ አድራጊ ጓደኛውን ከመገሠጹና ኢየሱስን እንዲያስታውሰው ከመጠየቁ በፊት ከሆነ ይህ ሁኔታ ንስሐ እንዲገባ አስተዋጽኦ አድርጎለት ሊሆን ይችላል። አራት ሴቶች ማለትም የኢየሱስ እናትና እህቷ ሰሎሜ እንዲሁም መግደላዊት ማርያምና የታናሹ ያዕቆብ እናት የሆነችው ማርያም ወደ መከራው እንጨት የቀረቡት በጨለማው ወቅት ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ የሚወደው ሐዋርያ ዮሐንስ ከእነርሱ ጋር ነበር።

የኢየሱስ እናት አጥብታና ተንከባክባ ያሳደገችው ልጅ እዚያ ላይ ተሰቅሎ ሲሠቃይ ስታይ ልቧ ምንኛ ‘በሐዘን ጦር ተወግቶ’ ይሆን! ሆኖም ኢየሱስ ስለ ራሱ ሥቃይ ብቻ ሳይሆን ስለ እናቱም ደህንነት አስቧል። እንደምንም ተጣጥሮ በጭንቅላቱ ወደ ዮሐንስ በማመልከት እናቱን “አንቺ ሴት፣ እነሆ ልጅሽ” አላት። ከዚያም በጭንቅላቱ ወደ ማርያም በማመልከት ዮሐንስን “እናትህ እነኋት” አለው።

ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው በዚህ ወቅት መበለት የሆነችውን እናቱን እንዲንከባከባት ኢየሱስ ይበልጥ ለሚወደው ሐዋርያ በአደራ ሰጣት። ይህን ያደረገው የማርያም ሌሎች ልጆች ገና በእሱ ያላመኑ በመሆኑ ነው። በዚህ መንገድ ለእናቱ የሚያስፈልጉትን ሥጋዊ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ነገሮችንም በማዘጋጀት ጥሩ ምሳሌ ትቷል።

ከቀትር በኋላ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ላይ ኢየሱስ “ተጠማሁ” አለ። ኢየሱስ የአቋም ጽናቱ እስከ መጨረሻ ድረስ እንዲፈተን አባቱ ጥበቃውን ከእሱ ላይ እንዳነሳ ሆኖ የተሰማው ይመስላል። ስለዚህ “አምላኬ፣ አምላኬ፣ ለምን ተውኸኝ?” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ። በአቅራቢያው የነበሩ አንዳንዶች ይህን ሲሰሙ “እነሆ፣ ኤልያስን ይጠራል” አሉ። ወዲያውኑ ከመካከላቸው አንዱ ሮጦ ሄደና ሆምጣጤ ውስጥ የተነከረ ሰፍነግ በሂሶፕ አገዳ ጫፍ ላይ አድርጎ አጠጣው። ሌሎቹ ግን “ተዉ፤ ኤልያስ ሊያወርደው ይመጣ እንደ ሆነ እንይ” አሉ።

ኢየሱስ ሆምጣጤውን ከሰጡት በኋላ “ተፈጸመ” ብሎ ጮኸ። አዎን፣ አባቱ ወደ ምድር ሲልከው እንዲያከናውነው የሰጠውን ሥራ ሁሉ ፈጽሟል። በመጨረሻ “አባት ሆይ፣ ነፍሴን [“መንፈሴን፣” NW] በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” አለ። በዚህ መንገድ ኢየሱስ አምላክ እንደገና መልሶ እንደሚሰጠው በመተማመን የሕይወት ኃይሉን ለአምላክ በአደራ ሰጠ። ከዚያም ራሱን አዘንብሎ ሞተ።

ኢየሱስ የመጨረሻዋን ትንፋሽ እንደተነፈሰ ኃይለኛ የምድር ነውጥ ተከሰተና ዓለቶች ተሰነጠቁ። ነውጡ በጣም ኃይለኛ ስለነበረ ከኢየሩሳሌም ውጪ ያሉት መቃብሮች ተከፈቱና አስከሬኖቹ ወደ ውጪ ወጡ። የወጡትን አስከሬኖች የተመለከቱ መንገደኞች ወደ ከተማይቱ ገቡና የሆነውን ነገር አወሩ።

በተጨማሪም ኢየሱስ ሲሞት በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ ቅድስቱን ከቅድስተ ቅዱሳኑ የሚለየው ትልቅ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ። ይህ እጅግ ያጌጠ መጋረጃ 18 ሜትር ገደማ ከፍታ ያለውና በጣም ከባድ የነበረ ይመስላል! ይህ አስደናቂ ተአምር አምላክ በልጁ ገዳዮች ላይ የተሰማውን ቁጣ ከመግለጹም በላይ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ማለትም ወደ ሰማይ የሚያስገባው መንገድ በኢየሱስ ሞት አማካኝነት እንደተከፈተ ያመለክታል።

ሰዎች የምድር ነውጡንና የተፈጸሙትን ነገሮች ሲመለከቱ ከፍተኛ ፍርሃት አደረባቸው። ግድያውን እንዲያስፈጽም ኃላፊነት የተሰጠው መቶ አለቃ አምላክን አከበረ። “ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ” አለ። በጲላጦስ ፊት በተካሄደው ችሎት ላይ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ነኝ ብሏል በሚለው ክስ ላይ ውይይት ሲደረግ መቶ አለቃው በቦታው የነበረ ይመስላል። እናም አሁን ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ፣ አዎን፣ በእርግጥም እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው መሆኑን አምኗል።

ሌሎች ሰዎችም በእነዚህ ተአምራዊ ክንውኖች በጣም ተነክተው የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘንና ኀፍረት ለመግለጽ ደረታቸውን እየደቁ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። በእነዚህ ታላላቅ ክንውኖች ስሜታቸው በጥልቅ የተነካ ብዙ የኢየሱስ ሴት ደቀ መዛሙርት በርቀት ሆነው ይህን አስገራሚ ትዕይንት እየተመለከቱ ነበር። ሐዋርያው ዮሐንስም በቦታው ነበር። ማቴዎስ 27:​45-56፤ ማርቆስ 15:​33-41፤ ሉቃስ 23:​44-49፤ 2:​34, 35፤ ዮሐንስ 19:​25-30

▪ ለሦስት ሰዓት ያህል የጨለመው በፀሐይ ግርዶሽ ምክንያት ሊሆን የማይችለው ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት በዕድሜ የገፉ ወላጆች ላሏቸው ሰዎች ምን ጥሩ ምሳሌ ትቷል?

▪ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት የተናገራቸው አራት የመጨረሻ ዐረፍተ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

▪ የምድር ነውጡ ምን ነገር አስከትሏል? የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ለሁለት መቀደዱ ምን ትርጉም አለው?

▪ ግድያውን ያስፈጸመው መቶ አለቃ ተአምራቱን ሲመለከት ምን ተሰማው?