በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይመጣል ተብሎ ተስፋ የተሰጠበት ልጅ

ይመጣል ተብሎ ተስፋ የተሰጠበት ልጅ

ምዕራፍ 6

ይመጣል ተብሎ ተስፋ የተሰጠበት ልጅ

ዮሴፍና ማርያም ወደ ናዝሬት ሳይመለሱ እዚያው ቤተ ልሔም ውስጥ ቆዩ። አምላክ ለሙሴ የሰጠው ሕግ በሚያዘው መሠረት ኢየሱስ ስምንት ቀን ሲሞላው ገረዙት። ለአንድ ሕፃን በስምንተኛው ቀን ስም ማውጣትም የተለመደ ነገር የነበረ ይመስላል። ስለዚህ መልአኩ ገብርኤል አስቀድሞ በነገራቸው መሠረት ልጃቸውን ኢየሱስ ብለው ጠሩት።

ከወር በላይ የሚሆን ጊዜ አለፈ፤ ኢየሱስም ከተወለደ 40 ቀን ሆነው። አሁን ወላጆቹ ወዴት ይወስዱታል? እነርሱ ካሉበት ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቆ ኢየሩሳሌም ውስጥ ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ ይወስዱታል። አምላክ ለሙሴ በሰጠው ሕግ መሠረት ወንድ ልጅ ከተወለደ ከ40 ቀናት በኋላ እናትየዋ በቤተ መቅደሱ የመንጻት መሥዋዕት ማቅረብ ይኖርባታል።

ማርያምም ያደረገችው ይህንኑ ነበር። ሁለት ትንንሽ ወፎች መሥዋዕት አድርጋ አቀረበች። ይህ ዮሴፍና ማርያም የነበሩበትን የኢኮኖሚ ሁኔታ የሚጠቁም ነው። የሙሴ ሕግ ከወፎች የበለጠ ዋጋ ያለው ጠቦት መሥዋዕት ሆኖ መቅረብ እንዳለበት ያመለክታል። ሆኖም እናቲቱ ይህን ለማቅረብ አቅሟ የማይፈቅድላት ከሆነ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት ርግቦች ማቅረብ ትችላለች።

በቤተ መቅደሱ ውስጥ አንድ በዕድሜ የገፋ ሰው ኢየሱስን ወስዶ አቀፈው። ይህ ሰው ስምዖን ይባላል። ይሖዋ ይመጣል ብሎ ተስፋ የሰጠበትን ክርስቶስን ወይም መሲሑን ሳያይ እንደማይሞት አምላክ ገልጦለት ነበር። ስምዖን በዚህ ዕለት ወደ ቤተ መቅደሱ ሲመጣ መንፈስ ቅዱስ ዮሴፍና ማርያም ወደያዙት ልጅ መራው።

ስምዖን ኢየሱስን ይዞ እንዲህ ሲል አምላክን አመሰገነ:- “ጌታ ሆይ፣ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።”

ዮሴፍና ማርያም ይህን ሲሰሙ ተደነቁ። ከዚያም ስምዖን ባረካቸውና ማርያምን ልጅዋ ‘በእስራኤል ውስጥ ለብዙዎች የመጥፋት ለብዙዎች ደግሞ የመዳን ምክንያት እንደሚሆንና’ እርስዋም ልክ እንደ ተሳለ ሰይፍ ሐዘን በነፍስዋ እንደሚያልፍ ነገራት።

በዚህ ወቅት ሐና የምትባል አንዲት የ84 ዓመት ነቢይት ነበረች። እንዲያውም ከቤተ መቅደስ ጠፍታ አታውቅም ነበር። በዚያው ጊዜ ወደ እነሱ ቀረብ ብላ አምላክን ማመስገን ጀመረች፤ ይሰሙ ለነበሩት ሰዎችም ስለ ኢየሱስ ተናገረች።

ዮሴፍና ማርያም በቤተ መቅደሱ በተከናወኑት በእነዚህ ነገሮች ምንኛ ተደስተው ይሆን! ይህ ሁሉ ነገር ልጁ አምላክ ይመጣል ብሎ የተስፋ ቃል የሰጠበት ሰው መሆኑን እንዳረጋገጠላቸው ምንም አያጠራጥርም። ሉቃስ 2:​21-38፤ ዘሌዋውያን 12:​1-8

▪ በነበረው ልማድ መሠረት ለአንድ እስራኤላዊ ወንድ ልጅ ስም የሚወጣው መቼ ነበር?

▪ አንዲት እስራኤላዊት እናት ልጅዋ 40 ቀን ሲሞላው ምን ማድረግ ይጠበቅባት ነበር? ማርያም ይህን ብቃት ለማሟላት ያደረገችው ነገር የነበረችበትን የኢኮኖሚ ሁኔታ የሚያሳየው እንዴት ነው?

▪ በዚህ ወቅት የኢየሱስን ማንነት የተረዱት እነማን ነበሩ? ይህንንስ ያሳዩት እንዴት ነው?