በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዮሐንስ መንገዱን አዘጋጀ

ዮሐንስ መንገዱን አዘጋጀ

ምዕራፍ 11

ዮሐንስ መንገዱን አዘጋጀ

ኢየሱስ በ12 ዓመቱ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበሩትን አስተማሪዎች አንዳንድ ጥያቄዎችን ከጠየቀ አሁን አሥራ ሰባት ዓመታት አልፈዋል። ወቅቱ 29 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የጸደይ ወራት ነው። ሁሉም ሰው በዮርዳኖስ ወንዝ አካባቢ ባለው አገር ሁሉ እየሰበከ ስላለው የኢየሱስ የአክስት ልጅ ስለ ዮሐንስ የሚያወራ ይመስላል።

በእርግጥም ዮሐንስ በቁመናውም ሆነ በንግግሩ የሰዎችን ትኩረት የሚስብ ነበር። ልብሱ ከግመል ፀጉር የተሠራ ነበር፤ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር። ምግቡ አንበጣና የበረሀ ማር ነበር። መልእክቱስ? “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” የሚል ነበር።

ይህ መልእክት የአድማጮቹን ስሜት ቀስቅሷል። ብዙዎቹ ንስሐ መግባት ማለትም አቋማቸውን መለወጥና ቀደም ሲል ሲከተሉት የነበረውን አኗኗር ልክ አላስፈላጊ እንደሆነ ነገር እርግፍ አድርገው መተው እንዳለባቸው ተገነዘቡ። ስለዚህ ከኢየሩሳሌም እንኳን ሳይቀር በዮርዳኖስ ዙሪያ ካለው አገር ሁሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ወደ ዮሐንስ ይመጡ ነበር። ዮሐንስም በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ እያጠለቀ ያጠምቃቸው ነበር። ይህን ያደርግ የነበረው ለምንድን ነው?

ዮሐንስ ሰዎችን ያጠምቅ የነበረው የአምላክን የቃል ኪዳን ሕግ በመተላለፍ ለፈጸሙት ኃጢአት ከልብ ንስሐ መግባታቸውን የሚያሳይ ምልክት ወይም ማረጋገጫ እንዲሆን ነበር። በመሆኑም አንዳንድ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደ ዮርዳኖስ መጥተው በነበረበት ጊዜ ዮሐንስ “እናንተ የእፉኝት ልጆች” በማለት አውግዟቸዋል። “ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም:- አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና:- ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል። አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል” አላቸው።

ዮሐንስ ብዙ ትኩረት እየሳበ በመሄዱ አይሁዶች ካህናትንና ሌዋውያንን ወደ እሱ ላኩ። የተላኩት ሰዎች “አንተ ማን ነህ?” ብለው ጠየቁት።

ዮሐንስ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም” ሲል ተናገረ።

“እንኪያስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን?” ብለው ጠየቁት።

“አይደለሁም” ብሎ መለሰ።

“ነቢዩ ነህን?”

“አይደለሁም።”

“እንኪያስ:- ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” ብለው አጥብቀው ጠየቁት።

“ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ:- የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ” ሲል ዮሐንስ ገለጸላቸው።

“እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፣ ስለ ምን ታጠምቃለህ?” ሲሉ ጠየቁት።

“እኔ በውኃ አጠምቃለሁ” ሲል መለሰላቸው። ‘እናንተ የማታውቁት ከእኔ በኋላ የሚመጣው በመካከላችሁ ቆሟል’ አላቸው።

ሰዎች ንጉሥ የሚሆነውን መሲሕ ለመቀበል የሚያስችል ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ እንዲኖራቸው በማድረግ ዮሐንስ መንገዱን እያዘጋጀ ነበር። ዮሐንስ ስለ መሲሑ ሲናገር “እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፣ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከበር ይህ ነው” ብሏል። እንዲያውም ዮሐንስ “ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል” ሲል ተናግሯል።

ስለዚህ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” የሚለው የዮሐንስ መልእክት ይሖዋ የሾመው ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት ሊጀምር መሆኑን የሚያመለክት ለሕዝቡ እንደ ማስታወቂያ ሆኖ የሚያገለግል ነበር። ዮሐንስ 1:​6-8, 15-28፤ ማቴዎስ 3:​1-12፤ ሉቃስ 3:​1-18፤ ሥራ 19:​4

▪ ዮሐንስ ምን ዓይነት ሰው ነበር?

▪ ዮሐንስ ሰዎችን ያጠመቀው ለምንድን ነው?

▪ ዮሐንስ መንግሥቱ ቀርቧል ሊል የቻለው ለምንድን ነው?