በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዮሐንስ እምነት ጎድሎት ነበርን?

ዮሐንስ እምነት ጎድሎት ነበርን?

ምዕራፍ 38

ዮሐንስ እምነት ጎድሎት ነበርን?

ወኅኒ ቤት ከገባ አንድ ዓመት ገደማ የሆነው አጥማቂው ዮሐንስ በናይን የምትገኘው መበለት ልጅ ከሞት እንደተነሣ ሰማ። ሆኖም ዮሐንስ ይህ ምን ትርጉም እንዳለው በቀጥታ ከኢየሱስ መስማት ፈልጎ ነበር። ስለዚህ “የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላውን እንጠብቅ?” ብለው እንዲጠይቁት ሁለት ደቀ መዛሙርቱን ላካቸው።

ዮሐንስ በተለይ ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት ኢየሱስን ባጠመቀበት ጊዜ የአምላክ መንፈስ በኢየሱስ ላይ ሲወርድ ከማየቱም በላይ አምላክ በሞገስ እንደተቀበለው ሲናገር የሰማ በመሆኑ ይህ ጥያቄ ግራ ሊያጋባ ይችላል። ይህ የዮሐንስ ጥያቄ አንዳንዶች እምነቱ ደክሞ ነበር ብለው እንዲደመድሙ ሊያደርጋቸው ይችላል። ሆኖም ዮሐንስ እምነቱ አልደከመም። ዮሐንስ መጠራጠር ጀምሮ ቢሆን ኖሮ በዚህ ወቅት ኢየሱስ ዮሐንስን በጣም አሞግሶ ባልተናገረ ነበር። ታዲያ ዮሐንስ ይህን ጥያቄ ያቀረበው ለምንድን ነው?

ዮሐንስ፣ ኢየሱስ መሲሕ ስለመሆኑ ከራሱ ማረጋገጫ ማግኘት ፈልጎ ይሆናል። ይህ በእስር ቤት እየማቀቀ ያለውን ዮሐንስን በጣም ሊያበረታው ይችላል። ይሁን እንጂ የዮሐንስ ጥያቄ ከዚህም ሌላ ያዘለው ትርጉም ያለ ይመስላል። መሲሑ እንደሚፈጽማቸው አስቀድሞ በትንቢት የተነገሩትን ነገሮች ሙሉ በሙሉ የሚፈጽም ሌላ ተተኪ ይመጣ እንደሆነና እንዳልሆነ ማወቅ ፈልጎ እንደነበረ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።

ዮሐንስ የሚያውቃቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በአምላክ የሚቀባው ሰው ንጉሥና ነፃ አውጪ እንደሚሆን ይናገራሉ። ሆኖም ኢየሱስ ከተጠመቀ ብዙ ወራት ያለፉ ቢሆንም እንኳ ዮሐንስ አሁንም እንደታሰረ ይገኛል። ስለዚህ ዮሐንስ ኢየሱስን ‘የአምላክን መንግሥት በሚታይ ሥልጣን የምታቋቁመው አንተ ነህ ወይስ ስለ መሲሑ ክብር የተነገሩትን አስደናቂ ትንቢቶች በሙሉ የሚፈጽም ሌላ ተተኪ ይመጣል?’ ብሎ መጠየቁ እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።

ኢየሱስ የዮሐንስን ደቀ መዛሙርት ‘ይመጣል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ሰው እኔ ነኝ!’ አላላቸውም። ከዚህ ይልቅ በዚያው ሰዓት ብዙ ሰዎችን ከሁሉም ዓይነት በሽታና ሕመም በመፈወስ አስደናቂ ትዕይንት አሳየ። ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው:- “ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ ዕውሮች ያያሉ፣ አንካሶችም ይሄዳሉ፣ ለምጻሞችም ይነጻሉ፣ ደንቆሮዎችም ይሰማሉ፣ ሙታንም ይነሣሉ፣ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል።”

በሌላ አነጋገር የዮሐንስ ጥያቄ ኢየሱስ እያከናወነ ካለው ነገር ሌላ ተጨማሪ ነገር ያደርጋል ብሎ እንደሚጠብቅና ምናልባትም ራሱን ዮሐንስን እንደሚያስፈታው ይጠብቅ እንደነበረ ሊያመለክት ይችላል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እየፈጸመው ካለው ተአምራት ሌላ እንዳይጠብቅ ለዮሐንስ መንገሩ ነበር።

የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ሲሄዱ ኢየሱስ ወደ ሕዝቡ ዞረና በ⁠ሚልክያስ 3:​1 ላይ ይመጣል ተብሎ አስቀድሞ የተነገረለት የይሖዋ “መልእክተኛ” እና በ⁠ሚልክያስ 4:​5, 6 ላይ ይመጣል ተብሎ አስቀድሞ የተነገረለት ነቢዩ ኤልያስ ዮሐንስ መሆኑን ነገራቸው። ዮሐንስ ከእሱ በፊት ከተነሣው ከማንኛውም ነቢይ እኩል እንደሆነ በመግለጽ እንዲህ ሲል አወድሶታል:- “እውነት እላችኋለሁ፣ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ሰዎች ለመግባት ትግል የሚያደርጉበት ግብ ሆኗል።”​—NW

ኢየሱስ እዚህ ላይ ዮሐንስ መንግሥተ ሰማያትን እንደማይወርስ አመልክቷል፤ ምክንያቱም በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚያንሰው ዮሐንስን ይበልጠዋል። ዮሐንስ ጥርጊያውን ለኢየሱስ ያዘጋጀለት ቢሆንም ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ በመንግሥቱ ከእሱ ጋር ተባባሪ ገዥዎች እንዲሆኑ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ከመግባቱ ወይም ስምምነት ከማድረጉ በፊት ሞቷል። ዮሐንስ መንግሥተ ሰማያትን እንደማይወርስ ኢየሱስ የተናገረው ለዚህ ነው። ከዚህ ይልቅ ዮሐንስ የአምላክ መንግሥት ምድራዊ ተገዥ ይሆናል። ሉቃስ 7:​18-30፤ ማቴዎስ 11:​2-15

▪ ዮሐንስ ይመጣል ተብሎ የተነገረለት ሰው ኢየሱስ ነው ወይስ ሌላ መጠበቅ ያስፈልጋል የሚል ጥያቄ ያቀረበው ለምንድን ነው?

▪ ዮሐንስ የትኞቹን ትንቢቶች እንደፈጸመ ኢየሱስ ተናግሯል?

▪ አጥማቂው ዮሐንስ ከኢየሱስ ጋር በሰማይ የማይሆነው ለምንድን ነው?