በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዮሐንስ እየቀነሰ ኢየሱስ ግን እየጨመረ ሄደ

ዮሐንስ እየቀነሰ ኢየሱስ ግን እየጨመረ ሄደ

ምዕራፍ 18

ዮሐንስ እየቀነሰ ኢየሱስ ግን እየጨመረ ሄደ

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በ30 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በጸደይ ወራት ከተከበረው የማለፍ በዓል በኋላ ኢየሩሳሌምን ለቀው ሄዱ። ይሁን እንጂ በገሊላ ወደሚገኘው መኖሪያቸው አልተመለሱም፤ ከዚህ ይልቅ ወደ ይሁዳ አገር ሄዱና ሰዎችን አጠመቁ። አጥማቂው ዮሐንስ ይህንኑ ሥራ ማከናወን ከጀመረ ወደ አንድ ዓመት ገደማ ሆኖታል፤ በዚህም ጊዜ ቢሆን ዮሐንስ እርሱን የሚከተሉ ደቀ መዛሙርት ነበሩት።

እርግጥ ኢየሱስ ራሱ አላጠመቀም። ደቀ መዛሙርቱ ግን የእርሱን መመሪያ በመከተል አጥምቀዋል። እነርሱ ያከናውኑት የነበረው ጥምቀትም ዮሐንስ ካከናወነው ጥምቀት ጋር አንድ ትርጉም ነበረው:- አይሁዶች የአምላክን የሕግ ቃል ኪዳን በመጣስ ለፈጸሙት ኃጢአት ንስሐ መግባታቸውን የሚያሳይ ምልክት ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ አንድ ልዩ ትርጉም ያለው ጥምቀት እንዲያከናውኑ አዟቸዋል። በአሁኑ ጊዜ የሚደረገው ክርስቲያናዊ ጥምቀት አንድ ሰው ይሖዋ አምላክን ለማገልገል ራሱን ለእርሱ መወሰኑን የሚያመለክት ነው።

ይሁን እንጂ በዚህ የኢየሱስ አገልግሎት መጀመሪያ ላይ ዮሐንስም ሆነ ኢየሱስ ምንም እንኳ ለየብቻ ሆነው ይሠሩ የነበረ ቢሆንም ሁለቱም ንስሐ የገቡ ሰዎችን እያስተማሩ ያጠምቁ ነበር። ሆኖም የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ቅናት አደረባቸውና “መምህር ሆይ፣ . . . እነሆ፣ እርሱ ያጠምቃል ሁሉም ወደ እርሱ ይመጣሉ” ብለው በኢየሱስ ላይ የተሰማቸውን ቅሬታ ለዮሐንስ ነገሩት።

ዮሐንስ በኢየሱስ ሥራ መሳካት ተደሰተ እንጂ አልቀናም። ደቀ መዛሙርቱም እንደ እሱ እንዲደሰቱ ፈለገ። “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፣ ነገር ግን:- ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንዳልሁ ራሳችሁ ትመሰክሩልኛላችሁ” በማለት ወደ ኋላ መለስ ብሎ አስታወሳቸው። ከዚያም አንድ ግሩም ምሳሌ ተጠቅሞ እንዲህ ሲል አስረዳቸው:- “ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምፅ እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ።”

የሙሽራው ሚዜ የሆነው ዮሐንስ ከስድስት ወራት በፊት ደቀ ­መዛሙርቱን ከኢየሱስ ጋር ሲያስተዋ​­ውቅ በጣም ተደስቶ ነበር። ከእነር​­ሱም መካከል አንዳንዶቹ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችን የምታቅፈው የክርስቶስ ሰማ​­ያዊት ሙሽራ ክፍል እጩ አባላት ሆነዋል። የዮሐንስ ዓላማ የክርስቶስ አገልግሎት የተሳካ እንዲሆን መንገዱን ማዘጋጀት በመሆኑ የአሁኖቹ ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስን እንዲከተሉ ፈልጎ ነበር። “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል” ሲል አጥማቂው ዮሐንስ ገልጿል።

ቀደም ሲል የአጥማቂው ዮሐንስ ደቀ መዝ​­ሙር የነበረው አዲሱ የኢ​­የሱስ ደቀ መዝ⁠ሙር ዮሐንስ፣ ኢየሱስ ከየት እን​­ደመጣና በሰው ልጆች መዳን ረገድ የሚጫወተውን ከፍተኛ ሚና በማስመልከት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው። . . . አባት ልጁን ይወዳል ሁሉንም በእጁ ሰጥቶታል። በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።”

አጥማቂው ዮሐንስ የእሱ ሥራ እየቀነሰ እንደሚሄድ ከተናገረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ንጉሥ ሄሮድስ አሰረው። ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን የራሱ ሚስት አድርጎ ወስዷት ነበር። ዮሐንስ አድራጎቱ ትክክል እንዳልሆነ በሕዝብ ፊት ባጋለጠው ጊዜ ሄሮድስ ወደ ወኅኒ አወረደው። ዮሐንስ መታሰሩን ሲሰማ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይሁዳን ለቆ ወደ ገሊላ ሄደ። ዮሐንስ 3:​22 እስከ 4:​3፤ ሥራ 19:​4፤ ማቴዎስ 28:​19፤ 2 ቆሮንቶስ 11:​2፤ ማርቆስ 1:​14፤ 6:​17-20

▪ ኢየሱስ ሞቶ ከመነሳቱ በፊት በእሱ አመራር የተከናወነው ጥምቀት ምን ትርጉም ነበረው? ከሞት ከተነሳ በኋላ ያለው ጥምቀትስ ምን ትርጉም አለው?

▪ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱ የተሰማቸው ቅሬታ ተገቢ አለመሆኑን የገለጸው እንዴት ነው?

▪ ዮሐንስ የታሰረው ለምንድን ነው?