በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደቀ መዝሙር መሆን የሚያስከትለው ኃላፊነት

ደቀ መዝሙር መሆን የሚያስከትለው ኃላፊነት

ምዕራፍ 84

ደቀ መዝሙር መሆን የሚያስከትለው ኃላፊነት

ኢየሱስ ከታወቀው ፈሪሳዊ (ሰውየው የሳንሄድሪን ሸንጎ አባል ሳይሆን አይቀርም) ቤት ወጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞውን ቀጠለ። ኢየሱስ ሲሄድ ብዙ ሕዝብ ተከተለው። ይሁን እንጂ እሱን እንዲከተሉ የገፋፋቸው ነገር ምንድን ነው? የኢየሱስ እውነተኛ ተከታይ መሆን ምን ነገሮችን ያጠቃልላል?

ሕዝቡ አብረውት እየተጓዙ ሳሉ ኢየሱስ ወደ እነሱ ዞሮ እንዲህ ሲላቸው ሳይደነግጡ አልቀረም:- “ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ፣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።”

ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር? እዚህ ላይ ኢየሱስ ተከታዮቹ ቃል በቃል ዘመዶቻቸውን መጥላት አለባቸው ማለቱ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለዘመዶቻቸው ያላቸው ፍቅር ለእሱ ካላቸው ፍቅር ያነሰ መሆን አለበት ማለቱ ነው። የኢየሱስ ቅድመ አያት የነበረው ያዕቆብ ልያን ‘ይጠላ’ እንደነበረና ራሔልን ይወድ እንደነበር ተገልጿል፤ ይህ ማለት ለልያ የነበረው ፍቅር ለራሔል ከነበረው ፍቅር ያነሰ ነበር ማለት ነው።

ኢየሱስ አንድ ደቀ መዝሙር “የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር” መጥላት እንዳለበት መናገሩንም ልብ በል። አሁንም ቢሆን ኢየሱስ ይህን ሲል አንድ እውነተኛ ደቀ መዝሙር ከራሱ ሕይወት እንኳ ሳይቀር አስበልጦ ሊወደው እንደሚገባ መናገሩ ነው። በዚህ መንገድ ኢየሱስ የእሱ ደቀ መዝሙር መሆን ከባድ ኃላፊነት የሚያስከትል መሆኑን ጎላ አድርጎ ገልጿል። በሚገባ ሳያስቡበት እንዲሁ ዘው ተብሎ የሚገባበት ነገር አይደለም።

ኢየሱስ ቀጥሎ “ማንም መስቀሉን [“የመከራውን እንጨት፣” NW] ተሸክሞ በኋላዬ የማይመጣ፣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም” በማለት እንዳመለከተው የእሱ ደቀ መዝሙር መሆን መከራና ስደት ያስከትላል። ስለዚህ አንድ እውነተኛ ደቀ መዝሙር ኢየሱስ የተሸከመውን ዓይነት የነቀፋ ሸክም ለመሸከም ፈቃደኛ መሆን አለበት፤ ይህም ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንዳደረገው አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በአምላክ ጠላቶች እጅ መሞትንም ይጨምራል።

ስለዚህ ኢየሱስን እየተከተለው ያለው ሕዝብ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን የሚያስከትለውን ኃላፊነት በጥሞና ሊያስብበት ይገባል። ኢየሱስ ይህን ሐቅ አንድ ምሳሌ በመጠቀም ጠበቅ አድርጎ ገልጾታል። እንዲህ አለ:- “ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ኪሳራውን የማይቈጥር ማን ነው? ያለዚያ መሠረቱን ቢመሠርት፣ ሊደመድመውም ቢያቅተው፣ ያዩት ሁሉ:- ይህ ሰው ሊሠራ ጀምሮ ሊደመድመው አቃተው ብለው ሊዘብቱበት ይጀምራሉ።”

ስለዚህ ኢየሱስ ግንብ ለመሥራት የሚፈልግ አንድ ሰው ግንባታውን ከመጀመሩ በፊት ሠርቶ ለመጨረስ የሚያስችለው በቂ ገንዘብ እንዳለውና እንደሌለው ለማረጋገጥ እንደሚያሰላ ሁሉ እየተከተሉት ያሉት ሰዎችም ደቀ መዛሙርቱ ከመሆናቸው በፊት የእሱ ደቀ መዝሙር መሆን የሚያስከትለውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እችላለሁ ብለው ቁርጥ ያለው ውሳኔ ላይ መድረስ እንዳለባቸው በምሳሌ አስረድቷቸዋል። ኢየሱስ በመቀጠል ሌላ ምሳሌ አቀረበ:-

“ወይም ሌላውን ንጉሥ በጦርነት ሊጋጠም የሚሄድ፣ ከሁለት እልፍ ጋር የሚመጣበትን በአንድ እልፍ ሊገናኝ የሚችል እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ የማያስብ ንጉሥ ማን ነው? ባይሆንስ ሌላው ገና ሩቅ ሳለ መልክተኞች ልኮ ዕርቅ ይለምናል።”

ከዚያም ኢየሱስ “እንግዲህ እንደዚሁ ማንም ከእናንተ ያለውን ሁሉ የማይተው ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም” በማለት የምሳሌዎቹን ፍሬ ነገር ጎላ አድርጎ ገልጿል። እየተከተሉት የነበሩት ሰዎችም ሆኑ ስለ ክርስቶስ የተማሩ ሰዎች ሁሉ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን አለባቸው። የእሱ ደቀ መዛሙርት መሆን ከፈለጉ ያላቸውን ነገር ሁሉ ማለትም ሕይወታቸውን ጨምሮ ንብረታቸውን ሁሉ መሥዋዕት ለማድረግ ዝግጁ መሆን አለባቸው። አንተ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ነህን?

“ጨው መልካም ነው” በማለት ኢየሱስ ንግግሩን ቀጠለ። በተራራው ስብከቱ ላይ ደቀ መዛሙርቱ “የምድር ጨው” እንደሆኑ ተናግሮ ነበር፤ ይህ ማለት ጨው ምግብን ከመበላሸት እንደሚጠብቀው ሁሉ እነርሱም ሕይወትን ከጥፋት የሚጠብቅ በጎ ተጽዕኖ በሰዎች ላይ ያሳድራሉ ማለት ነው። “የጨውነቱን ጣዕም ካጣ ግን በምን ሊጣፍጥ ይችላል? እንዲህ ዐይነቱ ጨው ለእርሻ መሬትም ሆነ ለማዳበሪያ የማይጠቅም ስለሆነ ወዲያ አውጥተው ይጥሉታል፤ እንግዲህ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ” (የ1980 ትርጉም) በማለት ኢየሱስ ደመደመ።

ስለዚህ ኢየሱስ ለተወሰነ ጊዜ የእርሱ ደቀ መዛሙርት ሆነው የቆዩ ሰዎች እንኳ ይህን አቋማቸውን እንደያዙ ለመቀጠል ያላቸው ቁርጠኝነት መላላት እንደሌለበት አመልክቷል። ይህ አቋማቸው ከላላ ዋጋ ቢስና የዚህ ዓለም መዘበቻ ይሆናሉ። በአምላክ ፊት ብቃት የጎደላቸው፣ እንዲያውም በአምላክ ላይ ነቀፋ የሚያመጡ ይሆናሉ። ከዚያ በኋላ ጣዕሙን እንዳጣ የተበከለ ጨው ወደ ውጭ ይጣላሉ፣ አዎን፣ ይጠፋሉ። ሉቃስ 14:​25-35፤ ዘፍጥረት 29:​30-33፤ ማቴዎስ 5:​13

▪ ዘመዶችንና ራስን ‘መጥላት’ ማለት ምን ማለት ነው?

▪ ኢየሱስ የትኞቹን ሁለት ምሳሌዎች ሰጥቷል? ትርጉማቸውስ ምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ ጨውን አስመልክቶ የሰጠው የማጠቃለያ ሐሳብ ፍሬ ነገር ምንድን ነው?