በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደቀ መዝሙር ይሆናል ተብሎ ያልታሰበ ሰው

ደቀ መዝሙር ይሆናል ተብሎ ያልታሰበ ሰው

ምዕራፍ 45

ደቀ መዝሙር ይሆናል ተብሎ ያልታሰበ ሰው

ኢየሱስ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሲወጣ አንድ በጣም አስፈሪ የሆነ ነገር ተመለከተ! በጣም ኃይለኛ የሆኑ ሁለት ሰዎች በአቅራቢያ ከሚገኘው መካነ መቃብር ወጥተው ወደእሱ እየሮጡ መጡ። ጋኔን የያዛቸው ሰዎች ነበሩ። አንደኛው ከሌላኛው ይበልጥ ኃይለኛ የሆነና በጋኔን ቁጥጥር ሥር ለረጅም ጊዜ ሲሠቃይ የኖረ ሰው ሳይሆን አይቀርም። ስለዚህ ይበልጥ ትኩረት የሳበው እሱ ነበር።

ይህ አሳዛኝ ሰው ለረጅም ጊዜ ራቁቱን በመቃብሮች መካከል ይኖር ነበር። ዘወትር ቀን ከሌት እየጮኸ ሰውነቱን በድንጋይ እየቧጨረ ያቆስል ነበር። በጣም ኃይለኛ ስለነበረ በዚያ መንገድ ለማለፍ የሚደፍር ሰው አልነበረም። ሰውየውን ለማሰር ብዙ ጥረት የተደረገ ቢሆንም ሰንሰለቱን በጣጥሶና እግር ብረቱን ሰባብሮ ከእግሩ ላይ ይጥለው ነበር። እሱን መቋቋም የሚያስችል ኃይል ያለው ሰው አልነበረም።

ሰውየው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ እግሩ ላይ ሲወድቅ ሰውየውን የያዙት አጋንንት “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፣ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳትሣቅየኝ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ” ብሎ እንዲጮኽ አደረጉት።

ኢየሱስ ደጋግሞ “አንተ ርኩስ መንፈስ፣ ከዚህ ሰው ውጣ” አለው። ከዚያም ኢየሱስ “ስምህ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው።

“ብዙዎች ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው” ሲል መለሰለት። አጋንንት የያዟቸውን ሰዎች ማሠቃየት ያስደስታቸዋል። ፍርሃት በተቀላቀለበት የቁጣ መንፈስ ብዙ ሆነው በሰዎቹ ላይ መስፈር የሚያስደስታቸው ይመስላል። ሆኖም ከኢየሱስ ጋር ፊት ለፊት ሲፋጠጡ ወደ ጥልቁ እንዳይሰዳቸው ለመኑት። ኢየሱስ ታላቅ ኃይል እንዳለው አሁንም መመልከት እንችላለን። ጨካኝ የሆኑ አጋንንትን እንኳ ሳይቀር ድል ማድረግ ይችላል። በተጨማሪም ይህ ሁኔታ አምላክ በእነርሱ ላይ በሚበይነው የመጨረሻ ፍርድ አጋንንት ከመሪያቸው ከሰይጣን ዲያብሎስ ጋር ወደ ጥልቁ እንደሚጣሉ የሚያውቁ መሆኑን ያሳያል።

በዚያው አቅራቢያ በተራራ ላይ ወደ 2,000 የሚጠጋ የዓሳማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር። ስለዚህ አጋንንቱ “ወደ እሪያዎቹ እንድንገባ ስደደን” አሉት። አጋንንቱ ሥጋዊ አካል ወዳላቸው ፍጥረታት ሰውነት ውስጥ በመግባት ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ አረመኔያዊ እርካታ እንደሚያገኙ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ኢየሱስ ወደ ዓሳማዎቹ እንዲገቡ ሲፈቅድላቸው 2,000 የሚሆኑት ዓሳማዎች በሙሉ እየፈረጠጡ ከተራራው አፋፍ ተወርውረው ባሕሩ ውስጥ ሰጠሙ።

ዓሳማዎቹን ይጠብቁ የነበሩት ሰዎች ይህን ሲመለከቱ በፍጥነት ሄደው ወሬውን በከተማውና በገጠሩ አዳረሱ። በዚህ ጊዜ ሰዎቹ የተ​ፈጸመውን ነገር ለማየት መጡ። በቦታው ሲደርሱ ከአጋንንቱ የተላቀቀውን ሰው አዩት። ልብስ ለብሶና አእምሮው ጤናማ ሆኖ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ ነበር!

ሰውየው ጤናማ ሊሆን የቻ​ለው እንዴት እንደሆነ በቦ⁠ታው የነ⁠በሩ የዓይን ምሥክሮች አወሩ። ስለ ዓሳማዎቹ አስደንጋጭ አሟሟትም ለሰዎቹ ነገሯቸው። ሰዎቹ ይህን ሲሰሙ ታላቅ ፍርሃት አደረባቸውና ኢየሱስ ክልሉን ለቅቆ እንዲሄድ አጥብቀው ለመኑት። ስለዚህ ኢየሱስ ልመናቸውን ሰምቶ ጀልባው ላይ ተሳፈረ። ቀደም ሲል በአጋንንት ተይዞ የነበረው ሰው አብሮት እንዲሄድ ይፈቅድለት ዘንድ ኢየሱስን ለመነው። ሆኖም ኢየሱስ እንዲህ አለው:- “ወደ ቤትህ በቤተ ሰዎችህ ዘንድ ሄደህ ጌታ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገልህ እንዴትስ እንደ ማረህ አውራላቸው።”

ብዙውን ጊዜ ኢየሱስ የፈወሳቸውን ሰዎች ለማንም እንዳይናገሩ ያዛቸው ነበር፤ ምክንያቱም ሰዎች ስሜት ቀስቃሽ በሆኑ የተጋነኑ ወሬዎች ላይ የተመሠረቱ መደምደሚያዎች ላይ እንዲደርሱ አይፈልግም ነበር። በዚህኛው ጊዜ ግን ቀደም ሲል አጋንንት ይዘውት የነበሩት ይህ ሰው ኢየሱስ ምናልባት ሊያገኛቸው ለማይችላቸው ሰዎች ስለሚመሰክር ሁኔታውን ለየት ባለ መንገድ መያዙ ተገቢ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሰውየው በቦታው መኖሩ ዓሳማዎቹ በማለቃቸው ምክንያት ሊባዛ የሚችለውን መጥፎ ወሬ በመከላከል ኢየሱስ ጥሩ ለመሥራት ኃይል እንዳለው ምሥክርነት ይሰጣል።

ቀደም ሲል በአጋንንት ተይዞ የነበረው ሰው የኢየሱስን መመሪያ ተቀብሎ ሄደ። ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር ሁሉ በመላዋ ዲካፖሊስ መናገር ጀመረ፤ ሰዎቹም በጣም ተገረሙ። ማቴዎስ 8:​28-34፤ ማርቆስ 5:​1-20፤ ሉቃስ 8:​26-39፤ ራእይ 20:​1-3

▪ በአጋንንት መንፈስ የተያዙት ሰዎች ሁለት ሆነው ሳለ በአንደኛው ላይ ትኩረት የተደረገው ለምን ሊሆን ይችላል?

▪ አጋንንት ወደፊት ወደ ጥልቁ እንደሚጣሉ የሚያውቁ መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?

▪ አጋንንት ሰዎችንና እንስሳትን መያዝ የሚያስደስታቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

▪ ኢየሱስ አጋንንት ይዘውት የነበረውን ሰው እሱ ያደረገለትን ነገር ለሌሎች እንዲናገር በማዘዝ ሁኔታውን ለየት ባለ መንገድ የያዘው ለምንድን ነው?