በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደግ ባልንጀራ የሆነ ሳምራዊ

ደግ ባልንጀራ የሆነ ሳምራዊ

ምዕራፍ 73

ደግ ባልንጀራ የሆነ ሳምራዊ

ኢየሱስ ያለው ከኢየሩሳሌም ሦስት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው ቢታንያ በምትባለው መንደር አቅራቢያ ሳይሆን አይቀርም። የሙሴን ሕግ ጠንቅቆ የሚያውቅ አንድ ሰው ቀረበውና “መምህር ሆይ፣ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” ብሎ ጠየቀው።

ኢየሱስ ይህ ሕግ አዋቂ የጠየቀው እንዲሁ እውቀት ለማግኘት ብሎ ሳይሆን ሊፈትነው ፈልጎ እንደሆነ አውቆ ነበር። የሕግ አዋቂው ዓላማ ኢየሱስ የአይሁዶችን ስሜት በሚጎዳ መንገድ እንዲመልስ ለማድረግ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ኢየሱስ “በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ?” ብሎ በመጠየቅ ሕግ አዋቂው ራሱ እንዲመልስ አደረገው።

ሕግ አዋቂው ያልተለመደ ዓይነት ማስተዋል በማሳየት ከ⁠ዘዳግም 6:​5⁠ና ከ⁠ዘሌዋውያን 19:​18 ላይ ጠቅሶ እንዲህ ሲል መለሰ:- “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፣ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ።”

ኢየሱስም መልሶ “እውነት መለስህ” አለው። “ይህን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ።”

ይሁን እንጂ ሕግ አዋቂው በዚህ አልረካም። የኢየሱስ መልስ እሱ የፈለገውን ያህል ቀጥተኛ አልሆነለትም። የእሱ የራሱ አመለካከት ትክክለኛ መሆኑንና ለሌሎች በሚያሳየው ባሕርይ ረገድ ጻድቅ መሆኑን ኢየሱስ እንዲያረጋግጥለት ፈልጎ ነበር። ስለዚህ “ባልንጀራዬስ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው።

አይሁዶች “ባልንጀራ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው መሰል የሆኑ አይሁዶችን ብቻ ነው የሚል እምነት ነበራቸው፤ በ⁠ዘሌዋውያን 19:​18 ዙሪያ ያለውም ሐሳብ ይህን የሚያመለክት ይመስላል። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስም እንኳ “አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ” ብሏል። ስለዚህ ሕግ አዋቂው፣ ምናልባትም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጭምር፣ በእነሱ አመለካከት አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች ባልንጀሮቻቸው ስላልሆኑ ለመሰል አይሁዶች ብቻ ደግነት ካሳዩ ጻድቃን እንደሆኑ አድርገው ያምኑ ነበር።

ኢየሱስ አድማጮቹን ሳያስከፋ አመለካከታቸውን ማስተካከል የሚችለው እንዴት ነው? አንድ ታሪክ ነገራቸው። ታሪኩ በእውነተኛ ገጠመኝ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል። “አንድ ሰው [አይሁዳዊ]” በማለት ኢየሱስ ታሪኩን መናገር ጀመረ፤ “ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ።”

ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ፤ አይቶትም አዘነለት።”

ብዙ ካህናትና በቤተ መቅደስ አገልግሎት የሚረዷቸው ሌዋውያን ይኖሩ የነበረው በኢያሪኮ ሲሆን በቤተ መቅደስ ከሚያገለግሉበት ከኢየሩሳሌም በ23 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደዚህች ከተማ ይመጡ የነበረው 900 ኪሎ ሜትር ድረስ ወደ ታች እያቆለቆለ በሚሄድ አደገኛ መንገድ ላይ ነበር። ካህኑና ሌዋዊው ከፍተኛ አደጋ የደረሰበትን መሰል አይሁዳዊ መርዳት ይጠበቅባቸው ነበር። ሆኖም እንደዚያ አላደረጉም። አይሁዳዊውን የረዳው አንድ ሳምራዊ ነበር። አይሁዳውያን ሳምራውያንን በጣም ይጠሏቸው ስለነበረ ከጥቂት ጊዜ በፊት ኢየሱስን “ሳምራዊ” በማለት ዘልፈውታል።

ሳምራዊው አይሁዳዊውን ለመርዳት ምን አደረገ? ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቊስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፣ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደርያ ወሰደው ጠበቀውም። በማግሥቱም ሁለት ዲናር [የሁለት ቀን ደመወዝ ያህል] አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና:- ጠብቀው፣ ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ አለው።”

ኢየሱስ ታሪኩን ከነገረው በኋላ ሕግ አዋቂውን “ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል?” ብሎ ጠየቀው።

ሕግ አዋቂው አንድ ሳምራዊ መልካም ሥራ ሠራ ብሎ በቀጥታ መናገር ደስ ስላላለው “ምሕረት ያደረገለት” ብቻ ብሎ መለሰ።

ኢየሱስ “ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ” በማለት ደመደመ።

ኢየሱስ ሕግ አዋቂውን አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎችም ባልንጀሮችህ ናቸው ብሎ በቀጥታ መልሶለት ቢሆን ኖሮ ሰውየው ይህን አይቀበልም ነበር፤ አብዛኞቹ አድማጮችም ከኢየሱስ ጋር በተደረገው ውይይት ለሰውየው ሊወግኑ ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ በእውነታ ላይ የተመረኮዘ ታሪክ ከእኛ ዘርና ብሔር የተለዩ ሰዎችም ጭምር ባልንጀሮቻችን እንደሆኑ በማያወላዳ መንገድ ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል። ኢየሱስ የሚያስተምርበት መንገድ ምንኛ የሚያስደንቅ ነው! ሉቃስ 10:​25-37፤ ሥራ 10:​28፤ ዮሐንስ 4:​9፤ 8:​48

▪ ሕግ አዋቂው ለኢየሱስ ያቀረባቸው ጥያቄዎች ምንድን ናቸው? ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ጥያቄውን ያቀረበበት ዓላማስ ምንድን ነው?

▪ አይሁዶች ባልንጀሮቻችን እነማን ናቸው ብለው ያምኑ ነበር? ደቀ መዛሙርቱም እንኳ ሳይቀሩ ይህ አመለካከት ነበራቸው እንድንል የሚያደርገን ነገር ምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ፣ ሕግ አዋቂው ሊያስተባብለው በማይችለው መንገድ ትክክለኛውን አመለካከት ያስተማረው እንዴት ነው?