በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጋኔን የያዘው ልጅ ተፈወሰ

ጋኔን የያዘው ልጅ ተፈወሰ

ምዕራፍ 61

ጋኔን የያዘው ልጅ ተፈወሰ

ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ርቀው ሄደው በነበረበት ወቅት፣ ምናልባትም በአርሞንዔም ተራራ ተረተር ላይ በነበሩበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም፣ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ችግር ውስጥ ገብተው ነበር። ኢየሱስ ሲመለስ አንድ ችግር እንዳለ ወዲያውኑ ተረዳ። በደቀ መዛሙርቱ ዙሪያ ብዙ ሕዝብ ተሰብስቦ ነበር፤ ጻፎቹ ደግሞ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እየተከራከሩ ነበር። ሰዎቹ ኢየሱስን ሲያዩ በጣም ተገረሙና ሰላምታ ሊሰጡት ሮጡ። “ስለ ምን ከእነርሱ ጋር ትከራከራላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው ወጣና ኢየሱስ ፊት ተንበርክኮ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “መምህር ሆይ፣ ዲዳ መንፈስ ያደረበትን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼአለሁ፤ በያዘውም ስፍራ ሁሉ ይጥለዋል፤ አረፋም ይደፍቃል፣ ጥርሱንም ያፋጫል ይደርቃልም፤ እንዲያወጡለትም ለደቀ መዛሙርትህ ነገርኋቸው፣ አልቻሉምም።”

ጻፎቹ ደቀ መዛሙርቱ ልጁን መፈወስ ባለመቻላቸው ያቃልሏቸውና ያሾፉባቸው የነበረ ይመስላል። በዚህ ወሳኝ ጊዜ ላይ ኢየሱስ ከተፍ አለ። ኢየሱስ “የማታምን ትውልድ ሆይ፣ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ?” ሲል ተናገረ።

ኢየሱስ የተናገረው በቦታው ለነበሩት ሰዎች ሁሉ ይመስላል፤ ሆኖም የተናገረው ነገር በይበልጥ ያነጣጠረው ደቀ መዛሙርቱን ሲያስጨንቁ በነበሩት ጻፎች ላይ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ቀጥሎ ኢየሱስ ልጁን “ወደ እኔ አምጡት” አላቸው። ሆኖም ልጁን ወደ ኢየሱስ ሲያመጡት የያዘው ጋኔን መሬት ላይ ጣለውና አንፈራገጠው። ልጁ መሬት ላይ እየተንከባለለ አረፋ ደፈቀ።

ኢየሱስ “ይህ ከያዘው ስንት ዘመን ነው?” ሲል ጠየቀ።

አባትየውም “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው” ሲል መለሰ። “ብዙ ጊዜም [ጋኔኑ] ሊያጠፋው ወደ እሳትም ወደ ውኃም ጣለው።” ከዚያም አባትየው “ቢቻልህ ግን እዘንልን እርዳንም” ብሎ ለመነው።

ምናልባትም አባትየው ለብዙ ዓመታት እርዳታ ለማግኘት ሲሞክር ቆይቶ ይሆናል። አሁን ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሊሳካላቸው ባለመቻሉ ተስፋው በጣም መንምኖበታል። ኢየሱስ የሰውየውን አሳዛኝ ልመና በድጋሚ በመጥቀስ “ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል” በማለት አበረታታው።

አባትየው ወዲያውኑ “አምናለሁ” በማለት ጮክ ብሎ ተናገረ፤ ሆኖም “አለማመኔን እርዳው” ብሎ ለመነው።

ኢየሱስ ሕዝቡ ወደ እነሱ እየተንጋጋ ሲመጣ አየና ጋኔኑ “አንተ ዲዳ ደንቆሮም መንፈስ፣ እኔ አዝሃለሁ፣ ከእርሱ ውጣ እንግዲህም አትግባበት” ሲል ገሠጸው። ጋኔኑ ልጁን ሲለቀው እንደገና እንዲጮኽና በኃይል እንዲፈራገጥ አደረገው። ከዚያም ልጁ ጸጥ ብሎ መሬቱ ላይ ተጋደመ፤ በዚህ ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች “ሞተ” ማለት ጀመሩ። ሆኖም ኢየሱስ እጁን ይዞ አስነሣው።

ቀደም ሲል ደቀ መዛሙርቱ ለስብከት ሥራ ሲላኩ አጋንንት አውጥተው ነበር። ስለዚህ አሁን ወደ ቤት ሲገቡ ብቻቸውን ሆነው ኢየሱስን “እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምንድር ነው?” ብለው ጠየቁት።

ኢየሱስ ይህ ሊሆን የቻለው እምነት ስለጎደላቸው መሆኑን በማመልከት “እንዲህ ዐይነቱ በጸሎት ካልሆነ በቀር በሌላ በምንም አይወጣም” አላቸው። (የ1980 ትርጉም) በዚህ ወቅት ይህን ለየት ያለ ኃይል ያለው ጋኔን ለማስወጣት ዝግጅት ያስፈልግ እንደነበረ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ሁኔታው ጠንካራ እምነት የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ ኃይል የሚሰጠውን የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት መጸለይ ያስፈልግ ነበር።

ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ ሲል አክሎ ተና​ገረ:- “እውነት እላችኋለሁ፣ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህን ተራራ:- ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል የሚሳናችሁም ነገር የለም።” እምነት እንዴት ያለ ታላቅ ኃይል ሊኖረው ይችላል!

በይሖዋ አገልግሎት የምናደርገውን እድገት የሚገቱ እንቅፋቶችና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ልክ እንደ አንድ ትልቅ ተራራ ልንወጣቸውና ልናስወግዳቸው የማንችላቸው ነገሮች ሆነው ሊታዩን ይችላሉ። ሆኖም ኢየሱስ በልባችን ውስጥ እምነት ብንተክልና ውኃ እያጠጣን እንዲያድግ ብናደርገው ወደ መብሰል ደረጃ ደርሶ እንደ ተራራ የመሰሉ እንቅፋቶችንና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንድንቋቋም የሚያስችለን መሆኑን አመልክቷል። ማርቆስ 9:​14-29፤ ማቴዎስ 17:​19, 20፤ ሉቃስ 9:​37-43

▪ ኢየሱስ ከአርሞንዔም ተራራ ሲመለስ ምን ሁኔታ አጋጠመው?

▪ ኢየሱስ ጋኔን ይዞት ለነበረው ልጅ አባት ምን ማበረታቻ ሰጠው?

▪ ደቀ መዛሙርቱ ጋኔኑን ማስወጣት ያልቻሉት ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ እምነት ምን ያህል ኃይል ሊኖረው እንደሚችል አመልክቷል?