በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፈሪሳውያን ሆነ ብለው ለማመን አልፈለጉም

ፈሪሳውያን ሆነ ብለው ለማመን አልፈለጉም

ምዕራፍ 71

ፈሪሳውያን ሆነ ብለው ለማመን አልፈለጉም

ቀደም ሲል ዓይነ ስውር የነበረው ለማኝ ወላጆች ተጠርተው ፈሪሳውያን ፊት ሲቀርቡ ፍርሃት አደረባቸው። በኢየሱስ የሚያምን ሰው ሁሉ ከምኩራብ እንዲባረር የተወሰነ መሆኑን ያውቁ ነበር። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ በማኅበረሰቡ ውስጥ ካሉ ሌሎች ሰዎች ጋር መቆራረጥ በተለይ በአንድ ድሃ ቤተሰብ ላይ ከፍተኛ ችግር ሊያስከትል ይችላል። ስለዚህ ወላጆቹ መልስ የሰጡት በጥንቃቄ ነበር።

“እናንተ ዕውር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን?” ብለው ፈሪሳውያን ጠየቋቸው። “ታድያ አሁን እንዴት ያያል?”

ወላጆቹ “ይህ ልጃችን እንደ ሆነ ዕውርም ሆኖ እንደ ተወለደ እናውቃለን” በማለት አረጋገጡላቸው። “ዳሩ ግን አሁን እንዴት እንዳየ አናውቅም፣ ወይም ዓይኖቹን ማን እንደ ከፈተ እኛ አናውቅም።” ልጁ የተፈጸመውን ነገር ሁሉ ለወላጆቹ እንደነገራቸው ጥርጥር የለውም፤ ሆኖም ወላጆቹ ዘዴ በመጠቀም “ጠይቁት እርሱ ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱ ስለ ራሱ ይናገራል” አሏቸው።

ስለዚህ ፈሪሳውያኑ ሰውየውን እንደገና ጠሩት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስን ለመወንጀል የሚያበቁ ማስረጃዎች እንደሰበሰቡ በማመልከት ሊያስፈራሩት ሞከሩ። “እግዚአብሔርን አክብር” አሉት። “ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን።”

ዓይነ ስውር የነበረው ሰው ክሳቸውን አላስተባበለም። “ኃጢአተኛ መሆኑን አላውቅም” አላቸው። ሆኖም “ዕውር እንደ ነበርሁ አሁንም እንዳይ ይህን አንድ ነገር አውቃለሁ” ሲል አክሎ ተናገረ።

ፈሪሳውያን በሰውየው የምሥክርነት ቃል ላይ ስህተት ለማግኘት ሲሉ “ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዓይኖችህን ከፈተ?” ብለው እንደገና ጠየቁት።

“አስቀድሜ ነገርኋችሁ” በማለት ሰውየው ተቃወማቸው፤ “አልሰማችሁምም፤ ስለ ምን ዳግመኛ ልትሰሙ ትወዳላችሁ?” ከዚያም “እናንተ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትወዳላችሁን?” በማለት የምጸት ጥያቄ አቀረበላቸው።

ይህ መልስ ፈሪሳውያኑን አስቆጣቸው። “አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ነህ” በማለት ወነጀሉት፤ “እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እናውቃለን፣ ይህ ሰው ከወዴት እንደሆነ አናውቅም አሉት።”

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው ለማኝ በመገረም “ከወዴት እንደ ሆነ እናንተ አለማወቃችሁ ይህ ድንቅ ነገር ነው፣ ዳሩ ግን ዓይኖቼን ከፈተ” ሲል መለሰላቸው። ይህ ወደ ምን መደምደሚያ ሊያደርስ ይገባል? ለማኙ ተቀባይነት ያለውን መሠረታዊ ሐሳብ ጠቀሰ:- “እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢኖር ያንን እግዚአብሔር ይሰማዋል እንጂ ኃጢአተኞችን እንዳይሰማ እናውቃለን። ዕውር ሆኖ የተወለደውን ዓይኖች ማንም እንደ ከፈተ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አልተሰማም።” ስለዚህ መደምደሚያው ግልጽ ሊሆን ይገባል:- “ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ምንም ሊያደርግ ባልቻለም ነበር።”

ፈሪሳውያን ለእንዲህ ዓይነቱ ቀጥተኛና ግልጽ ማስረጃ ምንም መልስ አልነበራቸውም። እውነትን መቋቋም አልቻሉም፤ ስለዚህ “አንተ ሁለንተናህ በኃጢአት ተወለድህ፣ አንተም እኛን ታስተምረናለህን?” በማለት ሰውየውን ሰደቡት። ከዚያም ሰውየውን ወደ ውጭ አስወጡት፤ ከምኩራብም ሳያባርሩት አይቀሩም።

ኢየሱስ ያደረጉትን ሲሰማ ሰውየውን አገኘውና “አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን?” አለው።

ዓይነ ስውር የነበረው ለማኝ “ጌታ ሆይ፣ በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው።

ኢየሱስም “ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው” ብሎ መለሰለት።

ወዲያውኑ ሰውየው በኢየሱስ ፊት ሰገደና “ጌታ ሆይ፣ አምናለሁ” አለ።

ከዚያም ኢየሱስ “የማያዩ እንዲያዩ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጣሁ” ሲል ገለጸ።

በዚህ ጊዜ የሚናገረውን እየሰሙ የነበሩ ፈሪሳውያን “እኛ ደግሞ ዕውሮች ነንን?” ብለው ጠየቁት። በአእምሮ ዕውሮች መሆናቸውን አምነው ቢቀበሉ ኖሮ ኢየሱስን እንዲቃወሙ ያደረጋቸው ነገር ይህ ነው ማለት ይቻል ነበር። ኢየሱስም “ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር” ያላቸው ለዚህ ነው። እነርሱ ግን ልባቸውን አደንድነው ዕውሮች እንዳልሆኑና መንፈሳዊ ብርሃንም እንደማያስፈልጋቸው ይናገሩ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ “እናያለን ትላላችሁ፤ ኃጢአታችሁ ይኖራል” አላቸው። ዮሐንስ 9:​19-41

▪ ዓይነ ስውር የነበረው ለማኝ ወላጆች ፈሪሳውያን ፊት ተጠርተው ሲቀርቡ የፈሩት ለምንድን ነው? በዚህም ምክንያት በጥንቃቄ የመለሱት እንዴት ነው?

▪ ፈሪሳውያን ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው ለማስፈራራት የሞከሩት እንዴት ነው?

▪ ፈሪሳውያኑን ያስቆጣቸው ሰውየው ያቀረበው የትኛው አሳማኝ ማስረጃ ነው?

▪ ፈሪሳውያን ኢየሱስን እንዲቃወሙ ያደረጋቸው በቂ ምክንያት የሌላቸው ለምንድን ነው?