በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ አምላክ መንግሥት ለመስበክ የተደራጁ ጉባኤዎች

ስለ አምላክ መንግሥት ለመስበክ የተደራጁ ጉባኤዎች

ስለ አምላክ መንግሥት ለመስበክ የተደራጁ ጉባኤዎች

ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረበት ጊዜ ከመንደር ወደ መንደርና ከከተማ ወደ ከተማ እየሄደ የእግዚአብሔርን መንግሥት ሰብኳል። ደቀ መዛሙርቱም ይህንኑ እንዲያደርጉ አሠልጥኖ ልኳቸዋል። ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ተከታዮቹ ከአሕዛብ ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ አዟቸዋል። የመጀመሪያው የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የምሥራቹን ለመስበክ ተደራጅቶ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ በደረሱበት ሁሉ የአምላክን መንግሥት ይሰብኩ ነበር።—ማቴዎስ 4:17, 23፤ 10:1–16፤ 28:19, 20፤ ሉቃስ 4:43, 44፤ 8:1፤ 10:1–9፤ ሥራ 1:8፤ 4:31፤ 5:42፤ 8:12፤ 19:8፤ 28:23, 30, 31፤ ሮሜ 10:9, 10, 14

ኢየሱስ ስለ ሥርዓቱ መደምደሚያ በተናገረበት ትንቢት ላይ እንዲህ ብሎአል:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” ይህ የስብከት ሥራ ዛሬም የክርስቲያን ጉባኤ ተቀዳሚ ግዴታ ነው።—ማቴዎስ 24:14፤ ማርቆስ 13:10

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በሙሉ ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራቹን በመስበክ አካባቢያቸውን ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲሸፍኑ በሚያስችል ሁኔታ ተደራጅተዋል። ይህ ሥራ ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲከናወን ሲባል የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ በእያንዳንዱ አገር ላለው ለያንዳንዱ ጉባኤ የሚመሰክርበት ክልል ይመድብለታል። ጉባኤውም ያንን የተመደበለትን ክልል በትናንሽ ክልሎች ይከፋፍልና ምሥራቹን በክልሉ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች የማዳረስ ኃላፊነት ለሚወስዱ ሰዎች ይመድባል።—1 ቆሮንቶስ 14:33, 40

ብዙ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን የሚያነጋግሩት ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ነው። በስብሰባዎቻቸውም ላይ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በመጠቀም እሰዎች ቤት ድረስ ሄደው እንዴት የመንግሥቱን መልእክት ባጭሩ ለማቅረብ እንደሚችሉ ሠልጥነዋል። ስለ አምላክ ቃል ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት ለሚፈልጉ ሰዎች የሚተውላቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችም ይይዛሉ።

በክልሉ ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ሰው በጣም አስፈላጊ የሆነውን የመንግሥት መልእክት የመስማት ዕድል እንዲያገኝ ለማስቻል ምሥክሮቹ ከቤት ወደ ቤት በሚሄዱበት ጊዜ ሰዎቹ በቤታቸው ያልተገኙ መሆናቸውን ወይም በሌላ ምክንያት ሙሉ ምሥክርነት ለመስጠት ያልተቻለ መሆኑን የሚያመለክት ዝርዝር ማስታወሻ መዝግበው ይይዛሉ። ያላገኙአቸውንም ሰዎች በሌላ ጊዜ ተመልሰው ያነጋግራሉ። ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎችም በማስታወሻ ላይ ይይዙና ተመልሰው በመምጣት ተጨማሪ ቅዱስ ጽሑፋዊ ዕውቀት ይሰጡአቸዋል። ፍላጎት ካላቸውም ቋሚ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ያደርጉላቸዋል። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት አለምንም ክፍያ ነው።

የይሖዋ ምሥክሮች በመንገድ ላይ ለሚተላለፉ ሰዎችም መጽሔት ይሰጣሉ። በዚህም መንገድ በቤታቸው ላይገኙ የሚችሉ ብዙ ሰዎችን ለማግኘት ይችላሉ። ሁሉም ሰው የመስማት አጋጣሚ እንዲያገኝ ልባዊ ጥረት ይደረጋል።—ሥራ 17:17፤ ራእይ 14:6, 7፤ 22:17

አብዛኞቹ ሰዎች ምንም ዓይነት ፍላጎት የሌላቸው ሆነው ሳሉ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ሰዎች ቤት መሄዳቸውን የማያቆሙት ለምንድን ነው? የግለሰቦች ሁኔታ እንደሚለወጥና በሌላ የጉብኝት ወቅት አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጡ ወይም ፍላጎት የሚያሳይ ሌላ ሰው በቤተሰቡ ውስጥ ሊገኝ እንደሚችል ታይቷል።

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ‘ከሁሉ አስቀድማችሁ መንግሥቱንና ጽድቁን ፈልጉ’ ብሏል። ከሁሉ አስቀድመን መንግሥቱን መፈለጋችንን ከምናሳይባቸው መንገዶች አንዱ ስለ አምላክ መንግሥት መስበክ ነው። የይሖዋ ምሥክሮችም ይህንን ሥራ በጣም ትልቅ ቦታ ይሰጡታል።—ማቴዎስ 6:33፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:2

● በዘመናችንም እንደሚከናወን የተተነበየው የትኛው የኢየሱስና የቀድሞ ክርስቲያኖች ሥራ ነው?

● የይሖዋ ምሥክሮች የስብከት ሥራ እንዴት ተደራጅቷል?

● አብዛኞቹ ሰዎች ምንም ዓይነት ፍላጎት የማያሳዩ ሆነው ሳሉ የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን ደጋግመው እቤታቸው ድረስ ሄደው የሚያነጋግሩት ለምንድን ነው?

[በገጽ 16, 17 ላይ ሥዕሎች]

የይሖዋ ምሥክሮች በተለያዩ አገሮች የአምላክን መንግሥት ሲሰብኩ

ታይላንድ

ሜክሲኮ

ኔዘርላንድስ

ኮሪያ

ኩራሳኦ

ጋና

ብሪታንያ

አውስትራሊያ