በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፍቅርና በአንድነት የሚገነቡን ጉባኤዎች

በፍቅርና በአንድነት የሚገነቡን ጉባኤዎች

በፍቅርና በአንድነት የሚገነቡን ጉባኤዎች

በምትኖርበት አካባቢ በሚደረጉ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች የጉባኤ ስብሰባዎች ተገኝተህ ታውቅ ይሆናል። ከሁሉም የኑሮ ዘርፍ የተውጣጡ ሰዎች ማለትም ቤተሰቦች፣ ነጠላ (ያላገቡ) ሰዎች፣ በዕድሜ የገፉና ወጣቶች በስብሰባዎቹ ይገኛሉ። ሁሉም የአምልኮ አንድነት ያላቸው ሲሆኑ ሌሎች ሰዎችንም ለመርዳት ፍላጎት አላቸው።

ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በአንድነት ለመሥራት በሚፈልጉበት በማንኛውም ድርጅት ውስጥ አንድ ዓይነት የበላይ ቁጥጥር እንዲኖር ያስፈልጋል። አምላክ የሥርዓት አምላክ ነው፤ በመሆኑም ይህ ሥርዓት በሕዝቦቹ ጉባኤ ውስጥም መታየት ይኖርበታል። እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ ዛሬም ብቃት ያላቸው፣ የጐለመሱና ተሞክሮ ያላቸው ክርስቲያን ወንዶች ሽማግሌዎች ወይም የበላይ ተመልካቾች ሆነው ይሾማሉ። እነርሱም ለጉባኤው የሚያስፈልጉትን መንፈሳዊ ነገሮች እየተከታተሉ እንቅስቃሴውን ይቆጣጠራሉ። በዚህም ሥራቸው ዲያቆናት በመባል በሚታወቁ ሌሎች ታማኝ ሰዎች ይታገዛሉ። እነዚህ ሰዎች ደመወዝ ወይም ሌላ ዓይነት የገንዘብ ጥቅም አያገኙም። ለመተዳደሪያ የሚያስፈልጋቸውን ገቢ አብዛኛውን ጊዜ ከሰብአዊ ሥራቸው እያገኙ ጉባኤውን በነፃ ያገለግላሉ።—1 ቆሮንቶስ 14:⁠33, 40፤ ፊልጵስዩስ 1:1፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:8, 9

እነዚህ ሰዎች የሚመረጡት እንዴት ነው? አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን የሚያሟሉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች መሆን ይገባቸዋል። ‘በልማዳቸው ሁሉ ልከኞች፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያላቸው፣ በሥርዓት የሚሄዱ፣ እንግዳ ተቀባዮች፣ ለማስተማር የሚበቁና ምክንያታዊ የሆኑ፣ ገንዘብ የማይወዱ፣ ቤተሰባቸውን በመልካም የሚያስተዳድሩ፣ አዲስ ክርስቲያን ያልሆኑ፣ በውጭም ካሉት ሰዎች በመልካም የተመሠከረላቸው፣ በትምህርታቸውም ታማኙን ቃል አጥብቀው የሚይዙ’ መሆናቸው ማሟላት ከሚኖርባቸው ብቃቶች ጥቂቶቹ ናቸው።—1 ጢሞቴዎስ 3:1–15፤ ቲቶ 1:7–9

እነዚህ ሰዎች የሚመረጡት በጉባኤው የድምፅ ብልጫ አይደለም። እንዲያውም የአንዳንዶቹ ጉባኤዎች አባላት በአብዛኛው አዲሶች ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህ ይልቅ ብቁ ስለመሆናቸው የድጋፍ ሐሳብ የሚቀርበው ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን ምን ያህል እንደሚያሟሉ ሊያስተውሉ በሚችሉ የጎለመሱና ተሞክሮ ባላቸው ሽማግሌዎች ነው። ከዚያም ሽማግሌዎቹና ዲያቆናቱ የሚሾሙት የመጀመሪያውን መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ ምሳሌ በመከተል በይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል ተቆጣጣሪነት ነው።

እነዚህ ሽማግሌዎች ወይም የበላይ ተመልካቾች ቀሳውስት አይደሉም። በሌሎች ላይ አለቆች በመሆን የሚሰለጥኑ አይደሉም። ኢየሱስ እንደተናገረው ፊተኛ የሚሆን ሁሉ የሁሉም አገልጋይ መሆን አለበት። በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌዎች በእርግጥ ለአምላክ መንግሥት የሚደክሙ የሥራ ባልደረቦች ናቸው።—ማቴዎስ 20:26, 27፤ 23:8–11፤ ሮሜ 12:8፤ 1 ቆሮንቶስ 3:5፤ 4:1, 2፤ ቆላስይስ 4:11፤ 1 ተሰሎንቄ 5:12–14

የበላይ ተመልካቾች እንደመሆናቸው መጠን በስብሰባዎች ላይ የሚቀርበውን ትምህርት ይቆጣጠራሉ። በስብከቱ ሥራ ሌሎችን እየመሩ ይሳተፋሉ። የጉባኤው ተቀዳሚ ዓላማ የመንግሥቱን ምሥራች በተመደበለት ክልል መስበክ ነው። የበላይ ተመልካቾች የጉባኤውን አባሎች በመጎብኘትና በሚያስፈልጋቸው ሁሉ በማበረታታት በእረኝነትም ያገለግላሉ።—ማቴዎስ 24:14፤ ሥራ 1:8፤ 1 ተሰሎንቄ 2:11, 12፤ 5:14, 15፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:24–26፤ ዕብራውያን 13:17፤ ያዕቆብ 5:13–16፤ 1 ጴጥሮስ 5:1–4

በተጨማሪም ሽማግሌዎች የተሳሳተ መንገድ የተከተለ ወይም የጉባኤውን መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና እንዲሁም አንድነት አደጋ ላይ የጣለ ግለሰብ ሲኖር የመገሰጽና የእርማት እርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት አላባቸው።—1 ቆሮንቶስ 5:4, 5, 7, 11–13፤ ቲቶ 1:9፤ 2:15፤ 3:10, 11

ከጉባኤው ጋር አዘውትረህ በመሰብሰብህ ጥሩ ቅርርብ ትመሠርታለህ፣ ብዙ መንፈሳዊ ጥቅሞችም ታገኛለህ።—መዝሙር 35:18፤ 84:10

● እያንዳንዱን ጉባኤ የሚቆጣጠሩት እነማን ናቸው?

● የበላይ ተመልካቾች የሚመረጡት በምን መሠረት ነው?

● ምን ዓይነት ኃላፊነቶች አሉአቸው?

[በገጽ 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የበላይ ተመልካቾች ጉባኤዎችን ያስተምራሉ፤ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው ስብከት ሌሎችን እየመሩ ይሳተፋሉ፣ በእረኝነት ጉብኝቶች ያበረታታሉ፤ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ምክርና ተግሳጽ ይሰጣሉ