በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን የሚያወድሱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማዘጋጀት

አምላክን የሚያወድሱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማዘጋጀት

አምላክን የሚያወድሱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማዘጋጀት

የይሖዋ ምሥክሮች በታተሙ ጽሑፎች አማካኝነት የአምላክን መንግሥት በመስበክ ሥራቸው በጣም የታወቁ ሆነዋል። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ከ1920 ጀምሮ ለሕዝብ የሚታደሉ መጽሔቶችንና መጻሕፍትን ለማዘጋጀት ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል በተውጣጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሲጠቀም ቆይቷል። ይህም የተደረገው በተቻለ መጠን ዝቅተኛ በሆነ ወጪና በአስተማማኝ ሁኔታ ጽሑፎችን ለማዘጋጀት እንዲቻል ነው።

ማኅበሩ ለ70 ዓመታት ያህል መጀመሪያ በብሩክሊን ከዚያም በሌሎች አገሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የማዘጋጀቱን ሥራ አስፋፍቷል። ሥራው በሙሉ ሲሠራ የቆየው ቁጥራቸው እየጨመረ በሄደ ፈቃደኛ ሠራተኞች ነው።

በ1970ዎቹ ዓመታት ማለቂያ ላይ የቀድሞው ዓይነት ጽሑፎችን የማተም ዘዴ እየተቀየረ ቀስ በቀስ በዘመናዊ የኮምፒዩተር ፎቶታይፕሴቲንግና ኦፍሴት መተካት ጀመረ። በዚህ ረገድ አጋጥሞ የነበረው ችግር በወቅቱ የነበሩት የኮምፒዩተር መሣሪያዎች ለተወሰኑ ቋንቋዎች ብቻ የሚያገለግሉ መሆናቸው ነበር። ይሁን እንጂ ማኅበሩ ቀደም ሲል ጀምሮ ጽሑፎችን በ160 ያህል ቋንቋዎች ሲያትም የቆየ ሲሆን በሌሎች ቋንቋዎችም ማተም አስፈላጊ ሆኖ ነበር።

በዚህ ምክንያት ለብዙ ቋንቋዎች ሊያገለግል የሚችል የኤሌክትሮኒክ ፎቶታይፕሴቲንግ ሲስተም እንዲያዘጋጁ ፈቃደኛ ሠራተኞች ተጠሩ። በጣም ጥሩ ውጤት ተገኘ። ለቴክኒካዊ ችግሮች የሚያስፈልጉት መፍትሔዎች ተገኙና ሜፕስ (MEPS) የተባለ የመጻፊያ፣ ጽሑፎችን የማዘጋጃና የፎቶታይፕሴቲንግ ሲስተም ተጀመረ። ይህ ሲስተም ከ200 በሚበልጡ ቋንቋዎች ያገለግላል። ሌሎች ተጨማሪ ቋንቋዎችንም ሊጨምር ይችላል።

በዛሬው ጊዜ ከ100 በሚበልጡ አገሮች ልዩ ልዩ ጽሑፎች እየተተረጐሙ ሜፕስ በተባለ የኮምፒተር ሲስተም አማካኝነት ለኅትመት ይዘጋጃሉ። በሌሎች ተጨማሪ አገሮችም ይህን አሠራር ለመዘርጋት ታቅዷል። በእነዚህ አገሮች የሚኖሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች በዚህ መሣሪያ እንዴት እንደሚሠሩና መሣሪያውንም እንዴት እንደሚይዙ ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። በአሁኑ ጊዜ ማኅበሩ 40 በሚያህሉ አገሮች ከ110 በሚበልጡ ቋንቋዎች መጽሔቶችን እያዘጋጀ ነው። ከእነዚህ አገሮች ውስጥ በ8ቱ ጠንካራ ሽፋን ያላቸው መጻሕፍትና መጽሐፍ ቅዱሶችም ይዘጋጃሉ።

ይህን ሥራ ለመሥራት ጸሐፊዎች፣ ተርጓሚዎች፣ አራሚዎች፣ አታሚዎች፣ መጽሐፍ ጠራዦችና የጉልበት ሥራ የሚሠሩ ሰዎች ያስፈልጋሉ። ከጉባኤዎች ጋር የሚደረገውን የመጻጻፍ ሥራም የሚያከናውኑ ሠራተኞችም ያስፈልጋሉ። አንዳንድ ሠራተኞች ለምግብ የሚያገለግሉ ጥሬ ዕቃዎችን ያመርታሉ፣ ምግብ ያዘጋጃሉ፣ የጽዳትና የልብስ አጠባ ሥራ ይሠራሉ። ይህ ሁሉ ሥራ የሚሠራው ራሳቸውን ዝግጁ አድርገው ባቀረቡና ከተለያዩ አገሮች በተውጣጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች ነው። በ1991 በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ጽሕፈት ቤቶች፣ ፋብሪካዎች፣ የመኖሪያ ቤቶችና እርሻዎች የሚሠሩ 12,068 ፈቃደኛ ሠራተኞች ነበሩ።

እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? ወንዶችና ሴቶች፣ ያላገቡና ያገቡ፣ ወጣቶችና አረጋውያን ሲሆኑ ሁሉም ሕይወታቸውን ለአምላክ የወሰኑ የይሖዋ ምስክሮች ናቸው። አንዳንዶቹ በዚህ ሥራ ለ40፣ ለ50ና ለ60 ዓመታት የቆዩ ናቸው። በሥራ ምድባቸው ላይ በሳምንት በአማካይ 44 ሰዓት ይሠራሉ። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜም ከዚህ የበለጠ ይሠራሉ። በምሽቶችና በሳምንቱ የመጨረሻ ቀኖች የምሥራቹን ከቤት ወደ ቤት ይሰብካሉ ወይም ሌሎች የጉባኤ ሥራዎችን ያከናውናሉ።

እነዚህ ሠራተኞች ቤቴል በሚባሉት የማኅበሩ የመኖሪያ ቤቶች መጠነኛ የመኖሪያ ክፍልና ምግብ ይዘጋጅላቸዋል። በተጨማሪም ለአገልግሎት በሚያደርጉት መጓጓዣና ለግል ወጪያቸው መተኪያ የሚሆን መጠነኛ ገንዘብ ይሰጣቸዋል።

እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ከ1920 ጀምሮ ከ200 በሚበልጡ ቋንቋዎች በዓለም ዙሪያ የታደሉ ከዘጠኝ ቢልዮን የሚበልጡ መጽሐፍ ቅዱሶች፣ መጻሕፍት፣ መጽሔቶችና በራሪ ጽሑፎች አዘጋጅተዋል። የዘላለሙ ምሥራች በሁሉም አገር በሚገኝ ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ይታወጅ ዘንድ የየግል ድርሻቸውን እያበረከቱ ነው።—ራእይ 14:6, 7

● የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ምን የሕትመት ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል? ለምንስ?

● ይህን ሁሉ ሥራ የሚሠሩት እነማን ናቸው? እንዴትስ ይኖራሉ?

[በገጽ 24 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በብሩክሊንና ዎልኪል ኒው ዮርክ ዩ ኤስ ኤ ፈቃደኛ ሠራተኞች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ከማምረት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በፋብሪካ፣ በመኖሪያ ቤት፣ በቢሮና በእርሻ ሲያከናውኑ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ፈቃደኛ ሠራተኞች መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከማምረት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተያያዙ የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውኑ

ስፔን

ጀርመን

ፊንላንድ

ካናዳ

ዴንማርክ

ስዊድን

ደቡብ አፍሪካ

ብራዚል

ኔዘርላንድስ

አውስትራሊያ