በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በስብከቱ ሥራ በግንባር ቀደምትነት ይሰለፋሉ

የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በስብከቱ ሥራ በግንባር ቀደምትነት ይሰለፋሉ

የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በስብከቱ ሥራ በግንባር ቀደምትነት ይሰለፋሉ

ለመጀመሪያ ጊዜ ያነጋገረህ የይሖዋ ምሥክር የሙሉ ጊዜ አቅኚ የሆነ አገልጋይ ወይም ሚስዮናዊ ሊሆን ይችላል። የይሖዋ ምሥክሮች ለሚሰጡት አገልግሎት ገንዘብ እንደማይከፈላቸው ስታውቅ ታዲያ እነዚህ ሰዎች እንዴት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሊሰማሩ ይችላሉ? የሚል ጥያቄ ይመጣብህ ይሆናል።

ራሳቸውን የወሰኑና የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ የወንጌል አገልጋዮች ናቸው። ቢሆንም ብዙዎቹ የቤተሰብ ወይም ሌላ ዓይነት ኃላፊነት ስላለባቸው በየሳምንቱ ከጥቂት ሰዓቶች በላይ በአገልግሎት ሊያሳልፉ አይችሉም። ይሁን እንጂ በዓለም ዙሪያ በሺህ የሚቆጠሩ ምሥክሮች ለአገልግሎቱ በዓመት 1,000 ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ለማሳለፍ እንዲችሉ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ወጪ ለመሸፈን የትርፍ ሰዓት ሥራ ብቻ ይሠራሉ። የኑሮ ደረጃቸውንም ዝቅ ለማድረግ ፈቃደኞች ሆነዋል።

እውነት ነው፤ የሙሉ ጊዜ አቅኚ አገልጋዮች እንደልባቸው የሚያወጡት ገንዘብ የላቸውም። ቢሆንም የአምላክን መንግሥት የሚያስቀድሙት ዝቅተኛ ኑሮ በመኖር እንደሆነ ስለሚያውቁ ቅር አይላቸውም። ብዙ በረከትም ያገኛሉ። በየወሩ ለ90 ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ የአምላክን ቃል ለሌሎች መናገር መቻል ራሱ አንድ አስደሳች ተሞክሮ ነው። የሙሉ ጊዜ አገልጋዩ በአገልግሎት ያለውን ችሎታ ለማሻሻልና ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በሚገባ ለመከታተል ይችላል። ይህም በጣም የሚያበረታታ ውጤት ያስገኝለታል። የሚያስፈልጓቸውን ሥጋዊ ነገሮች ያገኛሉ። ያላቸውንም ነገር በአድናቆት ይመለከቱታል።—ማቴዎስ 6:33

የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በየካቲት ወር 1943 የጊልያድን የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት አቋቋመ። የትምህርት ቤቱ ዓላማ በውጭ አገር በሚስዮናዊነት የሚያገለግሉ ልምድ ያላቸው የሙሉ ጊዜ አቅኚ አገልጋዮችን ማሠልጠን ነው። ይህ የአምስት ወር የሥልጠና ፕሮግራም በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፣ በይሖዋ ድርጅትና በውጭ አገር መስክ ለማገልገል በሚያዘጋጁ ትምህርቶች ላይ የተመሠረቱ ጥልቅ ጥናቶችን ያጠቃ ልላል።

ማኅበሩ ሚስዮናውያኑ ወደተመደቡበት ቦታ የሚያደርሳቸውን የመጓጓዣ ወጪ ይከፍላል። በተመደቡባቸውም ቦታዎች ለጤና ተስማሚ የሆኑ ምግቦችና የመኖሪያ ቦታ ያቀርብላቸዋል። በተጨማሪም ለእያንዳንዱ ሚስዮናዊ ለወጪ መተኪያ የሚሆን መጠነኛ ገንዘብ ይሰጣል። ሚስዮናውያኑ በየተራ ገበያ በመሄድ፣ ምግብ በማዘጋጀትና ቤት በማጽዳት የሚስዮናዊ ቤቱን ያካሂዳሉ። ይህን የመሰለ መጠነኛ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ከቤት ወደ ቤት በመስበክና ፍላጎት ላላቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራቱ ሥራ በወር ቢያንስ 140 ሰዓት ለማሳለፍ ይችላሉ።

ከእነዚህ ሚስዮናውያን ብዙዎቹ የሚመደቡት ከአገራቸውና ከቤተሰቦቻቸው በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀው ነው። ይኖሩበት ከነበረው የተለየ የኑሮ ደረጃና ባህል፣ አዲስ የአመጋገብ ልማድ፣ የተለየ የአየር ሁኔታና አዲስ ቋንቋ መልመድ ያስፈልጋቸዋል። ይህን ሁሉ ነገር የሚያደርጉት ሰዎችን ስለሚወዱና ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት እንዲማሩ ጠንካራ ፍላጎት ስላላቸው ነው።

ከ1943 እስከ 1991 የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ከ92 በላይ ኮርሶችን ሰጥቶ ከ6,500 የሚበልጡ ሚስዮናውያንን አስመርቆ ልኳል። እነዚህ ሚስዮናውያን በማኅበሩ አመራር ስር ሆነው በአፍሪካ፣ በማዕከላዊና ደቡብ አሜሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በደቡብ ፓስፊክ በግንባር ቀደምትነት በማገልገል ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በአውሮፓም ብዙ ሥራ አከናውነዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች በአገልግሎቱ የተሠማሩት በሙሉ ጊዜ አቅኚነት ወይም በሚሲዮናዊነት ይሁን ወይም በትርፍ ሰዓት፣ ከአገልግሎታቸው ምንም ዓይነት የገንዘብ ትርፍ አያገኙም። ሌሎች ሰዎች ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውቀት እንዲያገኙ ለመርዳት ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውንና ራሳቸውንም ሳይቀር መሥዋዕት ያደርጋሉ።—ዮሐንስ 17:3

● አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ሙሉ ጊዜያቸውን ለአገልግሎት ለማዋል የቻሉት እንዴት ነው? ይህን የሚያደርጉትስ ለምንድን ነው?

● አገልጋዮች ለሚስዮናዊነት ሥራ የሚሠለጥኑት እንዴት ነው?

● ሚስዮናውያን በውጭ አገር የሥራ ምድባቸው በሚያገለግሉበት ጊዜ ለመተዳደሪያቸው ድጋፍ የሚያገኙት እንዴት ነው?

[በገጽ 22 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በስተግራ:- የጊልያድ ትምህርት ቤት ክፍል፤ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩ ኤስ ኤ

በስተቀኝ:- አንድ ሚስዮናዊ በፓፑዋ ኒው ጊኒ የአምላክን ቃል ሲያስተምር

[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አቅኚ አገልጋዮችና ሚስዮናውያን በተለያዩ አገሮች የአምላክን ቃል ሲሰብኩ

ብራዚል

ዶሚኒካን ሪፑብሊክ

ስፔይን

ሴራልዮን፣ አፍሪካ