በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ ዓላማ ዛሬ ወደ ከፍተኛ ደረጃው ደርሷል

የአምላክ ዓላማ ዛሬ ወደ ከፍተኛ ደረጃው ደርሷል

የአምላክ ዓላማ ዛሬ ወደ ከፍተኛ ደረጃው ደርሷል

አምላክ ምድርን የፈጠረበት ዓላማ ጽድቅ በሰፈነበት አካባቢ በሚኖሩ ደስተኛ ሰዎች እንድትሞላ ነበር። የሰው ልጅ በሕይወት እንዲቀጥል የአምላክን ሕጎች መታዘዝ ነበረበት። የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ግን የአምላክን ትዕዛዝ ጥሰው ኃጢአተኞች ሆኑ። በዚህም ምክንያት በራሳቸው ላይ የሞት ኩነኔ አመጡ። ይህም በዘሮቻቸው ሁሉ ላይ ኃጢአትና ሞት አስከተለ።—ዘፍጥረት 1:27, 28፤ 2:16, 17፤ 3:1–19፤ ሮሜ 5:12

ስሙ ይሖዋ የሆነው አምላክ አለመታዘዝና ኃጢአት ያስከተሏቸውን ውጤቶች ከምድር ላይ ለማስወገድ ወሰነ። አያሌ ጊዜያት ካለፉ በኋላ ምድርን ሲመለከት ከሰው ልጆች መሃል አብራም የተባለ ሊታመን የሚችል ሰው አገኘ። ስሙንም ለወጠለትና አብርሃም ብሎ ጠራው። የአብርሃም ዘር ታላቅ ሕዝብ እንደሚሆንና በዚህም ሕዝብ በኩል የምድር ነገዶች በሙሉ ራሳቸውን የሚባርኩበት ዘር እንደሚመጣ አምላክ ቃል ገባለት።—ዘፍጥረት 12:1–3፤ 18:18, 19፤ 22:18፤ መዝሙር 83:18፤ ዕብራውያን 11:8–16

ከዘአበ ወደ 16ኛው መቶ ዘመን ማለቂያ አካባቢ የአብርሃም የልጅ ልጅ የነበረው የያዕቆብ ወይም የእሥራኤል ዘሮች በግብጽ ምድር በባርነት የሚኖሩ 12 ነገዶች ሆኑ። ይሖዋ እነዚህን እሥራኤላውያን ከግብጽ ነፃ አውጥቶ አንድ ብሔር አደረጋቸው። በሙሴ በኩልም በሲና ተራራ ላይ ብሔራዊ ሕገ መንግሥት የሚሆናቸውን ሕግ ሰጣቸው። ይሖዋ ንጉሣቸው፣ ፈራጃቸውና ሕግ ሰጪያቸው ነበር። የእሥራኤል ብሔር የአምላክ ምርጥ ሕዝብ፣ ምሥክርና ዓላማውን ለመፈጸም የተደራጀ ሆነ። በዚህ ሕዝብ በኩል ለአሕዛብ ሁሉ ታላላቅ ጥቅሞችን የሚያስገኘውን ዘላለማዊ መንግሥት የሚያቋቁመው መሲሕ መምጣት ነበረበት።—ዘጸአት 19:5, 6፤ 1 ዜና መዋዕል 17:7–14፤ 1 ነገሥት 4:20, 25፤ ኢሳይያስ 33:22፤ 43:10–12፤ ሮሜ 9:4, 5

ከ15 መቶ ዓመታት በኋላ ወይም የዛሬ 2,000 ዓመታት ገደማ አምላክ አንድያ ልጁን ከሰማይ ወደ ምድር ልኮ ወጣት አይሁዳዊት ድንግል ከነበረችው ከማርያም እንዲወለድ አደረገ። ሕጻኑ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ። እርሱም አምላክ ለቅድመ አያቱ ለዳዊት ቃል የገባለትን መንግሥት እንዲወርስ የአምላክ ዓላማ ነበር። ኢየሱስ 30 ዓመት ሲሞላው በአጥማቂው በዮሐንስ እጅ ተጠመቀና የአምላክን መንግሥት ማስታወቅ ጀመረ። ሕሙማንን በመፈወስ ያች የምትመጣው መንግሥት የሰው ልጆችን እንዴት እንደምትባርክ በተግባር አሳየ። ልዩ ልዩ ምሳሌዎችን በመናገር የዘላለም ሕይወት የሚፈልጉ ሁሉ ምን ማድረግ እንደሚፈለግባቸው አስረዳ። ከዚያም በኋላ ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ተገደለ። ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱም ለሰው ልጆች ቤዛ ሆነ።—ማቴዎስ 1:18–24፤ 3:13–16፤ 4:17–23፤ 6:9, 10፤ ምዕራፍ 13 በሙሉ፤ 20:28ሉቃስ 1:26–37፤ 2:14፤ 4:43, 44፤ 8:1፤ ዮሐንስ 3:16፤ ሥራ 10:37–39

መሲሐዊቷ መንግሥት የምትቋቋመው ገና ወደፊት ከብዙ ጊዜ በኋላ ማለትም በሥርዓቱ መደምደሚያ ጊዜ እንደሚሆን ኢየሱስ ገልጾ ነበር። ያ ጊዜ ሲደርስ በሰማይ በማይታይ ሁኔታ ተገኝቶ እንደሚነግስና ትኩረቱን ወደ ምድር በማዞር መገኘቱን እንደሚያሳውቅ ተናግሮ ነበር። ከ1914 ጀምሮ በዚህ እርሱ በተናገረለት ዘመን ውስጥ እንደምንኖር የዓለም ሁኔታዎች ያሳያሉ። ኢየሱስ በትንቢት እንደተናገረው የመንግሥቱ ምሥራች ለሁሉም ሕዝቦች ምሥክር እንዲሆን በዓለም በሙሉ በመሰበክ ላይ ነው። በዚህም ስብከት አማካኝነት ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ከአምላክ መንግሥት ጎን እየተሰበሰቡ ነው። እነዚህም ሰዎች በዚህ ሥርዓት ላይ ከሚመጣው ጥፋት ተርፈው በመሲሐዊት መንግሥት በምትተዳደረው ምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።—ማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25፤ ራእይ 7:9–17

በዛሬው ጊዜ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት የአምላክን ፈቃድ እናደርጋለን ይላሉ። ታዲያ እርስዎ እውነተኛዋን የክርስቲያን ጉባኤ ለይተው ለማወቅ የሚችሉት እንዴት ነው? ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ መጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ የሚናገሩትን በመመርመርና በዛሬው ጊዜ የዚህን የጥንት ጉባኤ ሥርዓት የሚከተለው ማን እንደሆነ በመመርመር ነው።

● አብርሃምና እስራኤል በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ ምን ድርሻ ነበራቸው?

● ኢየሱስ በአገልግሎቱና በሞቱ ምን ያከናወነው ነገር አለ?

● ዘመናችንን ልዩ የሚያደርጉ ምን ሁኔታዎች እንደሚከሰቱ አስቀድሞ ተነግሮ ነበር?