ምክርን ስማ፤ ተግሣጽን ተቀበል
ምዕራፍ አሥራ አምስት
ምክርን ስማ፤ ተግሣጽን ተቀበል
1. (ሀ) ሁላችንም ምክርና ተግሣጽ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? (ለ) ልንመረምረው የሚገባን ጥያቄ የትኛው ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ያዕቆብ 3:2 ላይ “ሁላችንም በብዙ ነገር እንሰናከላለን” ይላል። የአምላክ ቃል እንድንሆን የሚያበረታታን ዓይነት ሰዎች ሳንሆን የቀረንባቸውን በርካታ ጊዜያት ልናስታውስ እንችላለን። በመሆኑም “ምክርን ስማ፤ ተግሣጽን ተቀበል፤ በመጨረሻም ጠቢብ ትሆናለህ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ትክክል መሆኑን አምነን እንቀበላለን። (ምሳሌ 19:20) አኗኗራችንን ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር ለማስማማት አስፈላጊ የሆኑ ማስተካከያዎችን እንዳደረግን ጥርጥር የለውም። ሆኖም አንድ ክርስቲያን አንድን ጉዳይ በተመለከተ ምክር ቢለግሰን ምን ምላሽ እንሰጣለን?
2. በግል ምክር ሲሰጠን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
2 አንዳንዶች ምክር ሲሰጣቸው ምክንያት ሊደረድሩ፣ ድርጊቱን ለማቃለል ሊሞክሩ ወይም በሌሎች ሊያሳብቡ ይችላሉ። ሆኖም ምክርን ሰምቶ ሥራ ላይ ማዋል የተሻለ ነው። (ዕብራውያን 12:11) እርግጥ ነው፣ ማንም ሰው ከሌሎች ፍጽምና መጠበቅም ሆነ በረባ ባልረባው ወይም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ለግል ምርጫ በተዋቸው ጉዳዮች ላይ ዘወትር ምክር መስጠት አይኖርበትም። ከዚህም በተጨማሪ ምክሩን የሚሰጠው ሰው ስለ ጉዳዩ በቂ ግንዛቤ ላይኖረው ስለሚችል በአክብሮት ጉዳዩን ማስረዳት ሊያስፈልግ ይችላል። ይሁንና የተሰጠን ምክር ወይም ተግሣጽ ተገቢና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነው እንበል። በዚህ ጊዜ ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል?
ልናስታውሳቸው የሚገቡ ምሳሌዎች
3, 4. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ለምክርና ለተግሣጽ ትክክለኛ አመለካከት እንድናዳብር ሊረዳን የሚችል ምን ነገር ይዟል? (ለ) ንጉሥ ሳኦል ምክር ሲሰጠው ምን ምላሽ ሰጠ? ውጤቱስ ምን ሆነ?
3 የአምላክ ቃል ተገቢ ምክር ስለተሰጣቸው ሰዎች የሚገልጹ ታሪኮችን ይዟል። ለአንዳንዶቹ የተሰጠው ምክር ተግሣጽም ያዘለ ነበር። እንዲህ ያለ ምክር ከተሰጣቸው ሰዎች መካከል የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳኦል ይገኝበታል። ሳኦል፣ ይሖዋ አማሌቃውያንን በተመለከተ የሰጠውን መመሪያ ሳይታዘዝ ቀርቷል። አማሌቃውያን የአምላክን አገልጋዮች ይቃወሙ ስለነበር ይሖዋ አማሌቃውያንም ሆኑ እንስሶቻቸው በሙሉ እንዲደመሰሱ አዝዞ ነበር። ይሁን እንጂ ንጉሥ ሳኦል የአማሌቃውያን ንጉሥና ምርጥ እንስሶቻቸው እንዲተርፉ አደረገ።—1 ሳሙኤል 15:1-11
4 ይሖዋ ሳኦልን እንዲገሥጸው ነቢዩ ሳሙኤልን ላከው። ሳኦል ምን ምላሽ ሰጠ? አማሌቃውያንን በሙሉ እንደደመሰሰና ንጉሣቸው ብቻ በሕይወት እንዲተርፍ እንዳደረገ በመግለጽ ምንም ስህተት እንዳልሠራ ለማሳመን ሞከረ። ይሁንና ይህ ይሖዋ ከሰጠው መመሪያ ጋር የሚጋጭ ድርጊት ነበር። (1 ሳሙኤል 15:20) ሳኦል እንስሶቹ ያልጠፉበትን ምክንያት ሲገልጽ “ሕዝቡን ፈርቼ ስለ ነበር፣ የጠየቁኝን ታዝዣለሁ” በማለት ጥፋቱን በሕዝቡ ላይ ለማላከክ ሞክሯል። (1 ሳሙኤል 15:24) ይበልጥ ያሳሰበው የራሱ ክብር ስለነበር ሳሙኤል በሕዝቡ ፊት እንዲያከብረው እስከመጠየቅ ደርሷል። (1 ሳሙኤል 15:30) ውሎ አድሮ የሳኦል ንጉሣዊ ሥልጣን በይሖዋ ፊት ተቀባይነት አጣ።—1 ሳሙኤል 16:1
5. ንጉሥ ዖዝያን የተሰጠውን ምክር ባለመቀበሉ ምን ደረሰበት?
5 የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያን “ዕጣን ለማጠን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመግባቱ እግዚአብሔርን በደለ።” (2 ዜና መዋዕል 26:16) ይሁንና ዕጣን ማጠን የሚፈቀድላቸው ካህናት ብቻ ነበሩ። ሊቀ ካህናቱ ዖዝያንን ሊከለክለው ሲሞክር ንጉሡ ተቆጣ። በዚህ ጊዜ ምን ተከሰተ? መጽሐፍ ቅዱስ “በግንባሩ ላይ ለምጽ ወጣበት . . . እግዚአብሔር አስጨንቆታልና። ንጉሡ ዖዝያን እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ለምጻም ነበረ” ይላል።—2 ዜና መዋዕል 26:19-21
6. (ሀ) ሳኦልም ሆነ ዖዝያን ምክር ለመቀበል የተቸገሩት ለምንድን ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ ምክር አለመቀበል ከባድ ችግር የሆነው ለምንድን ነው?
6 ሳኦልም ሆነ ዖዝያን የተሰጣቸውን ምክር መቀበል አስቸጋሪ የሆነባቸው ለምንድን ነው? የሁለቱም ዋነኛ ችግር ኩራት ነበር፤ ራሳቸውን ከልክ በላይ ከፍ አድርገው ተመልክተዋል። ብዙዎች በዚህ ባሕርይ የተነሳ በራሳቸው ላይ መከራ ያመጣሉ። ምክር መቀበል የሆነ ጉድለት እንዳለባቸው የሚያሳይ ወይም ክብራቸውን የሚነካ ነገር እንደሆነ አድርገው የተመለከቱት ይመስላል። ሆኖም ኩራት ራሱ የድክመት ምልክት ነው። የአንድን ሰው አስተሳሰብ ስለሚያጨልም ይሖዋ በቃሉም ሆነ በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠውን እርዳታ ለመቀበል አሻፈረኝ እንዲል ያደርገዋል። በመሆኑም ይሖዋ “ትዕቢት ጥፋትን፣ የእብሪት መንፈስም ውድቀትን ትቀድማለች” ሲል ያስጠነቅቃል።—ምሳሌ 16:18፤ ሮሜ 12:3
ምክር መቀበል
7. ሙሴ ምክር ሲሰጠው ከወሰደው እርምጃ ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን?
7 ቅዱሳን ጽሑፎች ምክር በመቀበል ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን ታሪክ የያዙ ሲሆን እኛም ከእነዚህ ሰዎች መማር እንችላለን። የነበረበትን የሥራ ጫና መወጣት የሚችልበትን መንገድ በተመለከተ ከአማቱ ምክር ያገኘውን ሙሴን እንመልከት። ሙሴ የተሰጠውን ምክር በመስማት ወዲያውኑ ሥራ ላይ አውሏል። (ዘፀአት 18:13-24) ሙሴ ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው ቢሆንም የተሰጠውን ምክር የተቀበለው ለምንድን ነው? ትሑት ስለነበረ ነው። “ሙሴ በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበር።” (ዘኍልቍ 12:3) ትሕትና ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ሶፎንያስ 2:3 ይህ ባሕርይ ሕይወት ሊያስገኝልን እንደሚችል ይገልጻል።
8. (ሀ) ዳዊት የፈጸማቸው ኃጢአቶች ምንድን ናቸው? (ለ) ዳዊት፣ ናታን በገሠጸው ጊዜ ምን ምላሽ ሰጠ? (ሐ) ዳዊት የሠራቸው ኃጢአቶች ምን መዘዝ አስከትለውበታል?
2 ሳሙኤል 12:13) ምንም እንኳ አምላክ የዳዊትን ንስሐ የተቀበለ ቢሆንም ዳዊት፣ የሠራቸው ኃጢአቶች ካስከተሉበት መዘዝ ሊያመልጥ አልቻለም። ይሖዋ ‘ሰይፍ ከቤቱ እንደማይርቅ፣’ ‘ሚስቶቹ ለእሱ ቅርብ ለሆነ ሰው እንደሚሰጡ’ እና በምንዝር የወለደው ልጅ ‘እንደሚሞት’ ነግሮታል።—2 ሳሙኤል 12:10, 11, 14
8 ንጉሥ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር ከመፈጸሙም በላይ ባሏ ኦርዮን እንዲገደል በማድረግ የፈጸመውን ድርጊት ለመሸፋፈን ሞክሯል። ይሖዋ ዳዊትን እንዲገሥጸው ነቢዩ ናታንን ላከው። ዳዊት ንስሐ የገባ ሲሆን “እግዚአብሔርን በጣም በድያለሁ” በማለት ምንም ሳያንገራግር ጥፋቱን አምኗል። (9. ምክር ወይም ተግሣጽ ሲሰጠን ምን መዘንጋት አይኖርብንም?
9 ንጉሥ ዳዊት ትክክለኛ ምክርን መቀበል ያለውን ጥቅም ያውቅ ነበር። በአንድ ወቅት በአንዲት ሴት አማካኝነት ላገኘው ምክር አምላክን አመስግኗል። (1 ሳሙኤል 25:32-35) እኛም እንዲህ ዓይነት ሰዎች ከሆንን የኋላ ኋላ ሊጸጽተን የሚችል ነገር ከመናገርም ሆነ ከማድረግ እንቆጠባለን። ሆኖም ምክር ብሎም ተግሣጽ የሚያሰጥ ድርጊት ብንፈጽምስ? በዚህ ጊዜ የሚሰጠን ምክርም ሆነ ተግሣጽ ይሖዋ ለእኛ ዘላለማዊ ደኅንነት እንደሚያስብና እንደሚወደን የሚያሳይ ማስረጃ መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም።—ምሳሌ 3:11, 12፤ 4:13
ልናዳብራቸው የሚገቡ ውድ ባሕርያት
10. ኢየሱስ ወደ መንግሥቱ የሚገቡ ሁሉ የትኛውን ባሕርይ ማዳበር እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁሟል?
10 ከይሖዋም ሆነ ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ከፈለግን ልናዳብራቸው የሚገቡ አንዳንድ ባሕርያት አሉ። ኢየሱስ አንድን ሕፃን በደቀ መዛሙርቱ መካከል አቁሞ የሚከተለውን በተናገረበት ጊዜ ከእነዚህ ባሕርያት አንዱን ጠቁሟል:- ማቴዎስ 18:3, 4) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሆነ ይከራከሩ ስለነበር ትሕትናን ማዳበር አስፈልጓቸው ነበር።—ሉቃስ 22:24-27
“ካልተለወጣችሁ እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ፈጽሞ ወደ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም። ስለዚህ በመንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የሚበልጥ እንደዚህ ሕፃን ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ነው።” (11. (ሀ) በማን ፊት ትሑት መሆን አለብን? ለምንስ? (ለ) ትሑቶች ከሆንን ምክር ሲሰጠን ምን እናደርጋለን?
11 ሐዋርያው ጴጥሮስ “ሁላችሁም እርስ በርስ በመከባበር ትሕትናን ልበሱ፤ ምክንያቱም፣ ‘እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል’” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 5:5) በአምላክ ፊት ትሑቶች መሆን እንደሚያስፈልገን እናውቃለን፤ ሆኖም ይህ ጥቅስ እንደሚያሳየው በእምነት ባልንጀሮቻችን ዘንድም ትሑት መሆን ያስፈልገናል። ትሑቶች ከሆንን ከሌሎች ለመማር ጥረት እናደርጋለን እንጂ የሚሰጡንን ትክክለኛ አስተያየት ለመቀበል አንቸገርም።—ምሳሌ 12:15
12. (ሀ) ከትሕትና ጋር የቅርብ ዝምድና ያለው አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ ምንድን ነው? (ለ) ምግባራችን በሌሎች ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ ማሰብ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
12 ከትሕትና ጋር የቅርብ ዝምድና ያለው ሌላው ባሕርይ ለሌሎች ደኅንነት ማሰብ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ የራሱን ብቻ አይፈልግ። . . . እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። ለአይሁድም ሆነ ለግሪኮች ወይም ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን መሰናክል አትሁኑ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 10:24-33) እዚህ ላይ ጳውሎስ የግል ምርጫዎቻችንን ሁሉ እርግፍ አድርገን መተው አለብን ማለቱ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ አንድ ሰው ሕሊናው ትክክል እንዳልሆነ የሚነግረውን ነገር እንዲፈጽም ሊያደፋፍረው የሚችል ነገር ከማድረግ እንድንቆጠብ ማሳሰቡ ነበር።
13. የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ሥራ ላይ የማዋል ልማድ ማዳበር አለማዳበራችንን ሊያሳይ የሚችለው የትኛው ምሳሌ ነው?
13 የሌሎች ሰዎችን ደኅንነት ከግል ምርጫህ ታስቀድማለህ? ሁላችንም ይህን የማድረግ ልማድ ማዳበር አለብን። ይህን ልናደርግ የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። አለባበስንና አጋጌጥን እንደ ምሳሌ ልንወስድ እንችላለን። ይህ ጉዳይ ልከኛ፣ ንጹሕና ሥርዓታማ እንድንሆን የተሰጡንን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች ሳንጥስ የራሳችንን የግል ምርጫ ማድረግን የሚመለከት ነው። አለባበስህም ሆነ አጋጌጥህ በምትኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ የተለየ አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት እንዳይቀበሉ እንቅፋት እየፈጠረባቸው እንዳለ ብትገነዘብ ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኛ ነህ? የራስን ደስታ ከማስቀደም ይልቅ ሌላ ሰው የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ መርዳት የተሻለ እንደሆነ ግልጽ ነው።
14. ትሕትናንም ሆነ ለሌሎች አሳቢ የመሆንን ባሕርይ ማዳበር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
14 ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር እንኳ ሳይቀር በማጠብ በትሕትናም ሆነ ለሌሎች አሳቢነት በማሳየት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቷል። (ዮሐንስ 13:12-15) የአምላክ ቃል ኢየሱስን አስመልክቶ ሲናገር እንደሚከተለው ይላል:- “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ፣ በእናንተም ዘንድ ይሁን፤ እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣ በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ ራሱን ባዶ አደረገ፤ ሰው ሆኖ ተገልጦም፣ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት . . . ድረስ ታዛዥ ሆነ።”—ፊልጵስዩስ 2:5-8፤ ሮሜ 15:2, 3
የይሖዋን ተግሣጽ ለመቀበል እምቢ አትበል
15. (ሀ) አምላክን የሚያስደስት ባሕርይ እንዲኖረን ምን ለውጥ ማድረግ ያስፈልገናል? (ለ) ይሖዋ ለሁላችንም ምክርና ተግሣጽ የሚሰጠው በምን አማካኝነት ነው?
15 ሁላችንም ኃጢአተኞች በመሆናችን የአምላካችንን ባሕርያት ማንጸባረቅ ከፈለግን በአመለካከታችንም ሆነ በምግባራችን ረገድ ለውጥ ማድረግ ያስፈልገናል። “አዲሱን ሰው” መልበስ ይኖርብናል። ቈላስይስ 3:5-14) የሚሰጠን ምክር ወይም ተግሣጽ ደግሞ በምን ረገድ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልገንና ይህን ማስተካከያ እንዴት ማድረግ እንደምንችል እንድናስተውል ይረዳናል። ለእኛ የሚያስፈልገንን ትምህርት የምናገኝበት ዋነኛው ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) የይሖዋ ድርጅት የሚያዘጋጃቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችና ስብሰባዎች የአምላክን ቃል ተግባራዊ ማድረግ እንድንችል ይረዱናል። ምክሩን ቀደም ሲል የሰማነው ቢሆንም እንኳ ምክሩ እንደሚያስፈልገን ተሰምቶን ማሻሻያ ለማድረግ እንጥራለን?
(16. ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ምን እርዳታ ያደርግልናል?
16 ይሖዋ ስለሚወደንና ስለሚያስብልን አስፈላጊውን እርዳታ ያደርግልናል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት ጥሩ እርዳታ አግኝተዋል። ወላጆች ልጆቻቸው መጥፎ ሥነ ምግባር ተከትለው ለችግር እንዳይዳረጉ ምክርና ተግሣጽ ይሰጧቸዋል። (ምሳሌ 6:20-23) በጉባኤ ውስጥ ብዙውን ጊዜ አንዳንዶች በመስክ አገልግሎት የሚያደርጉትን ተሳትፎ ለማሻሻል ሲሉ ተሞክሮ ያላቸውን አገልጋዮች ምክርና ሐሳብ ይጠይቃሉ። አንዳንድ ጊዜ ሽማግሌዎች ከሌሎች ሽማግሌዎችም ሆነ በአገልግሎት ተሞክሮ ካላቸው ሌሎች ወንድሞች ምክር ሊጠይቁ ይችላሉ። መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ወንድሞች መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በገርነት መንፈስ ተገቢውን እርዳታ ይለግሳሉ። ምክር የምትሰጥ ከሆነ ‘አንተም እንዳትፈተን ራስህን መጠበቅ’ እንደሚያስፈልግህ አትዘንጋ። (ገላትያ 6:1, 2) አዎን፣ እውነተኛውን አንድ አምላክ አንድ ሆነን ለማምለክ ሁላችንም ምክርና ተግሣጽ ያስፈልገናል።
የክለሳ ውይይት
• ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ምን ማስተካከያዎች ማድረግ እንደሚያስፈልገን እንድንገነዘብ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ የሚረዳን እንዴት ነው?
• ብዙዎች አስፈላጊ ምክር ሲሰጣቸው ለመቀበል የሚቸገሩት ለምንድን ነው? ይህስ ምን ያህል አደገኛ ነው?
• የሚሰጠንን ምክር እንድንቀበል ሊረዱን የሚችሉት ውድ ባሕርያት የትኞቹ ናቸው? በዚህ ረገድ ኢየሱስ ጥሩ ምሳሌ የተወልንስ እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 142 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዖዝያን የተሰጠውን ምክር ባለመቀበሉ በሥጋ ደዌ በሽታ ተመቷል
[በገጽ 142 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሙሴ የዮቶርን ምክር በመቀበሉ ተጠቅሟል