በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሁላችንም ፊት የተደቀነ የአቋም ጥያቄ

በሁላችንም ፊት የተደቀነ የአቋም ጥያቄ

ምዕራፍ ስድስት

በሁላችንም ፊት የተደቀነ የአቋም ጥያቄ

1, 2. (ሀ) ሰይጣን በኤደን ምን ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል? (ለ) አነጋገሩ ይህን ጥያቄ እንዳስነሳ የሚያሳየው እንዴት ነው?

አንተን ጨምሮ በመላው የሰው ዘር ፊት የተደቀነ አንድ ትልቅ የአቋም ጥያቄ አለ። የዘላለም ሕይወት ማግኘት አለማግኘትህ የተመካው ከዚህ ጥያቄ ጋር በተያያዘ በምትወስደው አቋም ላይ ነው። ይህ የአቋም ጥያቄ የተነሳው በኤደን ዓመጽ በተቀሰቀሰበት ጊዜ ነው። በዚያን ጊዜ ሰይጣን ሔዋንን “በእርግጥ እግዚአብሔር፣ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉ’ ብሎአልን?” ሲል ጠይቋት ነበር። ሔዋንም አምላክ አንድን ዛፍ በተመለከተ ‘ከዛፉ ፍሬ እንዳትበሉ፤ አለበለዚያ ትሞታላችሁ’ ሲል የተናገረውን ቃል በመጥቀስ መለሰች። ከዚያም ሰይጣን፣ አዳምም ሆነ ሔዋን አምላክን መታዘዛቸው በሕይወታቸው ላይ ምንም የሚያመጣው ለውጥ እንደሌለ በመግለጽ ይሖዋን ሐሰተኛ ነው ብሎ በቀጥታ ክስ ሰንዝሮበታል። አምላክ ፍጥረታቱን አንድ ጥሩ ነገር ማለትም የራሳቸውን መሥፈርት የማውጣት ችሎታ እንደነፈጋቸው አድርጎ ተናግሯል። ሰይጣን “ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው” ሲል ገልጿል።—ዘፍጥረት 3:1-5

2 በተዘዋዋሪ መንገድ ሰይጣን፣ ሰዎች የአምላክን ሕግጋት ከሚታዘዙ ይልቅ በራሳቸው መንገድ ቢመሩ የተሻለ እንደሚሆን መናገሩ ነበር። በዚህ መንገድ የአምላክን አገዛዝ ተገዳድሯል። ይህም በአምላክ ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ማለትም በመግዛት መብቱ ላይ ትልቅ ጥያቄ አስነስቷል። የተነሳው ጥያቄ ‘ለሰው ልጆች የሚበጀው በይሖዋ አገዛዝ ሥር ቢሆኑ ነው ወይስ ራሳቸውን በራሳቸው ቢያስተዳድሩ?’ የሚል ነው። በዚህ ጊዜ ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋንን ወዲያውኑ ሊያጠፋቸው ይችል ነበር። ሆኖም ይህ እርምጃ በሉዓላዊነቱ ላይ ለተነሳው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ አያስገኝም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ እንዲፈጠርና ለተወሰነ ጊዜ እንዲቀጥል በመፍቀድ ለእሱም ሆነ ለሕግጋቱ አለመገዛት ምን ውጤት እንደሚያስከትል በተግባር እንዲታይ ማድረግ ይችላል።

3. ሰይጣን ያስነሳው ሁለተኛ ጥያቄ ምንድን ነው?

3 ሰይጣን በይሖዋ የመግዛት መብት ላይ የሰነዘረው ጥቃት በኤደን ብቻ ተወስኖ አልቀረም። ሌሎች ለይሖዋ ባላቸው ታማኝነትም ላይ ጥያቄ አስነስቷል። ይህ ከመጀመሪያው ጥያቄ ጋር ተዛማጅነት ያለው በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ጥያቄ ነው። ሰይጣን ያስነሳው ይህ ጥያቄ የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች እንዲሁም እጅግ ተወዳጅ የሆነውን የይሖዋ የበኩር ልጅን ጨምሮ የአምላክ መንፈሳዊ ልጆችን በሙሉ የሚመለከት ነው። ለምሳሌ ያህል በኢዮብ ዘመን ሰይጣን፣ ይሖዋን የሚያገለግሉ ሁሉ ይህን የሚያደርጉት ለአምላክና ለአገዛዙ ባላቸው ፍቅር ተገፋፍተው ሳይሆን ለራሳቸው የግል ጥቅም ብለው ነው ሲል ተከራክሯል። መከራ ወይም ችግር ቢደርስባቸው የራሳቸውን ጥቅም ያስቀድማሉ በማለት ተሟግቷል።—ኢዮብ 2:1-6፤ ራእይ 12:10

ታሪክ ምን አረጋግጧል?

4, 5. የሰው ልጅ አካሄዱን በራሱ ለማቅናት ያደረገውን ሙከራ በተመለከተ ታሪክ ምን አረጋግጧል?

4 በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ ከተነሳው ጥያቄ ጋር በተያያዘ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ አንድ ነጥብ አለ:- አምላክ የሰው ልጆች ከእሱ አገዛዝ ሥር ወጥተው ራሳቸውን በተሳካ መንገድ ማስተዳደር እንዲችሉ አድርጎ አልፈጠራቸውም። ለእነሱ ጥቅም በማሰብ ሕይወታቸው በእሱ የጽድቅ ሕግጋት ላይ የተመካ እንዲሆን አድርጎ ፈጥሯቸዋል። ነቢዩ ኤርምያስ “እግዚአብሔር ሆይ፤ የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ። እግዚአብሔር ሆይ ቅጣኝ” ሲል ተናግሯል። (ኤርምያስ 10:23, 24) በመሆኑም የአምላክ ቃል “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ” ሲል አጥብቆ ያሳስባል። (ምሳሌ 3:5) አምላክ የሰው ልጆች በሕይወት መኖር ይችሉ ዘንድ እሱ ላወጣቸው የተፈጥሮ ሕግጋት እንዲገዙ አድርጎ እንደፈጠራቸው ሁሉ ስምምነትና አንድነት ያለው ኅብረተሰብ እንዲገኝ የሚያስችሉ የሥነ ምግባር ሕግጋትም ሰጥቷቸዋል።

5 አምላክ ሰብዓዊው ኅብረተሰብ ከእርሱ አገዛዝ ውጭ ሆኖ ራሱን በተሳካ ሁኔታ ማስተዳደር እንደማይችል ያውቅ ነበር። ሰዎች ከአምላክ አገዛዝ ነፃ ወጥተው ለመኖር ባደረጉት ከንቱ ሙከራ የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን አቋቁመዋል። በእነዚህ ሁኔታዎች ረገድ ያሉት ልዩነቶች በሰዎች መካከል የማያቋርጥ ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል፤ ይህም ዓመጽ፣ ጦርነትና ሞት አስከትሏል። “ሰው ሰውን መግዛቱ ጉዳት አስከትሎበታል።” (መክብብ 8:9 NW) በሰው ዘር የታሪክ ዘመናት ሁሉ የታየው ይኸው ነው። የአምላክ ቃል አስቀድሞ እንደተናገረው ክፉ ሰዎችና አታላዮች ‘በክፋት ላይ ክፋትን እየጨመሩ መሄዳቸውን’ ቀጥለዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:13) በተጨማሪም በ20ኛው መቶ ዘመን የሰው ዘር በሳይንስና በኢንዱስትሪ ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ የደረሰ ቢሆንም ቀደም ባሉት ዘመናት ታይተው የማያውቁ ችግሮችንና መከራዎችንም አስተናግዷል። ሰዎች አካሄዳቸውን በራሳቸው ማቅናት እንደማይችሉ የሚገልጹት በኤርምያስ 10:23 ላይ የሰፈሩት ቃላት እውነት መሆናቸው በማያሻማ ሁኔታ ተረጋግጧል።

6. አምላክ፣ የሰው ልጅ ከእሱ አገዛዝ ማፈንገጡ ያስከተላቸውን ችግሮች በቅርቡ የሚያስወግደው እንዴት ነው?

6 የሰው ልጅ ከአምላክ አገዛዝ ማፈንገጡ ሥር የሰደዱ አሳዛኝ ችግሮችን ያስከተለበት ሲሆን ይህም ሰብዓዊ አገዛዝ መቼም ቢሆን ሊሳካለት እንደማይችል በማያዳግም ሁኔታ አረጋግጧል። ደስታ፣ አንድነት፣ ጤንነትና ሕይወት የሚያስገኘው የአምላክ አገዛዝ ብቻ ነው። ይሖዋ ከእርሱ ያፈነገጠውን ሰብዓዊ አገዛዝ የታገሰበት ዘመን ሊያበቃ የተቃረበ መሆኑን የአምላክ ቃል ይናገራል። (ማቴዎስ 24:3-14፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በቅርቡ ሰብዓዊ አገዛዝን በማስወገድ ምድርን የመግዛት ሥልጣን እንዳለው ያረጋግጣል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “በነዚያ ነገሥታት [በአሁኑ ጊዜ ባሉት ሰብዓዊ አገዛዞች] ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት [በሰማይ] ይመሠርታል [ሰዎች ዳግመኛ ምድርን አይገዙም]፤ እነዚያን [በአሁኑ ጊዜ ያሉትን] መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—ዳንኤል 2:44

ከጥፋት ተርፎ አምላክ ወደሚያመጣው አዲስ ዓለም መግባት

7. የአምላክ አገዛዝ የሰውን አገዛዝ በሚያስወግድበት ጊዜ ከጥፋት የሚተርፉት እነማን ናቸው?

7 የአምላክ አገዛዝ የሰውን አገዛዝ በሚያስወግድበት ጊዜ ከጥፋት የሚተርፉት እነማን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጣል:- “ቅኖች [የአምላክን የመግዛት መብት የሚደግፉ] በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ። ክፉዎች [የአምላክን የመግዛት መብት የማይደግፉ] ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ።” (ምሳሌ 2:21, 22) በተመሳሳይም መዝሙራዊው “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ . . . ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” ሲል ገልጿል።—መዝሙር 37:10, 29

8. አምላክ ሉዓላዊነቱን ሙሉ በሙሉ የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?

8 የሰይጣን ሥርዓት ከጠፋ በኋላ አምላክ እንደ ዓመጽ፣ ጦርነት፣ ድህነት፣ መከራ፣ በሽታና ሞት ያሉትን የሰውን ልጅ ለብዙ ሺህ ዓመታት ሲያሠቃዩ የኖሩ ችግሮች አስወግዶ በምትኩ አዲስ ዓለም ያመጣል። መጽሐፍ ቅዱስ ታዛዥ የሰው ዘሮች የሚያገኟቸውን በረከቶች እንደሚከተለው በማለት ጥሩ አድርጎ ይገልጻል:- “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።” (ራእይ 21:3, 4) አምላክ በክርስቶስ በሚመራው ሰማያዊ መንግሥቱ አማካኝነት ሉዓላዊ ጌታችን ማለትም ገዥያችን የመሆን መብት እንዳለው ሙሉ በሙሉ ያረጋግጣል።—ሮሜ 16:20፤ 2 ጴጥሮስ 3:10-13፤ ራእይ 20:1-6

ለተነሳው የአቋም ጥያቄ የሰጡት ምላሽ

9. (ሀ) ለይሖዋ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ለቃሉ ምን ዓይነት አመለካከት ነበራቸው? (ለ) ኖኅ ታማኝነቱን ያሳየው እንዴት ነው? እኛስ ከእሱ ምሳሌ ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

9 ባለፉት የታሪክ ዘመናት ሁሉ ይሖዋን እንደ ሉዓላዊ ጌታ አድርገው በመቀበል ከእርሱ ጎን በታማኝነት የቆሙ ወንዶችና ሴቶች አሉ። ሕይወታቸው እርሱን በመስማትና በመታዘዝ ላይ የተመካ እንደሆነ ያውቁ ነበር። ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ኖኅ ነው። በመሆኑም አምላክ ኖኅን “ሰውን ሁሉ ላጠፋ ነው፤ . . . አንተ ግን . . . መርከብ ሥራ” ብሎት ነበር። ኖኅም ይሖዋ የሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ አድርጓል። በዚያ ዘመን የነበሩ ሌሎች ሰዎች ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ቢሆንም ምንም አዲስ ነገር እንደማይፈጠር በማሰብ የተለመደ ኑሯቸውን ቀጥለዋል። ሆኖም ኖኅ ግዙፍ መርከብ የሠራ ከመሆኑም በላይ ስለ ይሖዋ የጽድቅ መንገዶች ያለማሰለስ ይሰብክ ነበር። ዘገባው በመቀጠል “ኖኅም ሁሉን እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ” ሲል ይገልጻል።—ዘፍጥረት 6:13-22፤ ዕብራውያን 11:7፤ 2 ጴጥሮስ 2:5

10. (ሀ) አብርሃምና ሣራ የይሖዋን ሉዓላዊነት የደገፉት እንዴት ነው? (ለ) ከአብርሃምና ከሣራ ምሳሌ ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

10 አብርሃምና ሣራም ይሖዋ ያዘዛቸውን ሁሉ በመፈጸምና ሉዓላዊነቱን በመደገፍ ረገድ ግሩም ምሳሌዎች ናቸው። በበለጸገችው በከለዳውያን ከተማ በዑር ይኖሩ ነበር። ሆኖም ይሖዋ አብርሃምን ወደማያውቀው አገር እንዲሄድ ባዘዘው ጊዜ አብርሃም “እግዚአብሔር እንዳዘዘው ወጣ።” ሣራ በዑር በተመቻቸ ቤት ከወዳጅ ዘመዶቿ ጋር የተደላደለ ኑሮ ትኖር እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም በከነዓን ምድር ምን ሁኔታዎች ሊያጋጥሟት እንደሚችሉ ምንም የምታውቀው ነገር ባይኖርም ይሖዋንና ባሏን በመታዘዝ ወደተባለችው ቦታ ሄዳለች።—ዘፍጥረት 11:31 እስከ 12:4፤ የሐዋርያት ሥራ 7:2-4

11. (ሀ) ሙሴ የይሖዋን ሉዓላዊነት የደገፈው በምን ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ ነው? (ለ) ሙሴ የተወልን ምሳሌ እኛን ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት ነው?

11 የይሖዋን ሉዓላዊነት የደገፈው ሌላው ሰው ሙሴ ነው። ይህንንም ያደረገው በጣም አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ማለትም የግብጹን ፈርዖን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ነበር። ሙሴ ይህን ማድረግ የቻለው በራሱ የሚተማመን ሰው ስለነበረ አይደለም። እንዲያውም ጥሩ የመናገር ችሎታ እንደሌለው ተሰምቶት ነበር። ቢሆንም ይሖዋን ታዝዟል። በይሖዋ እርዳታና በወንድሙ በአሮን እገዛ ልበ ደንዳና ለነበረው ፈርዖን በተደጋጋሚ ጊዜያት የይሖዋን ቃል ተናግሯል። አንዳንድ እስራኤላውያን እንኳ ሳይቀሩ ሙሴን ክፉኛ ተችተውታል። ሆኖም ሙሴ ይሖዋ ያዘዘውን ሁሉ በታማኝነት ያከናወነ ከመሆኑም በላይ በእርሱ አማካኝነት የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ነፃ ወጥቷል።—ዘፀአት 7:6፤ 12:50, 51፤ ዕብራውያን 11:24-27

12. (ሀ) ለይሖዋ ታማኝ መሆን ሲባል አምላክ በጽሑፍ እንዲሰፍር ያደረገውን ቃሉን ብቻ መታዘዝ ማለት እንዳልሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ስለዚህ ዓይነቱ ታማኝነት ያገኘነው ግንዛቤ በ1 ዮሐንስ 2:15 ላይ የሰፈረውን ሐሳብ በሥራ ላይ እንድናውል ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

12 ለይሖዋ ታማኝ የሆኑ ሰዎች መታዘዝ የሚጠበቅባቸው አምላክ በጽሑፍ ያሰፈረውን ቃል ብቻ እንደሆነ አድርገው አያስቡም። የጲጥፋራ ሚስት ዮሴፍ ከእርሷ ጋር ምንዝር እንዲፈጽም ለማባበል በሞከረችበት ጊዜ ምንዝርን የሚከለክል አምላክ ያወጣው በጽሑፍ የሰፈረ ሕግ አልነበረም። ይሁን እንጂ ዮሴፍ ይሖዋ በኤደን ያቋቋመውን የጋብቻ ሥርዓት ያውቅ ነበር። ከሌላ ሰው ሚስት ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸም አምላክን የሚያሳዝን ድርጊት እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። አምላክ እስከምን ድረስ የግብጻውያንን ልማድ እንዲከተል እንደሚፈቅድለት በተግባር ሞክሮ ለማየት አልደፈረም። አምላክ ለሰው ልጆች በተናገራቸውም ሆነ ባደረጋቸው ነገሮች ላይ በማሰላሰል ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ የተመላለሰ ከመሆኑም በላይ የአምላክ ፈቃድ ነው ብሎ ያመነበትን ነገር ሁሉ በሚገባ በሥራ ላይ አውሏል።—ዘፍጥረት 39:7-12፤ መዝሙር 77:11, 12

13. (ሀ) ከኢዮብ (ለ) ከሦስቱ ዕብራውያን ጋር በተያያዘ ዲያብሎስ ውሸታም መሆኑ የተረጋገጠው እንዴት ነው?

13 ይሖዋን በሚገባ የሚያውቁት ሰዎች ከባድ ፈተና ቢደርስባቸው እንኳ እርሱን አይተዉም። ሰይጣን፣ በይሖዋ ፊት ትልቅ ሞገስ ያገኘው ኢዮብ እንኳ ሀብቱን ወይም ጤናውን ቢያጣ አምላክን እንደሚተው ተናግሮ ነበር። ሆኖም ኢዮብ ብዙ መከራ የደረሰበት ለምን እንደሆነ ባያውቅም የዲያብሎስ ውሸታምነት እንዲረጋገጥ አድርጓል። (ኢዮብ 2:9, 10) ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላም ሰይጣን ላለመረታት ሲል አንድ በቁጣ የነደደ የባቢሎን ንጉሥ ሦስት ወጣት ዕብራውያንን ንጉሡ ላቆመው ምስል ካልሰገዱ ወደሚነደው እሳት እንደሚጣሉ በመግለጽ እንዲያስፈራራቸው አድርጓል። ወጣቶቹ ከንጉሡ ትእዛዝና ጣዖት ማምለክን ከሚያወግዘው የይሖዋ ሕግ አንዱን ለመምረጥ ሲገደዱ ይሖዋን እንደሚያገለግሉና የመጨረሻው ሉዓላዊ ገዥያቸው እርሱ እንደሆነ ቁርጥ ባለ አነጋገር አስታወቁ። ለአምላክ ታማኝ መሆን ከሕይወታቸው ይበልጥ ዋጋ ያለው ነገር እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር።—ዳንኤል 3:14-18

14. ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ለይሖዋ ከልብ ታማኝ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

14 ታዲያ እነዚህን ምሳሌዎች ስናይ አንድ ሰው ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ፍጹም መሆን ያስፈልገዋል ብለን መደምደም እንችላለን? ወይም ደግሞ አንድ ሰው አንድ ስሕተት ቢሠራ በቃ አከተመለት ማለት ነው? በፍጹም! መጽሐፍ ቅዱስ ሙሴ ስህተት የሠራባቸው ጊዜያት እንደነበሩ ይገልጻል። ይሖዋ ሙሴ በሠራው ስህተት ባይደሰትም ሞገሱን አልነፈገውም። የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትም የራሳቸው የሆኑ ድክመቶች ነበሯቸው። ይሖዋ የወረስነውን አለፍጽምና ግምት ውስጥ የሚያስገባ ሲሆን ሆን ብለን የእሱን ፈቃድ ችላ እስካላልን ድረስ በእኛ ይደሰታል። ባለብን ድክመት የተነሳ አንድ ኃጢአት ብንሠራ ከልብ ንስሐ መግባትና ድርጊቱ ልማድ እንዳይሆንብን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። በዚህ መንገድ ይሖዋ ጥሩ ነው የሚለውን ነገር እንደምንወድና መጥፎ ነው የሚለውን ደግሞ እንደምንጠላ በተግባር እናሳያለን። ኃጢአትን በሚያስተሰርየው የኢየሱስ መሥዋዕት ላይ ባለን እምነት አማካኝነት በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም ይዘን መኖር እንችላለን።—አሞጽ 5:15፤ የሐዋርያት ሥራ 3:19፤ ዕብራውያን 9:14

15. (ሀ) ከሰው ልጆች መካከል ለአምላክ ፍጹም ታማኝነት ያሳየው ማን ነው? ይህስ ምን አረጋግጧል? (ለ) ኢየሱስ ያደረገው ነገር የሚጠቅመን እንዴት ነው?

15 ይሁንና የሰው ልጆች ለይሖዋ ሉዓላዊነት ፍጹም ታዛዥነት ማሳየት ይችላሉ? የዚህ ጥያቄ መልስ ለ4,000 ዓመታት ገደማ ቅዱስ ምስጢር ሆኖ ቆይቶ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 3:16) አዳም ፍጹም ሆኖ የተፈጠረ ቢሆንም ለአምላክ በማደር ረገድ ፍጹም ምሳሌ ሆኖ አልተገኘም። ታዲያ ማን ሊሆን ይችላል? ኃጢአተኛ ከሆኑት የአዳም ዘሮች መካከል ፍጹም ምሳሌ ሊሆን የሚችል እንደማይገኝ የታወቀ ነው። ይህን ማድረግ የቻለው ብቸኛው ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ዕብራውያን 4:15) ኢየሱስ ያከናወነው ነገር በተሻለ ሁኔታ ውስጥ የነበረው አዳም ቢፈልግ ኖሮ ፍጹም የሆነ ታማኝነት ማሳየት ይችል እንደነበረ አረጋግጧል። አዳም ታማኝ ሆኖ ያልተገኘው አምላክ እንከን ያለው አድርጎ ስለፈጠረው አይደለም። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመለኮታዊ ሕግ በመታዘዝ ብቻ ሳይሆን ለጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ለይሖዋ ያደሩ በመሆን ረገድም ልንኮርጀው የሚገባ ምሳሌያችን ነው።—ዘዳግም 32:4, 5

በግለሰብ ደረጃ ምን ምላሽ እንሰጣለን?

16. ከይሖዋ ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ ባለን አቋም ረገድ ዘወትር ነቅተን መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው?

16 የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት በተመለከተ የተነሳው ጥያቄ በሁላችንም ፊት ተደቅኗል። ከይሖዋ ጎን እንደቆምን በይፋ ካሳወቅን ሰይጣን የጥቃቱ ዒላማ ያደርገናል። ከየአቅጣጫው ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድርብን ሲሆን ይህ ተጽዕኖ እሱ የሚገዛው ክፉ ሥርዓት እስከሚጠፋበት ጊዜ ድረስ ይቀጥላል። ስለዚህ ምንጊዜም ንቁዎች መሆን አለብን። (1 ጴጥሮስ 5:8) ምግባራችን በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ ከተነሳው ታላቅ ጥያቄና በፈተና ወቅት ለአምላክ ታማኝ መሆንን በተመለከተ ከተነሳው ሌላ ጥያቄ ጋር በተያያዘ አቋማችን ምን እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። ታማኝነት የጐደለው ምግባር በዓለም ዘንድ የተለመደ ስለሆነ ብቻ እንደ ቀላል ነገር አድርገን ልንመለከተው አይገባም። ለይሖዋ ታማኝ መሆን በማንኛውም የኑሮ ዘርፍ የጽድቅ መሥፈርቶቹን ተግባራዊ ለማድረግ መጣርን ይጠይቃል።

17. ከውሸትና ከስርቆት መራቅ ያለብን ምንጫቸው ማን ስለሆነ ነው?

17 ለምሳሌ ያህል ‘የሐሰት አባት’ የሆነውን ሰይጣንን መምሰል አይገባንም። (ዮሐንስ 8:44) በማንኛውም ሁኔታ እውነተኞች ሆነን መገኘት አለብን። ባለንበት የሰይጣን ዓለም ውስጥ ብዙውን ጊዜ ልጆች ወላጆቻቸውን ይዋሻሉ። ክርስቲያን ወጣቶች ግን እንዲህ አያደርጉም፤ በመሆኑም የአምላክ ሕዝቦች ፈተና ቢደርስባቸው ታማኝነታቸውን አይጠብቁም የሚለው የሰይጣን ክስ ሐሰት መሆኑን ያረጋግጣሉ። (ኢዮብ 1:9-11፤ ምሳሌ 6:16-19) አንድ ሰው ከእውነት አምላክ ጎን መቆም ሲገባው ‘ከሐሰት አባት’ ጎን እንደቆመ ሊያሳዩ የሚችሉ ከንግድ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች አሉ። እኛ እንዲህ ባሉ የንግድ ጉዳዮች አንካፈልም። (ሚክያስ 6:11, 12) ስርቆት በማንኛውም ሁኔታ ተቀባይነት የለውም። አንድ ሰው በጣም ቢቸግረው እንኳ ወይም የሚሰረቀው ሰው የቱንም ያህል ሀብታም ቢሆን እንዲህ ያለውን ድርጊት ለመፈጸም ሰበብ ሊሆን አይችልም። (ምሳሌ 6:30, 31፤ 1 ጴጥሮስ 4:15) ስርቆት በምንኖርበት አካባቢ የቱንም ያህል የተለመደና የተሰረቀውም ነገር እዚህ ግባ የማይባል ቢሆን እንኳ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት የአምላክን ሕግ የሚጻረር ነው።—ሉቃስ 16:10፤ ሮሜ 12:2፤ ኤፌሶን 4:28

18. (ሀ) በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ዘመን መጨረሻ ላይ የሰው ልጆች ሁሉ ምን ፈተና ይጠብቃቸዋል? (ለ) በአሁኑ ጊዜ ምን ልማድ ማዳበር ይኖርብናል?

18 በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ዘመን ሰይጣንና አጋንንቱ ጥልቁ ውስጥ ስለሚጣሉ በሰው ዘር ላይ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ ማሳደር አይችሉም። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ እፎይታ ነው! ሆኖም ይህ ሺህ ዓመት ሲያበቃ ለተወሰነ ጊዜ ይፈታሉ። ሰይጣንና የእሱ ተከታዮች ወደ ፍጽምና ደረጃ በደረሱትና በታማኝነት ከአምላክ ጎን በቆሙት ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። (ራእይ 20:7-10) በዚያን ጊዜ የመኖር መብት ካገኘን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነትን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ ምን ምላሽ እንሰጣለን? በዚያን ጊዜ ሁሉም ሰው ፍጽምና ደረጃ ላይ ስለሚደርስ ማንኛውም ሰው ታማኝነት የጎደለው ድርጊት የሚፈጽመው ሆን ብሎ ነው፤ ስለሆነም እንዲህ ያለው ድርጊት ዘላለማዊ ጥፋት ያስከትልበታል። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ በቃሉም ሆነ በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠንን ማንኛውንም መመሪያ የመታዘዝ ልማድ ማዳበራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! እንዲህ በማድረግ ለጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ሙሉ በሙሉ ያደርን መሆናችንን እናሳያለን።

የክለሳ ውይይት

• በሁላችንም ፊት የተደቀነው ትልቁ የአቋም ጥያቄ ምንድን ነው? እኛን ሊነካን የቻለውስ እንዴት ነው?

• በጥንት ዘመን የነበሩ ወንዶችና ሴቶች ለይሖዋ ታማኝ መሆናቸውን ያሳዩበት መንገድ ምን ያስገነዝባል?

• በየዕለቱ በምግባራችን ይሖዋን ማስከበራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]