በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቤተሰብ ውስጥ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ማንጸባረቅ

በቤተሰብ ውስጥ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ማንጸባረቅ

ምዕራፍ አሥራ ሰባት

በቤተሰብ ውስጥ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ማንጸባረቅ

1. ብዙ ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረጋቸው በትዳራቸው ላይ ምን ለውጥ አምጥቷል?

የጋብቻ መሥራች ይሖዋ ሲሆን ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተሰብ የሚጠቅም ከሁሉ የላቀ መመሪያ ይዟል። ብዙ ሰዎች ይህን መመሪያ ተግባራዊ በማድረጋቸው ትዳራቸው የተሳካ ሊሆን ችሏል። ጋብቻቸውን ሕጋዊ ሳያደርጉ እንዲሁ አብረው ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ጋብቻቸውን ሕጋዊ ማድረጋቸው የሚያስደስት ነው። ሌሎች ደግሞ ከጋብቻ ውጭ ይፈጽሙት የነበረውን የጾታ ግንኙነት እርግፍ አድርገው ትተዋል። ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ይሰድቡና ይደበድቡ የነበሩ ኃይለኛ ወንዶች ለቤተሰባቸው ደግና አሳቢ ሆነዋል።

2. ክርስቲያናዊ የቤተሰብ ሕይወት ምን ነገሮችን ያካትታል?

2 ክርስቲያናዊ የቤተሰብ ሕይወት ለትዳር ጥምረት ዘላቂነት ያለንን አመለካከት፣ በቤተሰብ ውስጥ ያሉብንን ኃላፊነቶች ለመወጣት የምናደርገውን ጥረትና ከቤተሰባችን አባላት ጋር ያለንን ግንኙነት የመሳሰሉ በርካታ ጉዳዮችን የሚያካትት ነው። (ኤፌሶን 5:33 እስከ 6:4) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቤተሰብ ሕይወት የሚሰጠውን ሐሳብ ማወቅ አንድ ነገር ሲሆን ምክሮቹን ተግባራዊ ማድረግ ግን ሌላ ነገር ነው። ማናችንም ብንሆን ኢየሱስ የአምላክን ትእዛዛት ወደ ጎን ገሸሽ በማድረጋቸው ምክንያት እንዳወገዛቸው ሰዎች መሆን አንፈልግም። እነዚህ ሰዎች እንዲሁ ለሃይማኖት ያደሩ መሆን ብቻ በቂ ነው የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ነበራቸው። (ማቴዎስ 15:4-9) ለአምላክ የማደርን ባሕርይ በቤተሰባችን ውስጥ ማንጸባረቅ ካልቻልን ለአምላክ ያደርን ሰዎች ነን ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር አንችልም። በመሆኑም “ትልቅ ትርፍ” የሆነውን ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ከልብ በመነጨ ስሜት ማንጸባረቅ ይኖርብናል።—1 ጢሞቴዎስ 5:4፤ 6:6 NW፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:5

ትዳር ምን ያህል ዘላቂ መሆን ይኖርበታል?

3. (ሀ) ብዙ ትዳሮች ምን እየሆኑ ነው? ሆኖም የእኛ ቁርጥ ውሳኔ ምን መሆን አለበት? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም ከዚህ አንቀጽ ቀጥሎ የቀረቡትን ጥያቄዎች መልስ።

3 የጋብቻ ሰንሰለት በቀላሉ የሚበጠስ እየሆነ መጥቷል። ለበርካታ ዓመታት በትዳር ተሳስረው የኖሩ አንዳንድ ባልና ሚስት ተፋትተው ሌላ ለማግባት ወስነዋል። በተጨማሪም ወጣት ባልና ሚስቶች ተጋብተው ብዙም ሳይቆዩ መፋታታቸው የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል። ሌሎች ምንም ያድርጉ ምን እኛ ግን ፍላጎታችን ይሖዋን ማስደሰት መሆን ይኖርበታል። እንግዲያው የአምላክ ቃል የትዳርን ዘላቂነት በተመለከተ ምን እንደሚል ለማስተዋል የሚከተሉትን ጥያቄዎችና ጥቅሶች እንመርምር።

አንድ ወንድና አንዲት ሴት በሚጋቡበት ጊዜ ለምን ያህል ጊዜ አብረን እንኖራለን ብለው ማሰብ አለባቸው? (ማርቆስ 10:6-9፤ ሮሜ 7:2, 3)

አንድ ሰው በአምላክ ፊት ተቀባይነት ባለው መንገድ ከትዳር ጓደኛው ለመፋታትና ሌላ ለማግባት ምክንያት የሚሆነው ምን ብቻ ነው? (ማቴዎስ 5:31, 32፤ 19:3-9)

ይሖዋ ቃሉ በሚፈቅደው መሠረት ያልተፈጸመን ፍቺ እንዴት ይመለከተዋል? (ሚልክያስ 2:13-16)

መጽሐፍ ቅዱስ ተለያይቶ መኖር የጋብቻን ችግሮች ለመፍታት ይረዳል ብሎ ያስተምራል? (1 ቆሮንቶስ 7:10-13)

ተለያይቶ ለመኖር ሊያስገድዱ የሚችሉት ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? (መዝሙር 11:5፤ ሉቃስ 4:8፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8)

4. አንዳንድ ትዳሮች የሚጸኑት ለምንድን ነው?

4 አንዳንድ ትዳሮች ስኬታማና ዘላቂ መሆን ችለዋል። ይህ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው? ወንዱም ሆነ ሴቷ ብስለት እስኪያገኙ ድረስ ወደ ትዳር ዓለም አለመግባታቸው አንዱ ወሳኝ ነገር ሲሆን ተመሳሳይ ፍላጎት ያለውና ነገሮችን አብሮ በግልጽ መወያየት የሚችል የትዳር ጓደኛ ማግኘትም ሌላው አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው። ይሖዋን የሚወድና የሚያጋጥሙትን ችግሮች በቃሉ መሠረት ለመፍታት የሚጥር የትዳር ጓደኛ ማግኘት ግን ከሁሉም በላይ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው። (መዝሙር 119:97, 104፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) እንዲህ ዓይነቱ ሰው አንዳንድ ነገሮች እንዳሰባቸው ሳይሆኑ ቢቀሩ መለያየት ወይም መፋታት እንደሚቻል አድርጎ አያስብም። የትዳር ጓደኛውን ድክመቶች ሰበብ በማድረግ ካሉበት ኃላፊነቶች ለመሸሽ አይሞክርም። ከዚህ ይልቅ ችግሮቹን በመጋፈጥ ጥሩ መፍትሔ ለማግኘት ይጥራል።

5. (ሀ) ለይሖዋ ታማኝ መሆን በትዳር ውስጥ ምን ድርሻ ያበረክታል? (ለ) ተቃውሞ በሚኖርበት ጊዜም እንኳ ይሖዋ ያወጣቸውን መሥፈርቶች መጠበቅ ምን ጥቅሞችን ሊያስገኝ ይችላል?

5 ሰይጣን ችግር ሲደርስብን የይሖዋን መንገዶች እንደምንተው አድርጎ ይከራከራል። (ኢዮብ 2:4, 5፤ ምሳሌ 27:11) ሆኖም ተቃዋሚ በሆነ የትዳር ጓደኛ የተነሳ ብዙ ችግር የደረሰባቸው አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች የጋብቻ ቃለ መሃላቸውን አላፈረሱም። ለይሖዋም ሆነ ለትእዛዛቱ ታማኞች ሆነው ጸንተዋል። (ማቴዎስ 5:37) እንዲያውም ለብዙ ዓመታት ሲደርስባቸው የነበረውን ተቃውሞ ተቋቁመው የጸኑ አንዳንዶች የትዳር ጓደኛቸው ከጎናቸው ሆኖ ይሖዋን ማገልገል በመጀመሩ ደስታ አግኝተዋል። (1 ጴጥሮስ 3:1, 2) ሌሎቹ ደግሞ የትዳር ጓደኛቸው የመለወጥ ዝንባሌ ባያሳይም ወይም ይሖዋን በማገልገላቸው ጥሏቸው ቢሄድም በቤተሰባቸው ውስጥ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ በማንጸባረቃቸው ይሖዋ እንደሚባርካቸው ያውቃሉ።—መዝሙር 55:22፤ 145:16

እያንዳንዱ የራሱን ድርሻ ሲወጣ

6. ትዳር ስኬታማ እንዲሆን የትኛውን ዝግጅት ማክበር ያስፈልጋል?

6 አንድን ትዳር ስኬታማ የሚያሰኘው ባለትዳሮቹ እንዲሁ አብረው መኖር መቻላቸው ብቻ አይደለም። ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ይሖዋ ከራስነት ሥልጣን ጋር በተያያዘ ላደረገው ዝግጅት አክብሮት ማሳየታቸው በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ይህም በቤተሰቡ ውስጥ ሥርዓትና የተረጋጋ መንፈስ እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ያደርጋል። አንደኛ ቆሮንቶስ 11:3 “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ ነው፤ የሴትም ራስ ወንድ ነው፤ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር ነው” ይላል።

7. የራስነት ሥልጣን በቤተሰብ ውስጥ ሊሠራበት የሚገባው እንዴት ነው?

7 በዚህ ጥቅስ ላይ በመጀመሪያ የተጠቀሰው ምን እንደሆነ ልብ ብለሃል? አዎን፣ እያንዳንዱ ወንድ ለክርስቶስ የራስነት ሥልጣን መገዛት ይኖርበታል። ይህም ማለት ባል የራስነት ሥልጣኑን የኢየሱስን ባሕርያት በሚያንጸባርቅ መንገድ ሊጠቀምበት ይገባል ማለት ነው። ክርስቶስ ለይሖዋ የሚገዛ ሲሆን ጉባኤውን ይወዳል እንዲሁም ይንከባከባል። (1 ጢሞቴዎስ 3:15) እንዲያውም ራሱን ለጉባኤው ‘አሳልፎ እስከ መስጠት ደርሷል።’ ኢየሱስ “የዋህና ትሑት” እንጂ ኩሩና ለሌሎች የማያስብ ሰው አልነበረም። ራሳቸውን ለእሱ የራስነት ሥልጣን የሚያስገዙ ሁሉ ‘ለነፍሳቸው ዕረፍት ያገኛሉ።’ አንድ ባል ቤተሰቡን በዚህ መንገድ የሚይዝ ከሆነ ራሱን ለክርስቶስ እያስገዛ እንዳለ ያሳያል። በዚህ ጊዜ አንዲት ክርስቲያን ሚስት ከባሏ ጋር መተባበሯና ለራስነት ሥልጣኑ መገዛቷ ጠቃሚና እረፍት የሚያስገኝ ይሆንላታል።—ኤፌሶን 5:25-33፤ ማቴዎስ 11:28, 29፤ ምሳሌ 31:10, 28

8. (ሀ) በአንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ የሚከሰቱ ሁኔታዎችን ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ ለመያዝ መሞከር የተፈለገውን ውጤት የማያስገኝ መስሎ የሚታየው ለምንድን ነው? (ለ) እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢያጋጥመን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

8 ያም ሆኖ ችግሮች መፈጠራቸው አይቀርም። የቤተሰቡ አባላት በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመላለስ ከመጀመራቸው በፊት በሌላ ሰው አመራር ሥር ሆኖ መኖር የማያስደስታቸው ዓይነት ሰዎች የነበሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ፍቅርና ደግነት ማሳየት ብዙም ውጤት የማያመጣ መስሎ ሊታይ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ቊጣና ንዴትን፣ ጭቅጭቅና ስድብን” አስወግዱ የሚል ምክር እንደሚሰጥ እናውቃለን። (ኤፌሶን 4:31) ይሁንና አንዳንድ የቤተሰብ አባላት በቁጣና በጩኸት ካልሆነ በስተቀር በሌላ መንገድ ቢነገራቸው የማይገባቸው ቢሆኑ ምን መደረግ ይኖርበታል? ኢየሱስ ይዝቱበትና ይሰድቡት ለነበሩት ሰዎች አጸፋውን ከመመለስ ይልቅ በአባቱ መታመንን መርጧል። (1 ጴጥሮስ 2:22, 23) ስለዚህ በቤተሰብ ውስጥ ፈታኝ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙህ ጊዜ የዓለምን መንገድ ከመከተል ይልቅ ይሖዋ እንዲረዳህ በመጸለይ ለአምላክ የማደር ባሕርይ እንዳለህ በተግባር አሳይ።—ምሳሌ 3:5-7

9. አብዛኞቹ ክርስቲያን ባሎች ስህተት ለመለቃቀም ከመጣር ይልቅ ምን ማድረግ ተምረዋል?

9 ሁልጊዜ ፈጣን የሆነ ለውጥ ማድረግ ባይቻልም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በትዕግሥትና ትጋት በተሞላበት መንገድ ሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ከተደረገ ጥሩ ውጤት ይገኛል። ብዙ ባሎች ክርስቶስ ጉባኤውን የያዘበትን መንገድ በሚገባ በመገንዘብ የወሰዱት እርምጃ በትዳራቸው ላይ ለውጥ እንዳመጣ ማስተዋል ችለዋል። የክርስቲያን ጉባኤ ፍጹም በሆኑ ሰዎች የተገነባ አይደለም። ሆኖም ኢየሱስ ጉባኤውን የሚወድ ከመሆኑም በላይ ለጉባኤው ጥሩ ምሳሌ ትቷል፤ እንዲሁም ጉባኤው እንዲሻሻል ለመርዳት ቅዱሳን ጽሑፎችን መሣሪያ አድርጎ ይጠቀማል። ከዚህም በተጨማሪ ሕይወቱን ለጉባኤው ሠውቷል። (1 ጴጥሮስ 2:21) እሱ የተወው ምሳሌ ብዙ ክርስቲያን ባሎች ጥሩ የቤተሰብ ራስ እንዲሆኑና ትዳራቸውን ለማሻሻል የሚያስችል ፍቅራዊ እርዳታ እንዲያበረክቱ አነሳስቷቸዋል። ስህተት ለመለቃቀም ከመጣር ወይም ከማኩረፍ ይልቅ ይህን ዘዴ መጠቀም እጅግ የተሻለ ውጤት ያስገኛል።

10. (ሀ) አንድ ባል ወይም አንዲት ሚስት ክርስቲያን እንደሆኑ የሚናገሩ ቢሆኑም እንኳ የቤተሰባቸውን ሕይወት አስቸጋሪ ሊያደርጉ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ሁኔታውን ለማሻሻል ምን ማድረግ ይቻላል?

10 አንድ ባል የቤተሰቡን ስሜታዊ ፍላጎት የማይረዳ ወይም ቅድሚያውን ወስዶ ለቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይትም ሆነ ለሌሎች እንቅስቃሴዎች አስፈላጊውን ዝግጅት የማያደርግ ከሆነስ? ወይም ደግሞ አንዲት ሚስት የተባባሪነት መንፈስ የሌላትና አምላካዊ ተገዥነት የማታሳይ ብትሆንስ? አንዳንዶች ችግሩን በተመለከተ በቤተሰብ ደረጃ አክብሮት በተሞላበት መንገድ በመወያየት ጥሩ ውጤት ማግኘት ችለዋል። (ዘፍጥረት 21:10-12፤ ምሳሌ 15:22) ውጤቱ ተስፋ ያደረግነውን ያህል ባይሆንም እያንዳንዳችን በሁሉም የኑሮ ዘርፍ የመንፈስ ፍሬን በማፍራትና ለሌሎች የቤተሰቡ አባሎች ፍቅራዊ አሳቢነት በማሳየት በቤተሰቡ ውስጥ የሰፈነው መንፈስ እንዲሻሻል አስተዋጽኦ ልናበረክት እንችላለን። (ገላትያ 5:22, 23) ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ሌላው ሰው አንድ ነገር እንዲያደርግ በመጠበቅ ሳይሆን የበኩላችንን ኃላፊነት በመወጣት ነው፤ በዚህ መንገድ ለአምላክ ያደርን ሰዎች መሆናችንን በተግባር እናሳያለን።—ቈላስይስ 3:18-21

መልስ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?

11, 12. ይሖዋ የቤተሰብ ሕይወታችን የተሳካ እንዲሆን ለመርዳት ምን ዝግጅት አድርጓል?

11 ሰዎች ከቤተሰባቸው ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ምክር ለማግኘት ይጥራሉ። እኛ ግን ከሁሉ የላቀው ምክር የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሆነ እናውቃለን፤ በተጨማሪም አምላክ በሚታየው ድርጅቱ አማካኝነት ቃሉን ሥራ ላይ እንድናውል የሚረዳን በመሆኑ እጅግ አመስጋኞች ነን። ታዲያ አንተ በዚህ ዝግጅት ሙሉ በሙሉ እየተጠቀምክ ነው?—መዝሙር 119:129, 130፤ ሚክያስ 4:2

12 በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከመገኘት በተጨማሪ በቤተሰብ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ቋሚ ጊዜ መድበሃል? እንዲህ የሚያደርጉ ቤተሰቦች በአምልኮ አንድ ሊሆኑ ይችላሉ። የአምላክን ቃል ከቤተሰባቸው ሁኔታ ጋር በሚስማማ መንገድ ተግባራዊ ሲያደርጉ የቤተሰባቸው ሕይወት ይሻሻላል።—ዘዳግም 11:18-21

13. (ሀ) ከቤተሰብ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ካሉን ብዙውን ጊዜ አጥጋቢ የሆነ መልስ ልናገኝ የምንችለው ከየት ነው? (ለ) የምናደርጋቸው ውሳኔዎች በሙሉ ምን የሚንጸባረቅባቸው መሆን ይኖርባቸዋል?

13 ከቤተሰብ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ሊኖሩህ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን መጠቀም ይቻላል? ጽንስን ማስወረድ ተገቢ የሚሆንበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል? አንድ ልጅ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ብዙም ፍላጎት ባይኖረው በቤተሰቡ የአምልኮ ሥርዓት ውስጥ እንዲካፈል የሚጠበቅበት እስከ ምን ድረስ ነው? እንዲህ የመሳሰሉ በርካታ ጥያቄዎች የይሖዋ ምሥክሮች ባዘጋጅዋቸው ጽሑፎች ላይ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል። መልሶቹን ለማግኘት የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫዎችን ጨምሮ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ የተለያዩ ጽሑፎችን የመጠቀም ልማድ አዳብር። የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ የሚጠቅሳቸው ጽሑፎች ከሌሉህ በመንግሥት አዳራሽ ባለው ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ይገኙ እንደሆነና እንዳልሆነ ማጣራት ትችላለህ። አሊያም ደግሞ በኮምፒውተር አማካኝነት እነዚህን ጽሑፎች ማግኘት የምትችልበት አጋጣሚ ይኖርህ ይሆናል። በተጨማሪም ጥያቄዎችህን ከጎለመሱ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ጋር ልትወያይባቸው ትችላለህ። ሆኖም ለእያንዳንዱ ጥያቄ ሁልጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብህና እንደሌለብህ የሚገልጽ ቀጥተኛ የሆነ መልስ አገኛለሁ ብለህ አትጠብቅ። አብዛኛውን ጊዜ በግልህ ወይም ከትዳር ጓደኛህ ጋር ተማክረህ ውሳኔ ላይ መድረስ ያለብህ አንተው ራስህ ነህ። በመሆኑም በውጭ ብቻ ሳይሆን በቤት ውስጥም ለአምላክ የማደርን ባሕርይ እንደምታንጸባርቅ የሚያሳይ ውሳኔ አድርግ።—ሮሜ 14:19፤ ኤፌሶን 5:10

የክለሳ ውይይት

• አንድ ሰው ለትዳር ጓደኛው ታማኝ መሆኑ ለይሖዋ ካለው ታማኝነት ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

• በቤተሰብ ችግሮች ምክንያት ውጥረት ውስጥ በምንገባበት ጊዜ አምላክን ደስ የሚያሰኘውን ነገር እንድናደርግ የሚረዳን ምንድን ነው?

• ሌሎቹ የቤተሰቡ አባላት ጉድለት ቢኖርባቸው እንኳ እኛ ሁኔታውን ለማሻሻል ምን ልናደርግ እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 155 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ባል የራስነት ሥልጣኑን የሚጠቀምበት መንገድ የኢየሱስን ባሕርያት የሚያንጸባርቅ መሆን ይኖርበታል

[በገጽ 157 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቤተሰብ ደረጃ ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ለቤተሰቡ አንድነት አስተዋጽኦ ያበረክታል