በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በይሖዋ ዙፋን ፊት የቆሙ እጅግ ብዙ ሕዝብ

በይሖዋ ዙፋን ፊት የቆሙ እጅግ ብዙ ሕዝብ

ምዕራፍ አሥራ ሦስት

በይሖዋ ዙፋን ፊት የቆሙ እጅግ ብዙ ሕዝብ

1. (ሀ) በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ የአምላክ አገልጋዮችም ሆኑ መቶ አርባ አራት ሺዎቹ ሽልማታቸውን ከማግኘታቸው በፊት ምን መሆን አለባቸው? (ለ) በዘመናችን ያሉት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ምን አጋጣሚ አላቸው?

ከአቤል ጀምሮ እስከ አጥማቂው ዮሐንስ ድረስ የነበሩት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ከምንም ነገር በላይ የአምላክን ፈቃድ ያስቀድሙ ነበር። ይሁንና ሁሉም በሞት ያንቀላፉ ሲሆን አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ትንሣኤ አግኝተው በምድር ላይ የሚኖሩበትን ጊዜ በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ መንግሥቱ የሚገዙት 144,000ዎችም ሽልማታቸውን ከማግኘታቸው በፊት መሞት አለባቸው። ይሁን እንጂ ራእይ 7:9 በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት፣ ሞትን ሳይቀምሱ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” እንደሚኖሩ ይገልጻል። አንተ ከእነዚህ መካከል ነህ?

እጅግ ብዙ ሕዝብ የተባሉት እነማን ናቸው?

2. በ⁠ራእይ 7:9 ላይ የተገለጹትን እጅግ ብዙ ሕዝብ ማንነት በግልጽ መረዳት የተቻለው እንዴት ነው?

2 በ1923 የይሖዋ አገልጋዮች ማቴዎስ 25:31-46 ላይ በተገለጸው የኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሱት “በጎች” እና በ⁠ዮሐንስ 10:16 ላይ የተጠቀሱት “ሌሎች በጎች” በምድር ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ያላቸው ሰዎች እንደሆኑ ተገንዝበው ነበር። በ1931 ደግሞ በ⁠ሕዝቅኤል 9:1-11 ላይ የተገለጹት ግምባራቸው ላይ ምልክት የተደረገባቸው ሰዎችም ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ሰዎች እንደሚያመለክቱ መረዳት ተችሏል። ከዚያም በ1935፣ እጅግ ብዙ ሕዝብ የተባሉት ሰዎች ኢየሱስ የገለጻቸው ሌሎች በጎች ክፍል እንደሆኑ ታወቀ። የአምላክን ሞገስ ያገኙት እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሆነዋል።

3. እጅግ ብዙ ሕዝብ ‘በዙፋኑ ፊት እንደቆሙ’ መገለጹ ወደ ሰማይ የሚሄዱ መሆናቸውን አያመለክትም የምንለው ለምንድን ነው?

3 በ⁠ራእይ 7:9 ላይ የተጠቀሱት እጅግ ብዙ ሕዝብ በራእዩ ላይ የታዩት በሰማይ ሆነው አይደለም። እነዚህ ሰዎች በአምላክ ‘ዙፋን ፊት ለመቆም’ የግድ ሰማይ መሄድ አያስፈልጋቸውም። በዙፋኑ ፊት እንደቆሙ መገለጹ አምላክ የሚያያቸው መሆኑን የሚያመለክት ነው። (መዝሙር 11:4) ይህ ሕዝብ ቁጥሩ ያልተወሰነ መሆኑን በራእይ 7:4-8 እና በራእይ 14:1-4 ላይ ከሰፈረው ሐሳብ ጋር በማነጻጸር “ማንም ሊቈጥራቸው የማይችል” የተባሉት እነዚህ ሰዎች የሰማያዊ ክፍል አባላት እንዳልሆኑ መረዳት ይቻላል። በእነዚህ ጥቅሶች ላይ ከምድር ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች ቁጥር 144,000 እንደሆነ ተገልጿል።

4. (ሀ) እጅግ ብዙ ሕዝብ የሚተርፉት ከየትኛው ‘ታላቅ መከራ’ ነው? (ለ) በ⁠ራእይ 7:11, 12 ላይ በተገለጸው መሠረት እነዚህ ሰዎች የሚያደርጉትን ተመልክተው በአምልኮ የሚተባበሯቸው እነማን ናቸው?

4 ራእይ 7:14 እነዚህን ሰዎች አስመልክቶ ሲናገር “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው” ይላል። በሰው ዘር ታሪክ ታይቶ ከማያውቀው ታላቅ መከራ ይተርፋሉ። (ማቴዎስ 24:21) በአምላክና በክርስቶስ አማካኝነት ለመዳን በመብቃታቸው ምስጋናቸውን በሚገልጹበት ጊዜ በሰማይ ያሉት ታማኝ ፍጥረታት ሁሉ “አሜን፤ ውዳሴና ክብር፣ ጥበብ፣ ምስጋናና፣ ሞገስ፣ ኀይልና ብርታትም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን፤ አሜን” በማለት አብረዋቸው ውዳሴ ያቀርባሉ።—ራእይ 7:11, 12

ለመዳን የሚበቁ መሆናቸውን ማስመሥከር

5. ከእጅግ ብዙ ሕዝብ አንዱ ለመሆን ምን እንደሚያስፈልግ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

5 እጅግ ብዙ ሕዝብ ከታላቁ መከራ የሚድኑት በይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች መሠረት ነው። ከጥፋቱ የሚድኑት ሰዎች ሊያሳዩአቸው የሚገቡት ባሕርያት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ሰፍረዋል። ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ ጽድቅ ወዳድ የሆኑ ሁሉ ለመዳን የሚበቁ መሆናቸውን በሚያስመሠክር መንገድ መመላለስ ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

6. እጅግ ብዙ ሕዝብ በበጎች መመሰላቸው ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

6 በጎች ገራምና ታዛዥ የሆኑ እንስሳት ናቸው። ስለዚህ ኢየሱስ የሰማያዊ ክፍል አባላት ያልሆኑ ሌሎች በጎች እንዳሉት ሲናገር በምድር ላይ ለዘላለም መኖር የሚፈልጉ ብቻ ሳይሆን ትምህርቶቹንም የሚታዘዙ ሰዎች እንዳሉ መናገሩ ነበር። “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔ ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 10:16, 27) እነዚህ ሰዎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን እሱን የሚሰሙና ያዘዛቸውን የሚያደርጉ ናቸው።

7. የኢየሱስ ተከታዮች የትኞቹን ባሕርያት ማዳበር ያስፈልጋቸዋል?

7 እነዚህ የኢየሱስ ተከታዮች በግለሰብ ደረጃ ምን ሌሎች ባሕርያት ማዳበር ያስፈልጋቸዋል? የአምላክ ቃል ‘ቀድሞ በነበራችሁ ሕይወት የለበሳችሁትን አሮጌ ሰውነት አውልቃችሁ ጣሉ፤ እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ’ ሲል መልስ ይሰጣል። (ኤፌሶን 4:22-24) የአምላክ አገልጋዮችን አንድነት የሚያጠናክሩ ባሕርያትን ማለትም ‘ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ትዕግሥትን፣ ቸርነትን፣ በጎነትን፣ ታማኝነትን፣ ገርነትንና ራስን መግዛትን’ ያዳብራሉ።—ገላትያ 5:22, 23

8. እጅግ ብዙ ሕዝብ ለቅቡዓን ቀሪዎች ድጋፍ በመስጠታቸው ምን ይገጥማቸዋል?

8 እጅግ ብዙ ሕዝብ የስብከቱን ሥራ በግንባር ቀደምትነት የሚያከናውኑትን አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የሰማያዊ ተስፋ ወራሾች ይረዷቸዋል። (ማቴዎስ 24:14፤ 25:40) በእነዚህ መጨረሻ ቀኖች መጀመሪያ ላይ ክርስቶስ ኢየሱስና መላእክቱ ሰይጣንንና አጋንንቱን ከሰማይ ወደ ምድር በመጣላቸው የተነሳ ሌሎች በጎች ተቃውሞ እንደሚያጋጥማቸው ቢያውቁም እንኳ ይህን ድጋፍ ከመስጠት ወደኋላ አይሉም። ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ ምድር መጣላቸው ‘ለምድር ወዮታ’ አስከትሏል። “ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን ብቻ እንደ ቀረው ስላወቀ፣ በታላቅ ቍጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዶአል።” (ራእይ 12:7-12) በመሆኑም የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እየቀረበ በሄደ መጠን ሰይጣን በአምላክ አገልጋዮች ላይ የሚሰነዝረውን ተቃውሞ ይበልጥ ያፋፍመዋል።

9. የአምላክ አገልጋዮች ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ምን ያህል ስኬታማ ሆነዋል? ለምንስ?

9 ከባድ ስደት ቢኖርም የስብከቱ ሥራ ወደፊት መግፋቱን ይቀጥላል። ይሖዋ “በአንቺ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል” ብሎ ቃል ገብቶ ስለነበር የመንግሥቱ ሰባኪዎች ቁጥር በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ ከነበረው ጥቂት ሺህ ተነስቶ በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሆኗል። (ኢሳይያስ 54:17) አንድ የአይሁድ ከፍተኛ ሸንጎ አባል እንኳ ሳይቀር የአምላክ ሥራ ፈጽሞ ሊከሽፍ እንደማይችል ተገንዝቦ ነበር። ደቀ መዛሙርቱን በተመለከተ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ፈሪሳውያን “አትንኳቸው፤ ሐሳባቸው ወይም አድራጎታቸው ከሰው ከሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ ግን ልትገቷቸው አትችሉም፤ እንዲያውም ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ትገኙ ይሆናል” ብሏቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 5:38, 39

10. (ሀ) በእጅግ ብዙ ሕዝብ ላይ የተደረገው “ምልክት” የምን ምሳሌ ነው? (ለ) የአምላክ አገልጋዮች ‘ከሰማይ የተሰማውን ድምፅ’ የሚታዘዙት እንዴት ነው?

10 እጅግ ብዙ ሕዝብ ከጥፋት ይድኑ ዘንድ ምልክት እንደተደረገባቸው ሆነው ተገልጸዋል። (ሕዝቅኤል 9:4-6) ‘ምልክቱ’ ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑና የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሆነው የተጠመቁ እንዲሁም የክርስቶስ ዓይነት ባሕርይ ለማንጸባረቅ የሚጥሩ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። የሰይጣንን ዓለም አቀፍ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በተመለከተ “ሕዝቤ ሆይ፤ በኀጢአቷ እንዳትተባበሩ፣ ከመቅሠፍቷም እንዳትካፈሉ፣ ከእርሷ ውጡ” የሚለውን ‘ከሰማይ የተሰማ ድምፅ’ ይታዘዛሉ።—ራእይ 18:1-5

11. እጅግ ብዙ ሕዝብ የይሖዋ አገልጋዮች መሆናቸውን በዋነኝነት የሚያሳዩት በምን መንገድ ነው?

11 ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ተከታዮቹን “እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 13:35) በአንጻሩ ግን የዚህ ዓለም ሃይማኖቶች አባላት የሆኑ ሰዎች ጦርነት ውስጥ ገብተው የራሳቸውን ሃይማኖት አባላት ይገድላሉ፤ በአብዛኛው ይህን የሚያደርጉት ደግሞ በአገርና በብሔር ስለሚለያዩ ብቻ ነው! የአምላክ ቃል እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት በዚህ ነው:- ጽድቅን የማያደርግ፣ ወንድሙንም የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም። . . . እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል . . . የክፉው ወገን ሆኖ ወንድሙን እንደ ገደለው እንደ ቃየን አትሁኑ።”—1 ዮሐንስ 3:10-12

12. ይሖዋ መጥፎ ፍሬ የሚያፈሩትን ሃይማኖታዊ ‘ዛፎች’ በታላቁ መከራ ወቅት ምን ያደርጋቸዋል?

12 ኢየሱስ “ጥሩ ዛፍ ሁሉ ጥሩ ፍሬ፣ መጥፎ ዛፍ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል። ጥሩ ዛፍ መጥፎ ፍሬ፣ መጥፎም ዛፍ ጥሩ ፍሬ ማፍራት አይችልም። ጥሩ ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል። ስለዚህ በፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ” ሲል ገልጿል። (ማቴዎስ 7:17-20) የዚህ ዓለም ሃይማኖቶች ያፈሩት ፍሬ በቅርቡ ይሖዋ በታላቁ መከራ የሚያጠፋቸው መጥፎ ‘ዛፎች’ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው።—ራእይ 17:16

13. እጅግ ብዙ ሕዝብ በአንድነት በይሖዋ ‘ዙፋን ፊት መቆማቸውን’ በተግባር የሚያሳዩት እንዴት ነው?

13 ራእይ 7:9-15 እጅግ ብዙ ሕዝብ ከጥፋት እንዲድኑ የሚያደርጋቸው ነገር ምን እንደሆነ ይጠቁማል። የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት በመደገፍ በአንድነት ‘በዙፋኑ ፊት ቆመው’ ታይተዋል። ‘ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው ያነጹ’ ሲሆን ይህም ኃጢአትን የሚያስተሰርየውን የኢየሱስ መሥዋዕት አምነው እንደተቀበሉ ያሳያል። (ዮሐንስ 1:29) ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሲሆን ይህንንም በውኃ በመጠመቅ አሳይተዋል። በመሆኑም በነጭ ልብስ የተመሰለውን ንጹሕ አቋም ይዘው በመመላለስ አምላክን ‘ቀንና ሌሊት ያገለግሉታል።’ ሕይወትህን እዚህ ላይ ከተገለጸው ሁኔታ ጋር ማስማማት ትችል ይሆን?

በአሁኑ ጊዜ የሚገኙ ጥቅሞች

14. የይሖዋ አገልጋዮች በአሁኑ ጊዜም እንኳ የሚያገኟቸው አንዳንድ ለየት ያሉ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

14 ይሖዋን የሚያገለግሉ ሰዎች በአሁኑ ጊዜም እንኳ ቢሆን እያገኙ ያሉትን በዓይነቱ ልዩ የሆነ ጥቅም ሳታስተውል አልቀረህም። ለምሳሌ ያህል ስለ ይሖዋ የጽድቅ ዓላማዎች ስትማር የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ብሩህ ተስፋ እንዳለ ተገንዝበሃል። በመሆኑም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት አስደሳች ተስፋ ይዘህ እውነተኛውን አምላክ ማገልገል የምትችልበት አጋጣሚ ስላገኘህ ሕይወትህ ዓላማ ያለው ሆኗል። አዎን፣ ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ “[እጅግ ብዙ ሕዝብን] ወደ ሕይወት ውሃ ምንጭም ይመራቸዋል።”—ራእይ 7:17

15. የይሖዋ ምሥክሮች ከፖለቲካና ከሥነ ምግባር ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተላቸው የጠቀማቸው እንዴት ነው?

15 እጅግ ብዙ ሕዝብ ካገኟቸው አስደናቂ ጥቅሞች አንዱ በዓለም ዙሪያ በይሖዋ አገልጋዮች መካከል ያለው ፍቅር፣ አንድነትና ስምምነት ነው። ከአንድ መንፈሳዊ ማዕድ ስለምንመገብ ሁላችንም የምንመራው በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙ አንድ ዓይነት ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ነው። ፖለቲካዊም ሆነ ብሔራዊ ርዕዮተ ዓለም የማይከፋፍለን ለዚህ ነው። ከዚህም በተጨማሪ አምላክ ከሕዝቡ የሚፈልጋቸውን ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እናሟላለን። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) ስለሆነም የይሖዋ ሕዝቦች በዓለም ላይ ካለው ግጭት፣ መከፋፈልና ብልሹ ሥነ ምግባር ተጠብቀው በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ መኖር ችለዋል። ይህ በ⁠ኢሳይያስ 65:13, 14 ላይ እንዴት እንደተገለጸ ልብ በል።

16. እጅግ ብዙ ሕዝብ በዓለም ላይ ያሉ የተለያዩ ችግሮች ቢደርሱባቸውም ምን ተስፋ አላቸው?

16 እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ሰብዓዊ አገልጋዮች ፍጹማን አይደሉም። እንዲሁም በዚህ ዓለም ውስጥ ባሉ ችግሮች ሊጠቁ ይችላሉ። የተለያዩ መከራዎች ሊደርሱባቸው ወይም ብሔራት በሚያደርጉት ጦርነት ለአደጋ ሊጋለጡና የጥቃት ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪም ሊታመሙ፣ ሊሠቃዩና ሊሞቱ ይችላሉ። ሆኖም በአዲሱ ዓለም አምላክ ‘እንባን ሁሉ ከዐይናቸው እንደሚያብስና ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ እንደማይኖር’ ሙሉ እምነት አላቸው።—ራእይ 21:4

17. በአሁኑ ጊዜ የሚደርስብን ሁኔታ ምንም ይሁን ምን እውነተኛውን አምላክ የሚያመልኩ ሰዎች ወደፊት ምን አስደናቂ ጊዜ ይጠብቃቸዋል?

17 በአሁኑ ጊዜ በእርጅና፣ በበሽታ፣ በአደጋም ሆነ በስደት ሕይወትህን ብታጣ እንኳ ይሖዋ በገነት ውስጥ ከሞት ያስነሳሃል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) ከዚያም በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ከሚቀርበው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ማዕድ መመገብህን ትቀጥላለህ። ዓላማዎቹ በሚያስደንቅ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ስትመለከት ለይሖዋ ያለህ ፍቅር እየጨመረ ይሄዳል። በዚያን ጊዜ ይሖዋ የሚያፈሳቸው ቁሳዊ በረከቶችም ለእሱ ያለህን ፍቅር ይበልጥ ያጠናክሩልሃል። (ኢሳይያስ 25:6-9) የአምላክ ሕዝቦች እንዴት ያለ አስደናቂ ጊዜ ይጠብቃቸዋል!

የክለሳ ውይይት

• መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ ብዙ ሕዝብን ከየትኛው ልዩ ሁኔታ ጋር አያይዞ ይጠቅሳቸዋል?

• መለኮታዊ ሞገስ ካገኙት እጅግ ብዙ ሕዝብ አንዱ ለመሆን ከፈለግን አሁን ምን ማድረግ አለብን?

• እጅግ ብዙ ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ ያገኟቸውንም ሆነ ወደፊት በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚያገኟቸውን በረከቶች ምን ያህል ከፍ አድርገህ ትመለከታቸዋለህ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 123 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሚሊዮን የሚቆጠሩት እጅግ ብዙ ሕዝብ እውነተኛውን አምላክ አንድ ሆነው ያመልካሉ