በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ነቢያት ሁሉ የመሰከሩለት

ነቢያት ሁሉ የመሰከሩለት

ምዕራፍ አራት

ነቢያት ሁሉ የመሰከሩለት

1. ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ስለነበረው ሕልውና የሚገልጹት መረጃዎች ከይሖዋ ጋር ስላለው ዝምድና ምን ይጠቁማሉ?

“አብ ወልድን ስለሚወድ የሚያደርገውን ሁሉ ያሳየዋል።” (ዮሐንስ 5:20) ወልድ ከአብ ማለትም ከይሖዋ ጋር እንዴት ያለ የጠበቀ ዝምድና ነበረው! ይህ የጠበቀ ወዳጅነት የተመሠረተው ወልድ ሰው ሆኖ ከመወለዱ ሕልቆ መሳፍርት ከሌለው ዘመን በፊት ነው። ወልድ የአምላክ አንድያ ልጅ ማለትም ይሖዋ ራሱ በቀጥታ የፈጠረው ብቸኛው ፍጡር ነው። በሰማይና በምድር ያለው የተቀረው ነገር የተፈጠረው እጅግ ተወዳጅ በሆነው በዚህ የበኩር ልጅ አማካኝነት ነው። (ቈላስይስ 1:15, 16) በተጨማሪም የአምላክ ቃል ማለትም መለኮታዊውን ፈቃድ ለሌሎች የሚያሳውቅ ቃል አቀባይ ሆኖ አገልግሏል። አምላክ በጣም የሚወደው ይህ ልጅ ሰው ሆኖ በመወለድ ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎ ተጠርቷል።—ምሳሌ 8:22-30፤ ዮሐንስ 1:14, 18፤ 12:49, 50

2. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ስለ ኢየሱስ ምን ያህል ይናገራሉ?

2 የአምላክ የበኩር ልጅ በተአምራዊ መንገድ ሰው ሆኖ ከመጸነሱ በፊት እሱን በተመለከተ በመንፈስ አነሳሽነት የተነገሩ በርካታ ትንቢቶች አሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል” ሲል ለቆርኔሌዎስ ገልጾለታል። (የሐዋርያት ሥራ 10:43) ኢየሱስ የሚጫወተው ሚና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሰፊው የተገለጸ በመሆኑ አንድ መልአክ ለሐዋርያው ዮሐንስ “ትንቢት የሚነገረው ለኢየሱስ ለመመስከር ነው” እስከ ማለት ደርሷል። (ራእይ 19:10 NW) እነዚህ ትንቢቶች ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ አመልክተዋል። የአምላክን ዓላማዎች በማስፈጸም ረገድ የሚጫወታቸውን የተለያዩ ሚናዎች ጠቁመዋል። ይህ ሁሉ ዛሬ ያለነውን ሰዎች ትኩረት ሊስብ ይገባል።

ትንቢቶቹ ምን ገልጸው ነበር?

3. (ሀ) በ⁠ዘፍጥረት 3:15 ላይ በሚገኘው ትንቢት ውስጥ በእባቡ፣ “በሴቲቱ” እና ‘በእባቡ ዘር’ የተመሰሉት እነማን ናቸው? (ለ) ‘የእባቡ ራስ መቀጥቀጥ’ የይሖዋን አገልጋዮች ትኩረት በእጅጉ የሚስበው ለምንድን ነው?

3 ከእነዚህ ትንቢቶች መካከል የመጀመሪያው የተነገረው በኤደን ዓመጽ ከተፈጸመ በኋላ ነው። ይሖዋ እባቡን እንዲህ አለው:- “በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።” (ዘፍጥረት 3:15) ይሖዋ ይህን ትንቢት የተናገረው በእባብ ለተወከለው ለሰይጣን ነው። “ሴቲቱ” ለይሖዋ እንደ ታማኝ ሚስት የሆነችውን ሰማያዊ ድርጅት ታመለክታለች። ‘የእባቡ ዘር’ ይሖዋንም ሆነ ሕዝቡን የሚቃወሙትን የሰይጣንን መንፈስ የሚያንጸባርቁ መላእክትንና ሰዎችን በሙሉ ያመለክታል። ‘የእባቡ ራስ መቀጥቀጥ’ ደግሞ የይሖዋን ስም ያጠፋውና በሰው ዘር ላይ ታላቅ መከራ ያመጣው ዓመጸኛው ሰይጣን መጨረሻ ላይ የሚደርስበትን ጥፋት ያሳያል። ይሁንና የእባቡን ራስ የሚቀጠቅጠው ዘር ዋነኛ ክፍል ማን ነው? ይህ ለብዙ መቶ ዘመናት “ምስጢር” ሆኖ ቆይቷል።—ሮሜ 16:20, 25, 26

4. የኢየሱስ የዘር ሃረግ ትንቢት የተነገረለት ዘር እርሱ መሆኑን ለማወቅ የሚረዳው እንዴት ነው?

4 በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ 2,000 ዓመታት ገደማ ካለፉ በኋላ ይሖዋ ተጨማሪ መግለጫዎች ሰጥቷል። ዘሩ በአብርሃም የትውልድ ሃረግ በኩል እንደሚገለጥ ጠቆመ። (ዘፍጥረት 22:15-18) ሆኖም ወደ ዘሩ የሚያደርሰው ይህ የትውልድ መሥመር በአምላክ ምርጫ እንጂ በሥጋዊ የትውልድ ሃረግ ላይ ብቻ የተመካ አልነበረም። አብርሃም ከአጋር የወለደውን ልጁን እስማኤልን ይወደው የነበረ ቢሆንም ይሖዋ ‘ኪዳኔን ሣራ ከምትወልድልህ ልጅ፣ ከይስሐቅ ጋር አደርጋለሁ’ ሲል ነግሮታል። (ዘፍጥረት 17:18-21) ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ይህን ቃል ኪዳን ያጸናው የይስሐቅ የበኩር ልጅ ከሆነው ከዔሳው ጋር ሳይሆን የእስራኤል 12 ነገዶች አባት ከሆነው ከያዕቆብ ጋር ነበር። (ዘፍጥረት 28:10-14) ውሎ አድሮ ደግሞ ዘሩ በይሁዳ ነገድ በዳዊት የትውልድ ሃረግ በኩል እንደሚመጣ የሚጠቁም ትንቢት ተነገረ።—ዘፍጥረት 49:10፤ 1 ዜና መዋዕል 17:3, 4, 11-14

5. ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን በጀመረበት ጊዜ መሲሕ መሆኑ በግልጽ የታወቀው እንዴት ነው?

5 የዘሩን ማንነት የሚጠቁሙ ምን ተጨማሪ ፍንጮች አሉ? መጽሐፍ ቅዱስ ከ700 ዓመታት አስቀድሞ ዘሩ ቤተልሔም በምትባል ሥፍራ ሰው ሆኖ እንደሚወለድ ተናግሮ ነበር። በተጨማሪም ዘሩ “ከቀድሞ ዘመን” ጀምሮ ማለትም በሰማይ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ይኖር እንደነበረ ይጠቁማል። (ሚክያስ 5:2) በምድር ላይ መሲሕ ሆኖ የሚገለጥበት ትክክለኛ ጊዜም በነቢዩ ዳንኤል አማካኝነት ተተንብዮ ነበር። (ዳንኤል 9:24-26) ኢየሱስ ይሖዋ የላከው መሲሕ ሆኖ በመንፈስ ቅዱስ በተቀባበት ወቅት ከሰማይ የተሰማው የአምላክ ድምፅ ኢየሱስ ልጁ መሆኑን በግልጽ አስታውቋል። (ማቴዎስ 3:16, 17) በዚህ መንገድ የዘሩ ማንነት ታወቀ! በመሆኑም ፊልጶስ “ሙሴ በሕግ መጻሕፍት፣ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን . . . ኢየሱስን አግኝተነዋል” ሲል በእርግጠኝነት መናገር ችሏል።—ዮሐንስ 1:45

6. (ሀ) ሉቃስ 24:27 በሚገልጸው መሠረት የኢየሱስ ተከታዮች ምን ነገር ማስተዋል ችለዋል? (ለ) ‘የሴቲቱ ዘር’ ዋነኛ ክፍል ማን ነው? የእባቡ ራስ መቀጥቀጥስ ምን ትርጉም አለው?

6 ከዚያ በኋላ የኢየሱስ ተከታዮች እሱን በተመለከተ የተነገሩ በርካታ ትንቢቶች በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እንደተካተቱ ማስተዋል ችለዋል። (ሉቃስ 24:27) ኢየሱስ የእባቡን ራስ የሚቀጠቅጠው ማለትም ሰይጣንን ከሕልውና ውጭ የሚያደርገው ‘የሴቲቱ ዘር’ ዋነኛ ክፍል እንደሆነ ይበልጥ ግልጽ ሆነ። በጉጉት የምንጠብቃቸው አምላክ ለሰው ዘሮች የሰጣቸው ተስፋዎች ሁሉ በኢየሱስ አማካኝነት ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ።—2 ቆሮንቶስ 1:20

7. በትንቢት የተነገረለትን መሲሕ ማንነት ከማወቅ በተጨማሪ ምን መገንዘብ ያስፈልጋል?

7 ይህን ማወቃችን በእኛ ላይ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን ዘር ስለሚቤዠው መሲሕ የተነገሩትን አንዳንድ ትንቢቶች ስላነበበ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ይናገራል። ጃንደረባው ባነበበው ነገር ግራ በመጋባት ወንጌላዊውን ፊልጶስን “ነቢዩ ይህን የሚናገረው ስለ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። ሆኖም ጃንደረባው ፊልጶስ የሰጠውን መልስ ሰምቶ ዝም አላለም። ፊልጶስ የሰጠውን ማብራሪያ በጥሞና ካዳመጠ በኋላ ፍጻሜ ያገኘውን ይህን ትንቢት በሚገባ መረዳቱ የበኩሉን እርምጃ መውሰድ እንደሚጠይቅበት ተሰምቶታል። መጠመቅ እንደሚያስፈልገው ተገንዝቧል። (የሐዋርያት ሥራ 8:32-38፤ ኢሳይያስ 53:3-9) እኛስ ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ እንነሳሳለን?

8. (ሀ) አብርሃም ይስሐቅን መሥዋዕት ሊያደርግ የነበረ መሆኑ ምን ያመለክታል? (ለ) ይሖዋ አሕዛብ ሁሉ በዘሩ ራሳቸውን እንደሚባርኩ ለአብርሃም የነገረው ለምንድን ነው? ይህስ ዛሬ ለእኛ የሚሠራው እንዴት ነው?

8 ከዚህም በተጨማሪ አብርሃም ከሣራ የወለደውን አንድ ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት ሊያደርግ እንደነበረ የሚገልጸውን ልብ የሚነካ ታሪክ ተመልከት። (ዘፍጥረት 22:1-18) ይህ ታሪክ ይሖዋ አንድያ ልጁን መሥዋዕት አድርጎ እንደሚሰጥ የሚያመለክት ነበር:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአል።” (ዮሐንስ 3:16) ይህም ይሖዋ ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሲል አንድያ ልጁን እንደሰጠ ሁሉ ‘ሁሉን ነገር በልግስና እንደሚሰጠን’ እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል። (ሮሜ 8:32) ታዲያ ከእኛ የሚፈለገው ምንድን ነው? ዘፍጥረት 22:18 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ይሖዋ ለአብርሃም ‘የአምላክን ቃል በመስማቱ’ አሕዛብ ሁሉ በዘሩ አማካኝነት ራሳቸውን እንደሚባርኩ ነግሮት ነበር። እኛም ይሖዋንና ልጁን መስማት ያስፈልገናል:- “በወልድ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ በወልድ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በላዩ ይሆናል እንጂ ሕይወትን አያይም።”—ዮሐንስ 3:36

9. በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ያገኘነውን የዘላለም ሕይወት ተስፋ የምናደንቅ ከሆነ ምን እናደርጋለን?

9 በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ያገኘነውን የዘላለም ሕይወት ተስፋ የምናደንቅ ከሆነ ይሖዋ በኢየሱስ በኩል የተናገረውን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ እንጥራለን። ይህ ቃል ለአምላክና ለሰዎች ካለን ፍቅር ጋር የተያያዘ ነው። (ማቴዎስ 22:37-39) ኢየሱስ እሱ ‘ያዘዘንን ሁሉ እንዲጠብቁ’ ሌሎችን ለማስተማር የሚያነሳሳን ለይሖዋ ያለን ፍቅር መሆኑን አመልክቷል። (ማቴዎስ 28:19, 20) በተጨማሪም አብረውን ይሖዋን ከሚያገለግሉ ሰዎች ጋር ዘወትር ‘በመሰብሰብ’ ይህን ፍቅር ልናሳያቸው ይገባል። (ዕብራውያን 10:25፤ ገላትያ 6:10) አምላክንና ልጁን ለመስማት በምንጥርበት ጊዜ ከእኛ ፍጽምናን እንደማይጠብቁ ማስታወስ ይኖርብናል። ዕብራውያን 4:15 ኢየሱስ ሊቀ ካህናችን እንደመሆኑ መጠን ‘በድካማችን ሊራራልን’ እንደሚችል ይናገራል። ይህን ማወቃችን በተለይ ያሉብንን ድክመቶች ለማሸነፍ እንዲረዳን በክርስቶስ በኩል ወደ አምላክ በምንጸልይበት ጊዜ በእጅጉ ያጽናናናል!—ማቴዎስ 6:12

በክርስቶስ ላይ እምነት እንዳለህ አሳይ

10. መዳን የሚቻለው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ የሆነው ለምንድን ነው?

10 ሐዋርያው ጴጥሮስ በኢየሩሳሌም ለሚገኘው የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በኢየሱስ ላይ እንደተፈጸመ ከገለጸ በኋላ “ድነት በሌላ በማንም አይገኝም፤ እንድንበት ዘንድ ለሰዎች የተሰጠ ከዚህ ስም በስተቀር ሌላ ስም ከሰማይ በታች የለምና” ብሎ በእርግጠኝነት በመናገር ንግግሩን ደምድሟል። (የሐዋርያት ሥራ 4:12) የአዳም ዘሮች በሙሉ ኃጢአተኞች በመሆናቸው የእነሱ ሞት ለማንም ቤዛ ሆኖ ሊያገለግል አይችልም። ሆኖም ኢየሱስ ፍጹም ስለሆነ ሕይወቱ መሥዋዕታዊ ዋጋ አለው። (መዝሙር 49:6-9፤ ዕብራውያን 2:9) ኢየሱስ፣ አዳም ካጠፋው ፍጹም ሕይወት ጋር እኩል ዋጋ ያለው ቤዛ ለአምላክ አቅርቧል። (1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6) ይህም አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት የምናገኝበትን አጋጣሚ ከፍቶልናል።

11. የኢየሱስ መሥዋዕት በእጅጉ ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት እንደሆነ አስረዳ።

11 ቤዛው በአሁኑ ጊዜም እንኳ ሳይቀር ሌሎች ጥቅሞችን ማግኘት የምንችልበትን መንገድ ከፍቶልናል። ለምሳሌ ያህል፣ ኃጢአተኞች ብንሆንም እንኳ የኢየሱስ መሥዋዕት የኃጢአት ይቅርታ በማግኘት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረን አስችሎናል። ይህም እስራኤላውያን የሙሴ ሕግ በሚጠይቀው መሠረት የእንስሳ መሥዋዕት በማቅረብ ያገኙ ከነበረው የኃጢአት ይቅርታ በእጅጉ የላቀ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 13:38, 39፤ ዕብራውያን 9:13, 14፤ 10:22) ይሁን እንጂ እንዲህ ያለውን የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት የክርስቶስ መሥዋዕት ምን ያህል እንደሚያስፈልገን አምነን መቀበል ይኖርብናል:- “ኀጢአት የለብንም ብንል፣ ራሳችንን እናስታለን፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። ኀጢአታችንን ብንናዘዝ ኀጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከዐመፃም ሁሉ ሊያነጻን እርሱ ታማኝና ጻድቅ ነው።”—1 ዮሐንስ 1:8, 9

12. በውኃ መጠመቅ በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና ለማግኘት ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው?

12 ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች በክርስቶስና በመሥዋዕቱ ላይ እምነት እንዳላቸው ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሰዎች አማኞች በሚሆኑበት ጊዜ ይህን እምነታቸውን በሕዝብ ፊት በይፋ ያሳዩ ነበር። ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው? ይጠመቁ ነበር። ለምን? ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ እንዲጠመቁ ስላዘዘ ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ የሐዋርያት ሥራ 8:12፤ 18:8) አንድ ሰው ይሖዋ በኢየሱስ በኩል ላደረገው ፍቅራዊ ዝግጅት ልባዊ አድናቆት ካደረበት እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አይልም። በሕይወቱ ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችን ሁሉ ያደርጋል፣ በጸሎት አማካኝነት ራሱን ለአምላክ ይወስናል ይህንንም በጥምቀት ያሳያል። በዚህ መንገድ እምነቱን በመግለጽ አምላክ ‘ንጹሕ ሕሊና’ እንዲሰጠው ይማጸናል።—1 ጴጥሮስ 3:21

13. ኃጢአት እንደሠራን ከተገነዘብን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለምንስ?

13 እርግጥ ነው፣ ከተጠመቅንም በኋላ ቢሆን የኃጢአት ዝንባሌ በውስጣችን መኖሩ አይቀርም። ታዲያ ምን ማድረግ እንችላለን? ሐዋርያው ዮሐንስ “ይህን የምጽፍላችሁ ኀጢአት እንዳትሠሩ ነው፤ ነገር ግን ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው።” (1 ዮሐንስ 2:1, 2) እንዲህ ሲባል ምንም ዓይነት ኃጢአት ብንሠራ አምላክ ይቅር እንዲለን በጸሎት እስከጠየቅነው ድረስ የኃጢአት ይቅርታ እናገኛለን ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይቻልም። የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት ቁልፉ እውነተኛ ንስሐ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የበለጠ ተሞክሮ ካላቸው የክርስቲያን ጉባኤ ሽማግሌዎች እርዳታ ማግኘት ሊያስፈልገን ይችላል። የፈጸምነውን ኃጢአት ላለመድገም ልባዊ ጥረት ማድረግ እንድንችል ድርጊቱ ስህተት መሆኑን አምነን መቀበልና ከልብ መጸጸት ይኖርብናል። (የሐዋርያት ሥራ 3:19፤ ያዕቆብ 5:13-16) ይህን ካደረግን ኢየሱስ እንደሚረዳንና የይሖዋን ሞገስ መልሰን እንደምናገኝ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።

14. (ሀ) የኢየሱስ መሥዋዕት ያስገኘልንን ከፍተኛ ጥቅም ግለጽ። (ለ) እምነት ካለን ምን እናደርጋለን?

14 ኢየሱስ ያቀረበው መሥዋዕት በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተገለጸው ዘር ሁለተኛ ደረጃ አባላት የሆኑትና ‘ታናሽ መንጋ’ ተብለው የተጠሩት ሰዎች በሰማይ ዘላለማዊ ሕይወት ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ከፍቶላቸዋል። (ሉቃስ 12:32፤ ገላትያ 3:26-29) በቢሊዮን ለሚቆጠሩ ሌሎች የሰው ዘሮች ደግሞ ገነት በምትሆን ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ከፍቷል። (መዝሙር 37:29፤ ራእይ 20:11, 12፤ 21:3, 4) የዘላለም ሕይወት ‘በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው።’ (ሮሜ 6:23፤ ኤፌሶን 2:8-10) በዚህ ስጦታ ላይ እምነት ካለንና ስጦታው ሊገኝ የቻለበትን መንገድ የምናደንቅ ከሆነ ይህን በተግባር እናሳያለን። ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም ኢየሱስን እንዴት አስደናቂ በሆነ መንገድ እንደተጠቀመበትና ሁላችንም የኢየሱስን ፈለግ መከተላችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ስለምንረዳ ክርስቲያናዊው አገልግሎት በሕይወታችን ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ እንዲይዝ እናደርጋለን። ይህን ዕጹብ ድንቅ የአምላክ ስጦታ በተመለከተ ለሌሎች ሰዎች በእርግጠኝነት ስንናገር እምነታችን በግልጽ ይታያል።—የሐዋርያት ሥራ 20:24

15. በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን አንድነት የሚያስገኘው እንዴት ነው?

15 እንዲህ ያለው እምነት ግሩም የሆነ አንድነት ያስገኛል! በዚህ እምነት አማካኝነት ከይሖዋ፣ ከልጁና በክርስቲያን ጉባኤ ካሉት ጋር ይበልጥ መቀራረብ ችለናል። (1 ዮሐንስ 3:23, 24) ይህ እምነት ይሖዋ “[ከአምላክ ስም በስተቀር] ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም” ለልጁ በደግነት በመስጠቱ እንድንደሰት ያደርገናል። ይህንንም ያደረገው “በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ” ነው።—ፊልጵስዩስ 2:9-11

የክለሳ ውይይት

• መሲሑ በተገለጠበት ወቅት በአምላክ ቃል ከልባቸው ያምኑ ለነበሩ ሰዎች ማንነቱ ግልጽ የነበረው ለምንድን ነው?

• ኢየሱስ ለከፈለው መሥዋዕት አድናቆት እንዳለን ለማሳየት ልናደርጋቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

• የኢየሱስ መሥዋዕት በአሁኑ ጊዜ የጠቀመን በምን መንገዶች ነው? ይህስ የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ በምንጸልይበት ጊዜ የሚረዳን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 36 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ የአምላክን ትእዛዛት እንዲጠብቁ ሌሎች ሰዎችን ያስተምሩ ዘንድ ተከታዮቹን አዟቸዋል