በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ክፋት እንዲቀጥል በመፍቀዱ ምን ተምረናል?

አምላክ ክፋት እንዲቀጥል በመፍቀዱ ምን ተምረናል?

ምዕራፍ ሰባት

አምላክ ክፋት እንዲቀጥል በመፍቀዱ ምን ተምረናል?

1, 2. (ሀ) ይሖዋ አዳምና ሔዋን በኤደን ባመጹበት ጊዜ ወዲያው ቢያጠፋቸው ኖሮ እኛ ምን እንሆን ነበር? (ለ) ይሖዋ ምን ፍቅራዊ ዝግጅቶች አድርጎልናል?

የዕብራውያን አባት የሆነው ያዕቆብ “የሕይወቴ ዘመኖች ጥቂትም ክፉም ሆኑብኝ” ሲል ተናግሯል። (ዘፍጥረት 47:9 የ1954 ትርጉም) በተመሳሳይም ኢዮብ የሰው ልጅ “ዘመኑ አጭርና በመከራ የተሞላ ነው” ሲል ገልጿል። (ኢዮብ 14:1) ልክ እንደ እነሱ አብዛኞቻችን የተለያዩ ችግሮች፣ ግፍ አልፎ ተርፎም እጅግ አሳዛኝ የሆኑ ሁኔታዎች ደርሰውብናል። ይሁን እንጂ አምላክ እኛን መፍጠሩ ምንም ስህተት የለውም። እርግጥ ነው፣ አዳምና ሔዋን መጀመሪያ ላይ የነበራቸው ዓይነት ፍጹም አእምሮና አካል የለንም፤ እንዲሁም የምንኖረው ገነት በሆነች ምድር ላይ አይደለም። ይሁንና ይሖዋ አዳምና ሔዋን ባመጹበት ጊዜ ወዲያውኑ ቢያጠፋቸው ኖሮ ምን ሁኔታ ይፈጠር ነበር? እርግጥ ነው፣ ወዲያው ቢያጠፋቸው ኖሮ በሽታ፣ ሐዘን ወይም ሞት እንደማይኖር የታወቀ ቢሆንም የሰው ዘርም አይኖርም ነበር። እኛም ብንሆን አንወለድም ነበር። አምላክ፣ ምንም እንኳ የሚወለዱት ልጆች አለፍጽምናን የወረሱ እንደሚሆኑ ቢያውቅም በምሕረቱ ተገፋፍቶ አዳምና ሔዋን ልጅ እንዲወልዱ ጊዜ ሰጥቷቸዋል። እንዲሁም ይሖዋ አዳም ያሳጣንን ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ በክርስቶስ አማካኝነት መልሰን እንድናገኝ ዝግጅት አድርጓል።—ዮሐንስ 10:10፤ ሮሜ 5:12

2 ገነት በሆነች ምድር ላይ ከበሽታ፣ ከሐዘን፣ ከሥቃይና ከሞት እንዲሁም ክፉ ከሆኑ ሰዎች ተገላግለን ለዘላለም የመኖር ተስፋ ከፊታችን የተዘረጋ መሆኑ እንዴት የሚያጽናና ነው! (ምሳሌ 2:21, 22፤ ራእይ 21:4, 5) ይሁን እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደምንረዳው የእኛ መዳን ለእኛም ሆነ ለይሖዋ አስፈላጊ ነገር ቢሆንም ከዚህ የላቀ ግምት የሚሰጠው ሌላ ጉዳይ አለ።

ለታላቅ ስሙ ሲል

3. ይሖዋ ለምድርና ለሰው ዘር ያለው ዓላማ ፍጻሜ ከምን ነገር ጋር የተያያዘ ነው?

3 አምላክ ለምድርና ለሰው ዘር ያለው ዓላማ መፈጸሙ ከስሙ ጋር የተያያዘ ነው። ይሖዋ የተባለው ስሙ “ይሆናል” የሚል ትርጉም አለው። ስለዚህ ስሙ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታና የእውነት አምላክ እንደሆነ እንዲሁም ዓላማ ያለውና ይህንንም ዓላማውን ዳር የሚያደርስ አምላክ መሆኑን ያመለክታል። ይሖዋ ካለው ሥልጣን አኳያ መላው ጽንፈ ዓለም ሰላምና ደኅንነቱ ይጠበቅ ዘንድ የአምላክ ስምና ስሙ የሚወክላቸው ነገሮች ሙሉ እውቅና ማግኘታቸው በጣም አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ ፍጥረታት ሁሉ ለእሱ መታዘዛቸው የተገባ ነው።

4. ይሖዋ ለምድር ያለው ዓላማ ምንን ይጨምራል?

4 ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ ሥራ ሰጣቸው። ገነትን በማስፋት መላዋን ምድር እንዲገዙ ብቻ ሳይሆን በዘሮቻቸውም እንዲሞሏት ጭምር ዓላማው መሆኑን ገልጾላቸዋል። (ዘፍጥረት 1:28) እነሱ በሠሩት ኃጢአት ይህ ዓላማው ተጨናግፎ ይቀር ይሆን? ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው ይሖዋ ለዚህች ምድርና ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ዳር ማድረስ ሳይችል ቢቀር በስሙ ላይ ከፍተኛ ነቀፋ እንደሚያመጣ የታወቀ ነው!

5. (ሀ) የመጀመሪያዎቹ ሰዎች መልካምና ክፉውን ከሚያሳውቀው ዛፍ ከበሉ መቼ እንደሚሞቱ ተነግሯቸው ነበር? (ለ) ይሖዋ ለምድር የነበረውን ዓላማ ሳያስተጓጉል በ⁠ዘፍጥረት 2:17 ላይ የተናገረውን ቃል የፈጸመው እንዴት ነው?

5 ይሖዋ አዳምና ሔዋን ትእዛዙን በመጣስ መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ ከበሉ በዚያው “ቀን” እንደሚሞቱ አስጠንቅቋቸው ነበር። (ዘፍጥረት 2:17) ይሖዋ በተናገረው ቃል መሠረት ኃጢአት በሠሩበት ቀን በጥፋታቸው ተጠያቂ በማድረግ የሞት ፍርድ በይኖባቸዋል። ከአምላክ አመለካከት አንጻር አዳምና ሔዋን በዚያኑ ዕለት ሞተዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ለምድር ያለውን ዓላማ ዳር ለማድረስ ሲል በአካላዊ ሁኔታ ከመሞታቸው በፊት ልጆች እንዲወልዱ ፈቀደላቸው። አምላክ 1,000 ዓመትን እንደ አንድ ቀን መመልከት የሚችል በመሆኑ የአዳም ሕይወት በ930 ዓመቱ ሲያከትም በዚያው በአንድ “ቀን” ውስጥ እንደሞተ ሊቆጠር ይችላል። (2 ጴጥሮስ 3:8፤ ዘፍጥረት 5:3-5) በዚህ መንገድ ይሖዋ በእነሱ ላይ የቅጣት ፍርዱን የሚያስፈጽምበትን ጊዜ በተመለከተ የተናገረው ቃል እውነተኝነት የተረጋገጠ ከመሆኑም በላይ ለምድር ያለው ዓላማ በእነሱ ሞት ምክንያት አልተጨናገፈም። ሆኖም ለተወሰነ ጊዜ ክፉዎችን ጨምሮ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች በሕይወት እንዲኖሩ ተፈቅዶላቸዋል።

6, 7. (ሀ) ዘፀአት 9:15, 16 በሚገልጸው መሠረት ይሖዋ ክፉዎች ለተወሰነ ጊዜ እንዲቀጥሉ የፈቀደው ለምንድን ነው? (ለ) ከፈርዖን ጋር በተያያዘ የይሖዋ ኃይል የተገለጠውና ስሙ የታወቀው እንዴት ነው? (ሐ) አሁን ያለው ክፉ ሥርዓት ሲደመደም ውጤቱ ምን ይሆናል?

6 ይሖዋ በሙሴ ዘመን ለግብጹ ገዥ የተናገረው ቃል ክፉዎች በሕይወት እንዲቀጥሉ የፈቀደበትን ምክንያት ይበልጥ ግልጽ ያደርግልናል። ፈርዖን የእስራኤል ልጆች ከግብጽ እንዳይወጡ በከለከለበት ጊዜ ይሖዋ ወዲያው አላጠፋውም። የይሖዋ ኃይል አስደናቂ በሆነ መንገድ የተገለጠባቸው አሥር መቅሰፍቶች በምድሪቱ ላይ ወርደዋል። ይሖዋ ፈርዖንን ሰባተኛ መቅሰፍት እንደሚያመጣ ባስጠነቀቀው ጊዜ እርሱንና ሕዝቡን በቀላሉ ከምድር ገጽ ሊያጠፋቸው ይችል እንደነበር ገልጾለታል። “ነገር ግን ኀይሌን እንዳሳይህና ስሜም በምድር ዙሪያ ሁሉ እንዲታወቅ ለዚህ አስነሥቼሃለሁ” ብሎታል።—ዘፀአት 9:15, 16

7 በእርግጥም ይሖዋ እስራኤላውያንን ነፃ ባወጣበት ጊዜ ስሙ በስፋት ታውቋል። (ኢያሱ 2:1, 9-11) ይህ ከሆነ ከ3,500 ዓመታት በላይ ያለፉ ቢሆንም ይሖዋ በዚያን ጊዜ ያደረገው ነገር ዛሬም አልተረሳም። በዚያን ጊዜ የታወቀው ይሖዋ የሚለው የግል መጠሪያ ስሙ ብቻ ሳይሆን የዚህ ስም ባለቤት የሆነው አምላክ እውነተኛ ማንነትም ጭምር ነው። በዚያን ጊዜ የተፈጸመው ነገር ይሖዋ ቃሉን የሚጠብቅና አገልጋዮቹን ለመታደግ ሲል አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስድ አምላክ እንደሆነ አረጋግጧል። (ኢያሱ 23:14) ሁሉን ለማድረግ የሚያስችል ኃይል ያለው በመሆኑ ዓላማውን ዳር እንዳያደርስ ሊያግደው የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ በግልጽ ታይቷል። (ኢሳይያስ 14:24, 27) በመሆኑም በቅርቡ የሰይጣንን ክፉ ሥርዓት ጠራርጎ በማጥፋት ታማኝ አገልጋዮቹን እንደሚታደግ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ሁሉን ማድረግ የሚችለው የይሖዋ ኃይል የሚገለጥበት ይህ ክንውንና በዚያ ጊዜ የሚፈጸመው ነገር ለይሖዋ ስም የሚያመጣው ክብር ምንጊዜም የማይረሳ ይሆናል። የሚያስገኛቸው ጥቅሞችም ፍጻሜ አይኖራቸውም።—ሕዝቅኤል 38:23፤ ራእይ 19:1, 2

‘የእግዚአብሔር ጥበብ እንዴት ጥልቅ ነው!’

8. ጳውሎስ የትኞቹን ነጥቦች እንድናጤን አሳስቦናል?

8 ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “እግዚአብሔር አድልዎ ያደርጋልን?” የሚል ጥያቄ ካቀረበ በኋላ “በፍጹም አያደርግም!” ሲል በእርግጠኝነት መልስ ሰጥቷል። ከዚያም የአምላክን ምሕረት ጎላ አድርጎ የገለጸ ሲሆን ይሖዋ ፈርዖን ለተወሰነ ጊዜ እንዲቀጥል የፈቀደበትን ምክንያት አስመልክቶ የተናገረውን ቃልም ጠቅሷል። በተጨማሪም ጳውሎስ እኛ የሰው ልጆች በሸክላ ሠሪ እጅ እንዳለ ሸክላ እንደሆንን አመልክቷል። አክሎም እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “እግዚአብሔር ቍጣውን ለማሳየት፣ ኀይሉንም ለማሳወቅ ፈልጎ የቍጣው መግለጫ [“ዕቃዎች፣” የ1954 ትርጉም] የሆኑትን፣ ለጥፋትም የተዘጋጁትን እጅግ ታግሦ ቢሆንሳ! አስቀድሞ ለክብር ላዘጋጃቸው፣ የምሕረቱም መግለጫዎች [“ዕቃዎች፣” የ1954 ትርጉም] ለሆኑት፣ የክብሩ ባለ ጠግነት እንዲታወቅ ይህን አድርጎ እንደ ሆነስ? የጠራው ከአይሁድ ወገን ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብ ወገን የሆ[ን]ነውን እኛን እንኳ ሳይቀር አይደለምን?”—ሮሜ 9:14-24

9. (ሀ) ‘ለጥፋት የተዘጋጁት የቁጣ’ ዕቃዎች እነማን ናቸው? (ለ) ይሖዋ ለተቃዋሚዎቹ ትዕግሥት ያሳየው ከምን አንጻር ነው? የመጨረሻው ውጤትስ ለሚወዱት ሁሉ መልካም የሚሆንላቸው እንዴት ነው?

9 በኤደን ዓመጽ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ይሖዋንም ሆነ እሱ ያወጣውን ሕግ የሚቃወሙ ሁሉ ‘ለጥፋት የተዘጋጁ የቁጣ ዕቃዎች’ ሆነዋል። ይሖዋ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ለረጅም ጊዜ ታግሷል። ክፉዎች እሱ በሚወስዳቸው እርምጃዎች ተሳልቀዋል፣ አገልጋዮቹን አሳደዋል አልፎ ተርፎም ልጁን ገድለዋል። ይሖዋ የሰው ልጅ በእሱ ላይ ማመጹም ሆነ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር መምረጡ የሚያስከትላቸውን መጥፎ ውጤቶች መላው ፍጥረት መመልከት የሚችልበት በቂ ጊዜ በመፍቀድ ከፍተኛ ትዕግሥት አሳይቷል። ከዚህም በተጨማሪ የኢየሱስ ሞት ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን ነፃ ለማውጣትና ‘የዲያብሎስን ሥራ ለማፍረስ’ የሚያስችል መንገድ ከፍቷል።—1 ዮሐንስ 3:8፤ ዕብራውያን 2:14, 15

10. ይሖዋ ላለፉት 1,900 ዓመታት ክፉዎችን የታገሠው ለምንድን ነው?

10 ኢየሱስ ከሞት ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ ከ1,900 ለሚበልጡ ዓመታት ይሖዋ ‘በቁጣ ዕቃዎች’ ላይ የጥፋት እርምጃ ከመውሰድ በመታቀብ ተጨማሪ ትዕግሥት አሳይቷል። ለምን? አንደኛው ምክንያት በሰማያዊው መንግሥት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚገዙትን ለመሰብሰብ ሲል ነው። እነዚህ ሰዎች ቁጥራቸው 144,000 ሲሆን ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የምሕረት ዕቃዎች’ ሲል ጠርቷቸዋል። መጀመሪያ የዚህ ሰማያዊ ክፍል አባላት እንዲሆኑ የተጠሩት አይሁዳውያን ነበሩ። ከጊዜ በኋላ አምላክ ከአሕዛብ ወገን ለሆኑ ሰዎችም ይህን ጥሪ አቅርቧል። ይሖዋ እነዚህ ሰዎች እንዲያገለግሉት አላስገደዳቸውም። ከዚህ ይልቅ ፍቅራዊ ዝግጅቶቹን ከሚያደንቁ ሰዎች መካከል የተወሰኑት በሰማያዊው መንግሥት ከልጁ ጋር ተባባሪ ገዥዎች የመሆን መብት እንዲያገኙ አድርጓል። አሁን የዚህን ሰማያዊ ክፍል አባላት የመሰብሰቡ ሥራ ተገባዷል።—ሉቃስ 22:29፤ ራእይ 14:1-4

11. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ ከይሖዋ ትዕግሥት እየተጠቀመ ያለው ቡድን የትኛው ነው? (ለ) ሙታን ምን አጋጣሚ ያገኛሉ?

11 ሆኖም ምድር ላይ ስለሚኖሩ ሰዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? ይሖዋ መታገሡ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጣ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” እንዲሰበሰብም አስችሏል። ይህ ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠር ሆኗል። ይሖዋ ምድራዊ ተስፋ ያለው ይህ ሕዝብ በዚህ ሥርዓት ላይ ከሚመጣው ጥፋት ተርፎ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኝ ቃል ገብቷል። (ራእይ 7:9, 10፤ መዝሙር 37:29፤ ዮሐንስ 10:16) አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሙታን ተነስተው የሰማያዊው መንግሥት ምድራዊ ተገዥዎች የመሆን አጋጣሚ ያገኛሉ። የአምላክ ቃል በሐዋርያት ሥራ 24:15 ላይ “ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን [ይነሳሉ]” ሲል ተንብዮአል።—ዮሐንስ 5:28, 29

12. (ሀ) ይሖዋ ክፋትን በመታገሡ ስለ እሱ ምን ተምረናል? (ለ) ይሖዋ ለእነዚህ ጉዳዮች እልባት ለመስጠት ስለወሰደው እርምጃ ምን ይሰማሃል?

12 ታዲያ ይህ ሁሉ ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ነው ሊባል ይችላል? በፍጹም፤ ምክንያቱም አምላክ ክፉዎችን ወይም ‘የቁጣ ዕቃዎችን’ ሳያጠፋ ታግሦ በመቆየት ከዓላማው ጋር በሚስማማ መንገድ ለሌሎች ርኅራኄ አሳይቷል። ይህም ይሖዋ ምን ያህል መሐሪና አፍቃሪ አምላክ እንደሆነ ያሳያል። በተጨማሪም ዓላማው ደረጃ በደረጃ ሲገለጥ ለማየት የሚያስችል ጊዜ በማግኘታችን ስለ ራሱ ስለ ይሖዋ ብዙ እንማራለን። ስለተለያዩ ባሕርያቱ ማለትም ስለ ፍትሑ፣ ስለ ምሕረቱ፣ ስለ ትዕግሥቱና ብዙ ገጽታ ስላለው ጥበቡ የምናገኘው ግንዛቤ እንድንደነቅ ያደርገናል። ይሖዋ በጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱ ማለትም በመግዛት መብቱ ላይ የተነሳውን ጥያቄ ጥበብ በተሞላበት መንገድ ለመፍታት የወሰደው እርምጃ አገዛዙ ተወዳዳሪ እንደማይገኝለት የሚያሳይ ማስረጃ ሆኖ ለዘላለም ይኖራል። እኛም “የእግዚአብሔር የጥበቡና የዕውቀቱ ባለ ጠግነት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱ አይመረመርም፤ ለመንገዱም ፈለግ የለውም!” የሚሉትን የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት እናስተጋባለን።—ሮሜ 11:33

ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የምናሳይበት አጋጣሚ

13. በግለሰብ ደረጃ መከራ ሲደርስብን ምን የማድረግ አጋጣሚ እናገኛለን? በዚህ ረገድ ጥሩ ምላሽ እንድንሰጥ ሊረዳን የሚችለውስ ምንድን ነው?

13 ብዙዎቹ የአምላክ አገልጋዮች በግለሰብ ደረጃ መከራ ይደርስባቸዋል። አምላክ ገና ክፉዎችን ስላላጠፋቸውና አስቀድሞ የተነገረለትን የሰው ዘር የተሐድሶ ዘመን ስላላመጣ በአምላክ አገልጋዮች ላይ የሚደርሰው መከራ ይቀጥላል። ይህ እንድንመረር ሊያደርገን ይገባል? ወይስ እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች የዲያብሎስን ውሸታምነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉን አጋጣሚዎች እንደሆኑ አድርገን እንመለከታቸዋለን? “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” የሚለውን ጥሪ ማስታወሳችን እንዲህ ያለ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። (ምሳሌ 27:11 የ1954 ትርጉም) ይሖዋን የሚሳደበው ሰይጣን ሰዎች ቁሳዊ ነገር አጥተው ቢቸገሩ ወይም አካላዊ ሥቃይ ቢደርስባቸው አምላክን እንደሚወቅሱ አልፎ ተርፎም እንደሚሳደቡ ተናግሯል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4, 5) ስለዚህ መከራ ሲደርስብን በታማኝነት ከጸናን የሰይጣን ክስ ሐሰት መሆኑን በማረጋገጥ የይሖዋን ልብ ደስ እናሰኛለን።

14. ፈተናዎች ሲደርሱብን በይሖዋ የምንታመን ከሆነ ምን ጥቅሞች ልናገኝ እንችላለን?

14 ፈተናዎች ሲደርሱብን በይሖዋ የምንታመን ከሆነ ውድ የሆኑ ባሕርያትን ማዳበር እንችላለን። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ የተለያዩ መከራዎች ሲደርሱበት ከዚያ በፊት በማያውቀው መንገድ ‘መታዘዝን ተምሯል።’ እኛም ፈተናዎች ሲደርሱብን ትዕግሥት፣ ጽናትና ለይሖዋ የጽድቅ መንገዶች የጠለቀ አድናቆት ልናዳብር እንችላለን።—ዕብራውያን 5:8, 9፤ 12:11፤ ያዕቆብ 1:2-4

15. መከራ ሲደርስብን በትዕግሥት መጽናታችን ሌሎችን ሊጠቅም የሚችለው እንዴት ነው?

15 ሌሎች የምናደርገውን ይመለከታሉ። አንዳንዶች ለጽድቅ ባለን ፍቅር ምክንያት የሚደርስብንን ነገር ሲመለከቱ በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች እነማን እንደሆኑ ከጊዜ በኋላ ሊያስተውሉ ይችላሉ። በአምልኮ ከእኛ ጋር በመተባበር የዘላለም ሕይወትን በረከቶች ለመውረስ ዝግጁ ሊሆኑ ይችላሉ። (ማቴዎስ 25:34-36, 40, 46) ይሖዋና ልጁ ሰዎች ይህን አጋጣሚ እንዲያገኙ ይፈልጋሉ።

16. በግለሰብ ደረጃ ለሚደርስብን መከራ ያለን አመለካከት ከአንድነት ጋር የተያያዘው እንዴት ነው?

16 እንግዲያው በሕይወታችን የሚደርሱብንን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለይሖዋ ያደርን መሆናችንን ለማሳየትና ፈቃዱን ለመፈጸም እንደሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርገን መመልከታችን መልካም ነው። እንደዚህ ማድረጋችን ከአምላክና ከክርስቶስ ጋር አንድ ለመሆን ጥረት እያደረግን እንዳለን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ኢየሱስ ሁሉንም እውነተኛ ክርስቲያኖች አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጸልዮአል:- “የእነርሱን ትምህርት ተቀብለው በእኔ ለሚያምኑ ጭምር እንጂ ለእነዚህ [ለቅርብ ደቀ መዛሙርቱ] ብቻ አልጸልይም፤ ይህም፣ አባት ሆይ፤ አንተ በእኔ፣ እኔም በአንተ እንዳለሁ ሁሉም አንድ እንዲሆኑ፣ . . . እነርሱም በእኛ እንዲሆኑ ነው።”—ዮሐንስ 17:20, 21

17. ለይሖዋ ታማኞች ከሆንን ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

17 ይሖዋ ለእሱ ታማኞች ከሆንን አብዝቶ ይባርከናል። ቃሉ “ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ፤ ምክንያቱም ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 15:58) በተጨማሪም “እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም . . . ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም” ሲል ይገልጻል። (ዕብራውያን 6:10) ያዕቆብ 5:11 ደግሞ እንዲህ ይላል:- “በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ፤ ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው።” ኢዮብ በመጨረሻ ያገኘው ውጤት ምን ነበር? “እግዚአብሔርም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን የኢዮብን ሕይወት ባረከ።” (ኢዮብ 42:10-16) አዎን፣ ይሖዋ ‘ከልብ ለሚሹት ዋጋ ይሰጣል።’ (ዕብራውያን 11:6) እኛም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ግሩም ተስፋ ይጠብቀናል!

18. ዛሬ ያሉን አሳዛኝ ትዝታዎች በአዲሱ ዓለም ውስጥ ቀስ በቀስ ምን ይሆናሉ?

18 የአምላክ መንግሥት ባለፉት ብዙ ሺህ ዓመታት በሰብዓዊው ኅብረተሰብ ላይ የደረሰውን ጉዳት ሙሉ በሙሉ ይጠግናል። በአሁኑ ጊዜ የሚደርስብን ማንኛውም መከራ በዚያን ጊዜ ከምናገኘው ደስታ ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በአዲሱ ዓለም ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የደረሰብንን ሥቃይ እያስታወስን አንረበሽም። በዚያን ጊዜ የሰዎች አእምሮ አስደሳች በሆኑ ሐሳቦችና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ስለሚጠመድ አሳዛኝ የሆኑ ትዝታዎቻቸው ቀስ በቀስ እየጠፉ ይሄዳሉ። ይሖዋ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “እኔ፣ አዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁ፤ ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤ አይታወሱም። ነገር ግን በምፈጥረው፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለዘላለም ሐሤት አድርጉ።” አዎን፣ በይሖዋ አዲስ ዓለም ውስጥ ጻድቃን “ምድር ሁሉ ሰላምና ዕረፍት አግኝታለች፤ የደስታም ዝማሬ ታስተጋባለች” ብለው መናገር ይችላሉ።—ኢሳይያስ 14:7፤ 65:17, 18

የክለሳ ውይይት

• ይሖዋ ክፋት እንዲቀጥል ቢፈቅድም ለስሙ ታላቅ አክብሮት ያሳየው እንዴት ነው?

• አምላክ ‘የቁጣ ዕቃዎችን’ መታገሡ ምሕረቱ ለእኛ እንዲደርስ ያስቻለው እንዴት ነው?

• በግለሰብ ደረጃ ከሚደርሱብን መከራዎች ጋር በተያያዘ ምን ነገር ለማስተዋል መጣር ይኖርብናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 67 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ይሖዋ “ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን የኢዮብን ሕይወት ባረከ”